አዲሱ የኤሲ ሚላን ተጫዋች ይናገራል


አዲሱ የኤሲ ሚላን ንብረት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሰኢድ ቪሲን ከዝውውሩ በኋላ በሰጠው የመጀመርያ ቃለምልልስ በጠካራ ስሜት ውስጥ ሆኖ አስተያየት ሰጥቷል

በአዲሱ የፈረንጆች ሚሌንየም ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደው ሰኢድ ኢትዮጵያን ለቆ ወደ ደቡባዊ አውሮፓዊቷ ሀገር ያቀናው በቪሲን ቤተሰብ አማካኝነት በማደጎ ሲወሰድ ገና ህፃን ነበር፡፡ ነገር ግን ሰኢድ ከእግርኳስ ስኬቱ በተጓዳኝ በልጅነቱ የለቀቃትን ሃገር ስለመርዳት ያልማል፡፡

‹‹ በዚህ 2 ቀናት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች ልረዳ አልቻልኩም፡፡ ከዝውወሩ በኋላ ህልሜን መኖር እንደምጀምር ተገንዝቤያለው፡፡ ትልቅ ተጫዋች የመሆን እና ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ህልም፡፡ እኔ ወደ ጣልያን ከመምጣቴ በፊት እኖር የነበረውን አይነት አስቸጋሪ ህይወት የሚያሳልፉ ህፃናትን የመርዳት ህልም…. ››

ሰኢድ ወደ እግርኳሱ አለም ብቅ ያለው በኖሴሪና በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ጨዋታዎችን በማሰናዳት በአካባቢው ታዋቂ የሆኑት ሊዮ ፊያስኮ አማካኝነት ለብሉ ሳይረል ህፃናት ቡድን ተመለመለ፡፡ ይህ ክለብ (ብሉ ሳይረል) ከሌላው ታላቅ ክለብ ኢንተር ሚላን ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ክለብ ነው፡፡ በዚህ ክለብ ድንቅ ብቃት የሚያሳዩ ተጫዋቾችም ኔራዙሪዎቹን የመቀላቀል እድል የሰፋ ነበር፡፡ ሰኢድም ይህ አጋጣሚ እንደሚመጣለት እርግጥ ነበር፡፡

ነገር ግን ባለፈው የፈረንጆች አመት በጣልያን እግርኳስ ፌዴሬሽን በሚዘጋጀው የታዳጊዎች ውድድር ላይ ያሳየውን አቋም ተከትሎ ኤሲ ሚላን ታዳጊው የማዘዋወር ከፍተኛ እድል የነበረውን ኢንተር ሚላንን የመስረቅ ያህል ቀድሞ አስፈርሞታል፡፡

በናፖሊ ፣ ጁቬንቱስ እና ማንቼስተር ሲቲ ጭምር ሲፈለግ የነበረውን ሰኢድ ኢንተር ሚላን በቅድሚያ ለማስፈረም ከ2 አመት በፊት ስምምነት ላይ ቢደርስም ኤሲ ሚላን ቀድሞ ማስፈረሙን ‹‹ ስርቆት ›› ያሉት ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ከ2 አመታት በኋላ በፕሮፌሽናል ደረጃ ኤሲሚላንን መወከል የሚችለው ሰኢድ በእርግጥም ህልሙን መኖር ጀምሯል፡፡ያጋሩ