የጋቶች ፓኖም ቀጣይ ማረፊያ ኢትዮዽያ ውስጥ ከሚገኙ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ሶከር ኢትዮዽያ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።
ባለፈው አመት መገባደጃ ላይ ወደ ሩሲያው አንዚ ማቻካላ ካመራ በኋላ ያለፉትን ስድስት ወራት በዳጌስታኑ ክለብ መቆየት የቻለው ጋቶች በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ከመጫወት በቀር ብዙ የመጫወት እድል አለማግኘቱን ተከትሎ በስምምነት በመለያየት ወደ ሀገሩ መመለሱ ይታወቃል።
በአሁን ሰአት አአ የሚገኘው ጋቶች ክለብ አልባ መሆኑን ተከትሎ የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ግዙፉን አማካይ የግላቸው ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ ። ከነዚህ መካከል አዲስ አዳጊ የሆነው መቐለ ከተማ ሲሆን ጋቶች ፓኖምን ለማስፈረም የተለያዩ ድርድሮች እያደረጉ እንዳሉ እና ከፍተኛ ሒሳብ እነረደቀረበለትም ተነግሯል።
ሌላው የጋቶች ፓኖም ፈላጊ ሆኖ የቀረበው ክለብ ኢትዮዽያን በ2010 በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ የሚወክለውና በዘንድሮ የውድድር አመት በውጤት ቀውስ ውስጥ በመግባቱ የረጅም ዘመን አሰልጣኙን ያሰናበተው ወላይታ ድቻ ነው። ከሶዶው ክለብ አመራሮች ባገኘነው መረጃ መሰረት በተጫዋቾች ዝውውር ሪከርድ በሆነ ወርሀዊ ደሞዝ ጋቶችን የግላቸው ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ዛሬ አመሻሽ ሶከር ኢትዮዽያ ባገኘችው ተጨማሪ መረጃ ደግሞ የኢትዮዽያ ቡና የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እንዲሁም ሌሎች የቦርድ አባላት እና የደጋፊ ማህበሩ አመራሮች እነሰዲሁም ራሱ ጋቶች ፓኖም በተገኘበት ለኢትዮዽያ ቡና ዳግም ሊጫወት በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙርያ ሰፊ ውይይት እና ድርድር ያደረጉ ሲሆን ጋቶች በቡና መለያ ዳግም ለመጫወት ፍላጎት ያለው እንደሆነ ገልፆ ሊከፈለው በሚገባው የገንዘብ መጠን ላይ ሳይስማሙ እንደቀሩ እና የክለቡ አመራሮች ሂሳቡ የተጋነነ መሆኑን ገልፀው ለሌላ ድርድር ቀነ ቀጠሮ ይዘው መለያየታቸውን ሰምተናል።
ጋቶች ፓኖም ቀጣይ ማረፊያ ኢትዮዽያ ቡና ፣ ወላይታ ድቻ ወይስ መቐለ ከተማ?