በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት መሪው ደደቢት ወደ አርባምንጭ ተጉዞ በግርጌ ላይ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2-1 በማሸነፍ በአስደናቂ አቋሙ ቀጥሏል።
በከፍተኛ ችግሮች ውስጥ የተሞላው አርባምንጭ ከተማ ትላንት በሙሉ የክለቡን አመራሮች እና የአሰልጣኝ አባላቱን በሙሉ ባሰናበተበት ማግስት ያለ አሰልጣኝ በክለቡ ውስጥ ረጅም ጊዜ በቆዩት አምበሉ አማኑኤል ጎበና እና ግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ መሪነት ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
በ36ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ከበደ በአግባቡ ተጠቅሞ ደደቢትን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ጌታነህ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ከአቤል ያለው ያገኘውን ኳስ በማስቆጠር የደደቢትን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል። ጌታነህ ዛሬ ያስቆጠራቸው ጎሎች በ7 ጎሎች በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ሰንጠረዡ አናት ላይ ከአልሀሰን ካሉሻ ጋር እንዲቀመጥ አስችሎታል።
በ82ኛው ደቂቃ ወንድሜነህ ዘሪሁን ከቅጣት ግብ ቢያስቆጥርም አርባምንጭ ከተማን መታደግ ሳይችል።ጨዋታው በደደቢት 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው ዙርያ የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡
አማኑኤል ጎበና (አምበል እና የዛሬውን ጨዋታ የመራ ተጫዋች)
“ሳናስበው ነበር እንድንመራ የተነገረን። እስከ ትላንት አሰልጣኝ በረከት ለጨዋታው ሲያዘጋጀን ነበር። ሳይታሰብ እሱ ተነስቷል። ቢሆንም ከተጫዋቾቹ ጋር ተነጋግረን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በጨዋታው ጥሩ ነበርን። አጥቅተን ተጫውተናል። ያው ግን የገባብን ግብ በኛ ተከላካዮች ስህተት ግብ አስተናግደናል።
“ከፊታችን በርካታ ጨዋታ ስላለን ካለንበት ቀውስ በርግጠኝነት እንወጣለን። በቀጣይ ብዙ እናሻሽላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ”
ንጉሴ ደስታ (ደደቢት)
“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ዳኝነቱ ግን ከአቅማችን በላይ ነበር። 90 ደቂቃ ሙሉ ሲበድለን ነበር። በአቅማችንና በችሎታችን አሸንፈን ወጣን እንጂ አዳልቶ አቻ እንድንወጣ ነበር ያሰበው። እግር ኳሱ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ግራ ያጋባል። ሶስት ነጥብ ይዘን በመውጣታችን ግን ደስ ብሎኛል፡፡ “