ሐሙስ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረግ አንድ ጨዋታ የሚቀጥል ይሆናል። አዲስ አበባ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበትን ይህን ጨዋታም እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።
አምና ዘጠነኛው ሳምንት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ያለግብ የተለያዩት ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ ሲገናኙ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ8 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም አዳማ ከተማ በ12 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ነው። እስካሁን 14 ግቦች ከመረቡ ላይ ያረፉበት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ጋር በመሆን በርካታ ግብ ያስተናገደ የሊጉ ክለብ ሆኗል። አዳማ ከተማ ደግሞ እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ከፋሲል ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጋር በመሆን 6 ጊዜ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የፈፀመ ክለብ ሆኗል። በዚህ ረገድ የአዳማ ከተማ የሚለየው ከስድስቱ አራቱን የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች መሆኑ ነው። ዛሬ የሚያደርጉት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግን በመሸናነፍ ከተጠናቀቀ ኢትዮ ኤሌክትሪክን እስከ 10ኛ እንዲሁም አዳማ ከተማን እስከ 3ኛ ደረጃ ከፍ የማድረግ አቅም ይኖረዋል።
ሁለቱን የመስመር ተከላካዮቹን ዐወት ገ/ሚካኤል እና ዘካሪያስ ቱጂን በጉዳት ያጣው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዲስ ፈራሚ አጥቂዎቹን ቢኒያም አሰፋ እና ሀይሌ እሸቱም ለጨዋታው እንደማይደርሱ ሰንተናል። በወላይታ ድቻው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጡት ተስፋዬ መላኩን እና በሀይሉ ተሻገር ደግሞ በቅጣት ጨዋታው የሚያልፋቸው ይሆናል። በአዳማ በኩል የተጎዱ ተጨዋቾችን ስንመለከት ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ የራቀውን ሚካኤል ጆርጅን ጨምሮ ሱለይማን መሀመድ እና አዲስ ህንፃን እናገኛለን። ቡልቻ ሹራ ደግሞ ከጉዳቱ ቢያገግምም የመሰለፍ ዕድሉ እርግጥ ያልሆነ ተጨዋች ነው።
በአዲሱ አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ እየተመራ ጨዋታውን እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በደደቢቱ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ተስፋ ባሳየው ስብስቡ ላይ ተመስርቶ በሊጉ ጥሩ ጉዞ ማድረግ ይጀምራል ተብሎ ቢጠበቅም ወደ ሽንፈቱ ተመልሷል። በሊጉ ጥሩ ያልሆነ አጀማመር የነበራቸው እንደ ደደቢት እና ጅማ አባ ጅፋር ያሉ ቡድኖች ከሙከራዎች በኃላ አሸናፊ ቡድኖቻቸውን ሲያገኙ ምን ያህል እንደተጠናከሩ ተመልክተናል። ሆኖም ኤሌክትሪክ ተመሳሳይ መልክ እየያዘ ከነበረው ቡድኑ ውስጥ በጉዳት እና ቅጣት አራት ተጨዋቾችን ማጣቱ ትልቅ ጉዳት ሆኖበታል። አሰልጣኝ አሸናፊ ከአብዛኞቹ ከአዳማ ተጨዋቾች ጋር አብሮ መስራት ተጋጣሚን ከማወቅ አንፃር ለኤሌክትሪክ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ቢታመንም ቡድኑ ከአራቱ ተከላካዮቹ ሶስቱን ማጣቱ ቀድሞውንም ቢሆን ችግር የነበረበትን የኃላ ክፍል ይበልጥ የሚያሳሳው ጉዳይ ነው። አሁን ላይ የአጥቂ አማካይነት ሚና የተሰጠው ካሉሻ አልሀሰንም የቡድኑን ደካማ ጎኖች ለማካካስ አቅም ያለው ተጨዋች ቢሆንም በዛሬው ጨዋታ ከበድ ያለ ፈተና ይጠብቀዋል። የዘንድሮ የኢትዮ ኤሌክትሩክን ግቦች ስናስተውል ተመሳሳይ አካሄድን እንመለከታለን። የኄውም የፊት አጥቂዎች በተለይም ዲዲዬ ለብሪ ከኳስ ንክኪ ጋር ወደ ኃላ በሚሳብባቸው እና የተጋጣሚን የመሀል ተከላካዮች ቦታ በሚያስትባቸው አጋጣሚዎች ካሉሻ አልሀሰን በሚያደርገው ቀጥተኛ ሩጫ ግብ የሚያስቆጥርበት አኳኃን ነው። ይህ አካሄድ ኢስማኤል ሳንጋሪን ከፊቱ ከሚያሰልፈው ጠንካራው የአዳማ የተከላካይ መስመር ጋር ሲገናኝ የሚኖረውን ውጤታማነት ከጨዋታው የምንመለከተው ይሆናል። አዳማ ከተማ ካለበት የማያረካ የሊግ ጉዞ እና ካለባቸው ጫና አንፃር የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገቡት አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ የተሻለ የማጥቃት አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። ቡድኑ ካለው ጥሩ የአማካይ መስመር ስብስብ አንፃር በዛሬው ጨዋታ የመሀል ሜዳዉን ለመቆጣጠር እና የግብ ዕድሎችንም ከኳስ ቁጥጥር የበላይነት በሚመነጩ አጋጣሚዎች ለመፍጠር እንደሚጠቀም ይጠበቃል። በጉዳት ምክንያት ቅርፁን ሲቀያይር የቆየው የፊት መስመር ላይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ግብ ያስቆጠረው ዳዋ ሁቴሳ የቡድኑ ጥቃት ከፊት ስል እንዲሆን የሚኖረው ድርሻ ወሳኝ ነው። በሲዳማው ጨዋታ ከታፈሰ ተስፋዬ ጋር የተጣመረው ዳዋ ላልተረጋጋው እና በአዲስ መልክ ለተዋቀረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የተከላካይ መስመር ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል።