በ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአዲስ አበባ ስታድየም በዕለተ ገና ባስተናገደው የመጀመሪያ ጨዋታ ፋሲል ከተማ በራምኬል ሎክ ብቸኛ ግብ መከላከያን ማሸነፍ ችሏል።
ቡድኖቹ ባለፈው በ9ኛው ሳምንት ከተጠቀሙባቸው የተጫዋቾች ምርጫዎቻቸው ቅያሪዎችን አድርገው ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለግብ የተለያየበት ጨዋታ ላይ የተጠቀመውን የምንይሉ ወንድሙ እና ማራኪ ወርቁ ጥምረት በየተሻ ግዛው እና ሳሙኤል ሳሊሶ በመተካት በተለመደው የ4-4-2 አሰላለፍ ቀርቧል። ቀኝ መስመር ተከላካይ ላይም ሽመልስ ተገኝ ከጉዳት መልስ የሙሉቀን ደሳለኝን ሚና ወስዷል። ድሬደዋ ላይ አይናለም ኃይለን በጉዳት ያጡት ፋሲሎች ደግሞ ሰይድ ሁሴንን የከድር ሀይረዲን የመሀል ተከላካይ አጣማሪ ሲያደርጉ የመስመር አጥቂው አብዱርሀማን ሙባረክን መመለስ ተከትሎ ራምኬል ሎክ የፍሊፕ ዳውዝን የፊት አጥቂነት ሚና ተረክቦ ፋሲል ከተማ በተለመደው የ4-3-3 አሰላለፉ ጨዋታውን ጀምሯል።
የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት በመሞከር ጨዋታውን የጀመሩት መከላከያዎች ከወገብ በላይ ያሉትን የፋሲል ከተማ ተጨዋቾችን በቅብብል አልፈው ለመግባት ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የታዩት የግብ ሙከራዎች በሙሉም መሀል ሜዳ ላይ የሚያስጥሉትን ኳስ በፍጥነት ወደተጋጣሚ ሜዳ ይዘው በመግባት ተጭነው በተጫወቱት ፋሲል ከተማዎች በኩል የተገኙ ነበሩ። በተለይ ወደኃላ እየተሳበ የአማካይ ክፍሉን የቁጥር ብልጫ በማካካስ ለቡድኑ ፈጣን ጥቃት ትልቅ አስተዋፅኦ ሲያደርግ የነበረው በግራ መስመር አጥቂነት ጨዋታውን የጀመረው ኤርሚያስ ኃይሉ 5ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሞክሮት ወደውጪ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። 13ኛው ደቂቃ ላይም አብዱርሀማን ሙባረክ በቀኝ መስመር በኩል ይዞ የገባውን ኳስ ለራምኬል ሎክ አሳልፎለት እሱ ከማግኘቱ በፊት የጦሩ ተከላካዮች አወጡት እንጂ ሌላኛ ሙከራ ለመሆን ከጫፍ ደርሶ ነበር። የመልሶ ማጥቃታቸው ጫና 19ኛው ደቂቃ ላይ ጫፍ የደረሰው ፋሲሎች በአንድ ደቂቃ ልዩነት በአብዱርሀማን ሙባረክ፣ ሔኖክ ገምተሳ እና ዳዊት እስጢፋኖስ አከታትለው ያደረጓቸው ከባድ ሙከራዎች ኢላማቸውን መጠበቅ ባይችሉም የተጋጣሚያቸውን ትኩረት ለመበተን እንደረዳቸው ከአንድ ደቂቃ በኃላ የተቆጠረው የራምኬል ሎክ ጎል ምስክር ነው። ሬምኬል ሎክ ከግቡ አፋፍ ላይ ወደ ጎል የቀየራትን ኳስ ከአብዱርሀማን ጋር ቦታ ተቃያይሮ ወደ ቀኝ የመጣው ኤርሚያስ ኃይሉ በዚሁ አቅጣጫ አጥብቦ በመግባት የሰጠውን ኳስ በመጠቀም ነበር።
ከጎሉ መቆጠር በኃላ የፋሲሎች ጫና የረገበበትን እና መከላከያዎች በተሻለ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉባቸውን 25 ደቂቃዎች ተመልክተናል። 14ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ኪዳኔ ካባከናት የቅርብ ርቀት ሙከራ በኃላ ወደ ፋሲሎች ሳጥን መቅረብ የተሳናቸው መከላከያዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ባደረጉት የተሻለ እንቅስቃሴም ቢሆን 30ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ለየተሻ ግዛው ያሳለፈለት እና ሳማኬ ቀድሞ በመውጣት ያዳነበት ኳስ የተሻለ ሙከራቸው ነበር። ጎል ካስቆጠሩ በኃላ ራምኬልን ለብቻ ከፊት በማድረግ የመስመር አጥቂዎቻቸውን በተወሰነ ሜትሮች ወደ ኃላ ስበው በዳዊት እስጢፋኖስ ግራ እና ቀኝ እንዲጫወቱ ያደረጉት ፋሲሎች ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ የመጡ ይመስላሉ። በዚህ ሁኔታ ሔኖክ ገምተሳ ከተከላካዮች ፊት ከያስር ሙገርዋ ጋር በመጣመሩ የተሻለ ነፃነት ያገኘው የመከላከያው በሀይሉ ግርማ ለቡድኑ የኳስ ቅብብል ማዕከል ሲሆን ታይቷል። ይህ ተጠቃሚ ያደረጋቸው መከላከያዎች የኳስ ቁጥጥራቸው ቢሻሻልም የተወሰደባቸውን የአማካይ ክፍል የቁጥር ብልጫ ማለፍ ተቸግረው ታይተዋል። በመሆኑም ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደፊት በመጣል አጋጣሚዎችን ለማግኘት ሲሞክሩም ነበር። ነገር ግን በሙከራ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች በመጨረሻዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ተቀዛቅዘው ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምርም ሜዳ ላይ የታየው እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው በቀጥታ የቀጠለ ነበር የሚመስለው። በሚመሰርቱት ኳስ መሀል ለመሀል ዕድሎችን መፍጠር የተሳናቸው መከላከያዎች የመስመር አማካዮቻቸውን በመጠቀም ክፍተቶችን ሲፈልጉ ፋሲሎች ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ሜዳ ላይ በመቆየት በመልሶ ማጥቃት ለመሀል ሜዳ ከቀረበው የመከላከያ የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመገኘት ጥረት ሲያደጉ ተስተውለዋል። በዚህ ሂደት 52ኛው ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ ለራምኬል ያሳለፈለት ኳስ ወደ አቤል ከመድረሱ በፊት ተከላካዮች ደርሰው ማውጣት ሲችሉ 63ኛው ደቂቃ ላይ ከእረፍት መልስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፋሲሎች ሳጥን ውስጥ ከደረሰው ጥቃት የመከላከያው የመስመር አማካይ አቤል ከበደ ጠንካራም ባይሆን ሙከራ ማድረግ ችሏል። በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ያለሙከራ የቀጠለው ጨዋታ 72ኛው ደቂቃ ላይ የቀይ ካርድ አስተናግዷል። ፌደራል ዳኛ ቢኒይም ወርቅአገኛው የቀይ ካርዱን የመዘዙት በአብዱርሀማን ሙባረክ ላይ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ተጨዋቹ ከማራኪ ወርቁ ጋር በተፈጠረ ሰጣ ገባ መሀል በግንባር በመማታቱ ነበር።
በቀሩት ደቂቃዎች በዳዊት እስጢፋኖስ ተቀይሮ የገባውን ኤፍሬም አለሙን ከፊት በማድረግ ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት የተንቀሳቀሱት ፋሲሎች ስኬታማ መሆን ችለዋል። ቡድኑ ይሄን ለማድረግ በራሱ ሜዳ ላይ ቆይቶ ከመከላከል ባለፈ ፊት ላይ የመከላከያ የኃላ መስመር ኳስ እንዳይጀምር በኤፍሬም መሪነት አፍኖ ለመያዝ ያደርግ የነበረው ጥረት እጅጉን ጠቅሞታል። ሆኖም በዚህ ሂደት ውስጥ ወደፊት ጠጋ በሚሉት ያስር ሙገርዋ እና ሔኖክ ገምተሳ ጀርባ በፋሲሎች የተከላካይ መስመር ፊት ሰፊ ክፍተትን ሲተው ታይቷል። ነገር ግን ይህን ክፍተት ለመጠቀምም ቢሆን ሲሞክሩ በነበሩት ቀጥተኛ አጨዋወት ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት መከላከያዎች ታህሳስ ወር ከገባ ወዲህ የመጀመርያ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።