200 ዕድለኛ የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ወደ ሲሸልስ ይጓዛሉ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ዋንኛ ስፓንሰር የሆነው ሄኒከን በዋሊያ ቢራ ምርቱ 200 ዕድለኛ ደጋፊዎችን ወደ ሲሸልስ ሊወስድ ነው፡፡ ዛሬ ምሽት ቦሌ በሚገኘው በሞሞና ሆቴል ‘መልካም አዲስ ዓመት’ በሚል ስም የተሰየመውን ምርቱን ያስተዋወቀው ሄኒከን በቢራው ቆርኪ ላይ ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን ዕድለኛ ለሚሆኑ 200 ደጋፊዎች ኢትዮጵያ ጋቦን ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሲሸልስ ጋር የምታደረገውን ጨዋታ በቦታው የመከታተል ዕድል ያገኛሉ፡፡ የኳስ ምስል ያለበትን ቆርኪ የሚያገኙ 200 ሰዎች ወደ ሲሸልስ የሚያመሩበት እድል ይገጥማቸዋል፡፡

ሙሉ ወጪያቸው ተችሎላቸው የሚጓዙት እኚህ ደጋፊዎች በሲሸልስ የሁለት ቀናት ቆይታ እንደሚያደርጉ ሶከር ኢትዮጵያ በጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት ችላለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በ56 ሚለዮን ብር ስፓንሰር ያደረገው ሄኒከን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጨምሮ ገልፇል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በፊት በበደሌ ስፓሻል ምርቱ ብሄራዊ ቡድኑን ስፓንሰር ማድረጉ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *