​ሪፖርት | የአዲስ ግደይ የጭማሪ ደቂቃ ግብ ለሲዳማ ቡና ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስገኝታለች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች ሲቀጥል ይርጋለም ላይ በሲዳማ ደርቢ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው  ሲዳማ ቡና በአዲስ ግደይ የጭማሪ ደቂቃ ግብ በማሸነፍ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል። የሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በአከባቢው መጠሪያ  ሩዱዋ ወይም የወንድማማቾች ደርቢ እየተባለ ቢጠራም የሁለቱ ክለቦች  ግንኙነት ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባለፈ ከፍተኛ ውጥረት ሲታይበት ይስተዋላል።

ሲዳማ ቡና ቅጣታቸውን አጠናቅቀው የተመለሱት ባዬ ገዛኸኝ እና ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ሲያካትት ጋናዊው የመስመር ተጫዋች አብዱለጢፍ መሀመድን ደግሞ በጉዳት ሳይዝ ገብቷል። ሀዋሳዎች በአንፃሩ ያቡን ዊሊያምን በጉዳት፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በቅጣት ሳይዙ ለመጫወት ተገደዋል።

ጨዋታው በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ደማቅ ህብረ ዝማሬ ታጅቦ በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው ፌደራል ዳኛ ሀብቱ ኪሮስን በህሊና ፀሎት በማሰብ ተጀምሯል። በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ላይ እምብዛም ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ያልታዩ ቢሆንም ሀዋሳዎች በዳዊት ፍቃዱ፣  ደስታ ዮሀንስ እና ፍሬው ሰለሞን ፤ ሲዳማዎች ደግሞ በፍፁም ተፈሪ አማካኝነት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን አድርገዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር በተስተናገደበት በዚህ ጨዋታ 25ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴን ያደረገው ሙሉአለም ረጋሳ ከደስታ ዮሀንስ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ ገብተው ከግብ ጠባቂው መሳይ ጋር ቢገናኝም ኳሷን ወደ ውጭ ሰዷታል። በ29ኛው ደቂቃም ሲዳማ ቡናዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ትርታዬ ደመቀ ሲያሻማ ጋናዊው ማይክል አናን በግንባሩ ገጭቶ በሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ በቀላሉ ተይዞበታል።

በ30ኛው ደቂቃ የሀዋሳ ከተማው ተከላካይ አዲስአለም ተስፋዬ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ለማውጣት ሲሞክር ከማይክል አናን ጋር ተጋጭቶ ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት በማስተናገዱ በአፋጣኝ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል እንዲያመራ ሆኗል። (ተጫዋቹ አሁን ከህክምና ወጥቶ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።) የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቅቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ትርታዬ ደመቀ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ አግኝቶ ያልተጠቀመበት ዕድል የክፍለጊዜው የመጨረሻ ሙከራ ነበር።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሀዋሳ ከተማ በግብ ሙከራም ሆነ በጨዋታ እንቅስቃሴ ወርዶ የታየበት እና ሲዳማ ቡና በመልሶ ማጥቃት የተጫወተበት፤ አጥቂው አዲስ ግደይም ወሳኝ ተጫዋችነቱን ያሳየበት ነበር። በ61ኛው ደቂቃ ፍፁም ተፈሪ የሰጠውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ሞክሮ ወደ ውጭ ሲወጣበት በሀዋሳ ከተማ በኩል በ66ኛው ደቂቃ  ሙሉአለም ረጋሳ በአስደናቂ መልኩ ለዳዊት ፍቃዱ ሰጥቶት ዳዊት ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ጠባቂው ሲመለስ ደስታ ዮሀንስ አግኝቶ ቢመታውም ሙከራው ዒላማውን ሳይጠበቅ ቀርቷል። የፍሬው ሰለሞን እና ታፈሰ ሰለሞን የአጨራረስ ድክመት እንዲሁም ደዊት ፍቃዱ በተደጋጋሚ ከግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ጋር ተገናኝቶ ያገኛቸውን ዕድሎች መጠቀም ያለመቻሉ ሀዋሳ ከተማ የነበረውን የጨዋታ ብልጫ ወደግብ እንዳይለውጥ አድርጎታል። በ83ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ለሙሉአለም ረጋሳ አሳልፎለት ሙሉአለም የሳተው ኳስ በሀዋሳ በኩል የባከነ ሌላ የግብ አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ተጠናቅቆ በተጨመረው ሁለት ደቂቃ ውስጥ የሀዋሳ ከተማው ሄኖክ ድልቢ በሳጥን ውስጥ በአዲስ ግደይ ላይ በሰራው ጥፋት ፌደራል ዳኛ ሚካኤሌ አርአያ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ግደይ ቢመታም ግብ ጠባቂው ሱሆሆ ሜንሳ አድኖበታል። ከፍፁም ቅጣት ምቱ የተመለሰው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቶ የተሰጠውን የማዕዘን ምትም ትርታዬ ደመቀ ሲያሻማ አዲስ ግደይ በግንባሩ ገጭቶ ሲዳማ ቡናን ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስጨበጠች ግብ አስቆጥሯል። እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ በአቻ ውጤት የተጓዘው ጨዋታም በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው አንጋፋው የሀዋሳ ከተማ አማካይ ሙሉአለም ረጋሳ በሜዳው በተገኘው ተመልካች አድናቆት ተችሮታል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

“ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው፤  እነሱ ኳሱን ይዘው ስለሚጫወቱ ይህን እንቅስቃሴ ለመስበር እና እያበላሸን በመስመር ላይ ለመጫወት አቅደን ነበር። በዚህ ሂደትም ቶሎ ቶሎ ወደግብ ብንደርስም ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም ነበር። ረጅም ኳስ መጫወታችን ጠቅሞናል፤ ዛሬ እነሱ በእንቅስቃሴ የተሻሉ ቢሆኑም የኛ ታክቲክ ያን ቶሎ አጥፍተን መጫወት ነበር። እነሱ ኳሱን ሲጫወቱ እኛ ነጥቀን በፍጥነት ለመጫወት ነበር የፈለግነው፤ ያም ተሳክቶልናል።”

ውበቱ አባተ ሀዋሳ ከተማ

“ጥሩ የተንቀሳቀስንበት የደርቢ ጨዋታ ነበር። በሁለታችንም በኩል ጥሩ ነገሮች ነበሩን። ከሜዳችን ውጭ እንደመጫወታችን ከባለፈው የመቐለ ጨዋታ እጅግ የተሻልንበት ነበር፤ ነገር ግን በጨዋታው የተሻልን ብንሆንም ተሸንፈን ወጥተናል። ጨዋታው ተጠናቆ ነበር፤ ፔናሊቲ ተሰጠብን፤ እስኪመታ ተጠብቆም ተመታ። ግብ ጠባቂያችን ኳሱን ካዳነው በኋላ ጨዋታው ማለቅ ነበረበት። ያለቀ ሰአት ነበር። በቀጣይ እናስተካክላለን፤ ዳኝነቱ ላይ ግን ምንም ማለት አልችልም። ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ነው – ማለቴ ሰአቱ ተጠናቆ ነው ያገቡብን። በተለይ አጥቂዎቻችን ተጎድተውብናል። ዊሊያም የለም፤ ዳዊት ከነጉዳቱ ነበር፤ ይህን ግን እንደ ችግር መቁጠር አያስፈልግም።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *