10ኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህ ሳምንት ከሚያስተናግዳቸው ጨዋታዎች መሀከል ከፍ ያለ ግምት የተሰጠው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ ዛሬ 11 ሰዐት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋል። ይህን ጨዋታ አስመልክተን ያሰናዳነውን ፅሁፍ እንደሚከተለው አቅርበንላቸዋል።
ቦታ፡ አዲስ አበባ ስታድየም
ቀን፡ ሐሙስ ታህሳስ 26 2010
ሰዐት፡ 11፡00
ዳኞች፡ ዋና ዳኛ አማኑኤል ኃ/ስላሴ (ኢንተርናሽናል)
ረዳት ዳኞች፡ በላቸው ይታዩ እና አይሌው አሸናፊ (ፌደራል)
የቅርብ ጊዜ ውጤቶች
ቅዱስ ጊዮርጊስ | አቻ-አቻ-አሸ-አቻ-አሸ
ጅማ አባ ጅፋር | አሸ-አሸ-አሸ-አቻ-አቻ
ውርርድ | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1.19 ፣ አቻ 1.90 ፣ ጅማ አባ ጅፋር 2.20
(ይህን ሊንክ በመጫን ዝርዝሩን መመልከት እና መወራረድ ይችላሉ | ሁሉ ስፖርት)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ቢኖሩትም ቡድኖቹ በሊጉ በአንድ ነጥብ ተበላልጠው ከመሪው ደደቢት ቀጥሎ መቀመጣቸው የጨዋታውን ዋጋ ከፍ አድርጎታል። ምን አልባት ጨዋታው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተደረገ ቢሆን ኖሮ ያሁኑን ያህል ትኩረት ባላገኘ ነበር። የያኔው እና የአሁኑን ጅማ አባ ጅፋር ልዩነትን ለመግለፅ በአምስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ተስኖት ቆይቶ በመጨረሻዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ማስቆጠር መቻሉን መግለፅ ብቻ በቂ ነው። በተቃራኒው በለፉት አራት ጨዋታዎች አርባምንጭ ላይ ካስቆጠራቸው ሶስት ግቦች ውጪ ባልተለመደ መልኩ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የተሳነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀሪ ጨዋታዎቹን ከማድረጉ በፊት ከደደቢት ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ሳይችል ቀርቷል። ቢሆንም ቡድኑ አሁንም ከመሪዎቹ ተርታ መሰለፍ አልተሳነውም። ይህን ጨዋታ ካሸነፈም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችል ደደቢትንም በሁለት ነጥቦች ልዩነት የሚቀርብ ይሆናል። ድሉ ለጅማ አባ ጅፋር ከሆነ ደግሞ ቡድኑ አራተኛ ተከታታይ አሸናፊነትን በመጎናፀፍ ከሊጉ መሪዎች ጋር ተመሳሳይ ታሪክ መፃፍ ይችላል።
ያለፉት ሳምንታት የቡድኖቹ አቀራረብ
የአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ቡድን ወደ አሸናፊነት የመለሰውን አሰላለፍ እና የተጨዋቾች ምርጫ ሳይቀይር ነው ያለፉትን ሶስት ሳምንታት የዘለቀው። በሚጠቀምበት የ 4-4-2 አሰላለፍ ውስጥም የሁለቱ የመስመር አማካዮች ዮናስ ገረመው እና ሔኖክ ኢሳያስ ሚና ከፍ ያለ ነው። ከራሱ ሜዳ በምጀምሩ ፈጣን እና ድንገተኛ ጥቃቶች እየተለየ የመጣው አባ ጅፋር የእንቅስቃሴዎቹ ዋነኛ መነሻዎች ሁለቱ መስመሮች ናቸው። ተጨዋቾቹ ተጋጣሚ ወደ መከላከል ቅርፁ ከመመለሱ በፊት ኳስ በሚያገኙባቸው አጋጣሚዎች ወደ እነርሱ ቀርበው ለሚታዩት አጥቂዎች በማሳለፍ የመጨረሻ ዕድሎችን በመፍጠር ላይ ይገኛሉ። በመቀጠል የኦኪኪ አፎላቢ እና ተስመንገ ገ/ኪዳን የአጥቂ ክፍል ጥምረት የተገኙትን ዕድሎችን ወደ ግብ የሚቀይርበት ንፃሬ ከፍ ማለቱ ተጠቃሽ ነው። ይህም ቡድኑ የነበረበት የግብ ማግባት ችግር ሙሉ ለሙሉ እንዲቀረፍ ምክንያት ሆኗል። ሁለቱ የመሀል አማካዮችን ስንመለከት ደግሞ ለተከላካይ መስመሩ ሽፋን የመስጠት ሚናቸው ጎልቶ ይታያል። ቡድኑ በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል የሚሰነዘርበትን ጥቃት በማርገብ እና የተጋጣሚ የአጥቂ አማካዮችን በማፈን እዚህ ቦታ ላይ የሚጣመሩት ይሁን እንዳሻው እና አሚኑ ነስሩ በሶስቱ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ባስተናገደው የአባጅፋር ቡድን ውስጥ ከተከላካይ ክፍሉ ፊት የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቃሽ ነው።
አሰልጣኝ ቫዝ ፒኒቶ ቡድኑን ከያዙት ጀምሮ ለኳስ ቁጥጥር የሚሰጠው ቦታ የጨመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን አቀራረብ እንደ ብቸኛ የግብ ዕድል መፍጠሪያነት ሲጠቀምበት አይታይም። ኳስ ከግብ ጠባቂው ሲጀመር የተከላካይ አማካዩ ሙሉአለም መስፍን ነፃ በሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ተጨዋቹ ከፊት ለፊቱ የሚገኙትን ምንተስኖት አዳነን እና አብዱልከሪም ኒኪማን በቅብብሎች ለማግኘት በሚጥርባቸው አጋጣሚዎች የቡድኑ ማጥቃት ሲቀጥል በተሻለ ሁኔታ የኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ያደረገ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማየት ይቻላል። ሆኖም ሶስቱ አማካዮች በተጋጣሚ ተጨዋቾች ጫና ውስጥ የሚገኙ ከሆነ የኃላ መስመር ተሰላፊዎቹ በተለይም ሳላዲን ባርጌቾ በረዣዥም ኳሶች የፊት አጥቂዎቹን ለማግኘት ሲሞክሩ ይታያል። ኳስ በመስመር አጥቂዎቹ እግር ስር ስትሆንም ተሻጋሪ ኳሶችን በተደጋጋሚ መመልከታችን አልቀረም። ይህን ሁኔታ በተለይም በድኑ ከወልዋሎ ዓ.ዩ እና መከላከያ ጋር ያለግብ በተለያየባቸው ጨዋታዎች ላይ በስፋት ተመልክተነዋል። በመሆኑም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቀደመ አጨዋወቱ እየተመለሰ ነው ? የሚል ጥያቄን እንድናነሳ የሚያደርግ ቢሆንም የቡድኑ ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በዚህ ሀሳብ አይስማሙም። ጉዳዩን አስመልክተን ላቀረብንላቸው ጥያቄም ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።
” ስለወልዋሎው ጨዋታ ብዙ ማለት እይቻልም። ምክንያቱም እዛ ሜዳ ላይ ተጨዋቾችን ለመመዘን በጣም አስቸጋሪ ነው። ከሜዳው አንፃር ባሰብነው የጨዋታ ዘዴ ተጠቅመን ማሸነፍ ያስቸግራል። ስለዚህም የነበረን አማራጭ ግባቻንን እየጠበቅን በምናገኛቸው አጋጣሚዎች ሙከራዎችን ማድረግ ነበር። በመከላከያውም ጨዋታ ምንም የቀየርነው የአጨዋወት ዘዴ የለም። ሆኖም ተጋጣሚያችን የመጫወት ፍላጎት አልነበረውም። ዘጠኝ የሚደርሱ ተጨዋቾቻቸው በፍፁም ቅጣት ምት ክልል አካባቢ ተከማችተው ነበር። በመሆኑም ኳስ ከኃላ መስርተን ተጋጣሚያችንን ወደራሳችን የሜዳ ክልል በማምጣት ክፍተት ለመፍጠር የምንሞክርበትን አጨዋወት አልተገበርንም። በተለይ በመጨረሻዎቹ ሰዐታት ላይ ጎል ማግኘት ስለነበረብን አንዳንድ ጊዜ ሜዳ ውስጥ እንደሚኖረው እንቅስቃሴ የምንቀይራቸው ነገሮች ይኖራሉ። የተጨዋቾቹም ጎል የማስቆጠር ፍላጎት ተጨምሮበትም ረዣዥም ኳሶችን ተጠቅመናል። በተለይ አንዳንዶቹ ጎል ሊሁኑ ይገቡ የነበሩ እና ምክንያታዊ የሆኑ ነበሩ። ያው ጨዋታው አስገድዶን ሊሆን ይቻላል እንጂ የጨዋታ አስተሳሰባችን በሁለት እና ሶስት ጨዋታዎች የሚቀየር አይደለም። በዛ ውስጥ ስህተቶች ሲኖሩ በማረም እንዲሁም አንዳንዴ በልምምድ ላይ ዝግጅት የተደረገበት መንገድ መሰረቱን ሳይለቅ ለውጥ ያለ አቀራረብን ልንከተል እንችላለን።
የቡድን ዜናዎች
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው ሳላዲን ባርጌቾ ወደ ልምምድ መመለሱን የሰማን ሲሆን ከዚህ ውጪ ከሳላዲን ሰይድ ፣ ታደለ መንገሻ ፣ አሜ መሀመድ እና ናትናኤል ዘለቀ የረዥም ጉዳት በተጨማሪ በትላንትናው የልምምድ መርሀ ግብር ጋዲሳ መብራቴ መጎዳቱ ታውቋል። በተመሳሳይ ጌቱ ረፌራን ፣ አሸናፊ ሽብሩን እና ዝናቡ ባፋአን ለረጅም ጊዜ በጉዳት ያጣው ጅማ አባ ጅፋር በወልዋሎው ጨዋታ ከተጎዱበት ተጨዋቾች መሀከል ተመስገን ገ/ኪዳን እና ዮናስ ገረመው የተሻለ የጤንነት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እና ለዛሬው ጨዋታ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተነግሯል። ሆኖም የፊት አጥቂው ኦኪኪ አፎላቢ እና በወልዋሎው ጨዋታ ከነጉዳቱ ተሰልፎ የተጫወተው ሔኖክ ኢሳያስ ከጨዋታ ውጪ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው።
ከጨዋታው ምን ይጠበቃል ?
ጨዋታው የሁለቱም ቡድኖች ዋነኛ የማጥቃት አማራጮች የሚፈተኑበት እንደሚሆን ይገመታል። የጉዳት ዜናዎቹን ተከትሎ ሊሳሳ የሚችለው የአባ ጅፋር መስመር አማካዮች ጥቃትን የማስጀመር ሂደት የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አጥቂዎች በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ አብዝቶ የመቆየትን እንዲሁም የመስመር ተከላካዮቹን ወደ ኃላ የተሳበ አቋቋምን ተከትሎ የተሻለ የመንቀሳቀሻ ክፍተት ሊያስገኝለት ቢችልም በአራቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ምንም ግብ ባላስተናገደው ጠንካራው የጊዮርጊስ ተከላካይ መስመር የሚፈተን ይሆናል። በእርግጥ ለመሀል ሜዳው በሚቀርበው የጊዮርጊሶች የተከላካይ መስመር ጀርባ ለአባጅፋር ፈጣን እና ጠንካራ አጥቂዎች የሚሆን ሰፊ ቦታ መኖሩ ከሰሞኑ የአጨራረስ ብቃታቸው ጋር ተደምሮ ጥሩ አጋጣሚን ሊፈጥርላቸው ይችላል። በሌላ በኩል የቅዱስ ጊዮርጊስ የኳስ ምስረታ በጅማ አባጅፋር የመሀል አማካዮች የጊዮርጊስን የአጥቂ አማካዮች ከጨዋታ ውጪ በማድረግም ሆነ በሚኖራቸው ጠቅላላ የመከላከል ተሳትፎ ምክንያት ፈተና እንደሚገጥመው ይታሰባል። ጥሩ ተክለሰውነት ያለው የተከላካይ መስመር ባለቤት የሆኑት ጅማዎች ከኃላ እና ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ የሚጣሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአማራጭነት የሚጠቀምባቸውን አደገኛ ረዣዥም ኳሶችን ለማክሸፍ የሚያችል አቅም አላቸው። እዚህ ጋር ከሳምንታት በፊት የመቐለ ከተማው ያሬድ ከበደ በግንባሩ ግብ ሲያስቆጥር ጅማዎች የሰጡትን ክፍተት ዛሬ የሚደግሙት ከሆነ ግን ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሰል ስህተቶችን በቀላሉ ወደ ግብነት የመቀየራቸው ዕድል የሰፋ ነው።
ምን ተባለ ?
ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
” ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ጥለናል። የግድ ወደ አሸናፊነት መመለስ ይኖርብናል። በርግጥ ተጋጣሚያችን ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ማሸነፉ እየተሻሻለ እና እየጠነከረ እንደመጣ ያመለክታል። ቢሆንም ራሳችን ላይ ትኩረት ማድረግ እንፈልጋለን። ባለፉት ጨዋታዎች የሰራናቸውን ስህተቶች በማረም ለዛውሬ ጨዋታ በመዘጋጀት አሳልፈናል። ”
አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር
” የመጨረሻ ጨዋታችንን ቅዳሜ እንደማድረጋችን እንደሌላው ጊዜ ሰፊ የዝግጅት ጊዜ አልነበረንም። ስለዚህ የተለየ ዝግጅት ባናደርግም የነበረውን ነገር ለማስቀጠል ነው ያሰብነው። በተለይ በስነልቦናው በኩል የአሸናፊነት መንፈሳችን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። የምንገጥመው ትልቅ ቡድን ነው። የስብስብ ጥራቱም ከፍ ያለ ነው ለዚህም ክብር አለን። በጨዋታውም በጥንቃቄ ተጫውተን ውጤት ይዘን ለመውጣት እንሞክራለን ”
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ሮበርት ኦዶንካራ
አብዱልከሪም መሀመድ – ሳላዲን ባርጌቾ – አስቻለው ታመነ – አበባው ቡጣቆ
አብዱልከሪም ኒኪማ – ሙሉአለም መስፍን – ምንተስኖት አዳነ
ተስፋዬ በቀለ – አዳነ ግርማ – አቡበከር ሳኒ
ጅማ አባ ጅፋር (4-4-2)
ዳዊት አሰፋ
ኄኖክ አዱኛ – ቢኒያም ሲራጅ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ
ዮናስ ግርማ – አሚኑ ነስሩ – ይሁን እንዳሻው – ፍራኦል መንግስቱ
ሳምሶን ቆልቻ – ተመስገን ገ/ኪዳን