የአሰልጣኞች ገፅ | የመንግስቱ ወርቁ አሰልጣኝነት ዘመን [ክፍል አንድ]


ሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


መንግስቱ ወርቁ በኢትዮጵያ እግርኳስ የሁሉ ነገር ምሳሌ ናቸው። ታላቅ ተጫዋች ብቻ ሳይሆኑ ምርጥ አሰልጣኝ እና የእግርኳስ ሰው ነበሩ። ከእግርኳስ ተጫዋችነት በ1966 ከተገለሉ በኋላ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ባህር እና ትራንዚት፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ አየር መንገድ፣ ባንኮች ፣ ወንጂ ስኳር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት አሰልጣኝ መንግስቱ ከውጤታማነት ባሻገር ቡድን በመገንባት ፣ ጠንካራ የስራ ባህል በማስረፅ እና አዳዲስ የእግርኳስ አስተሳሰቦች በማስተዋወቅ ረገድ የምንግዜም የኢትዮጵያ የእግርኳስ ባለውለታ ናቸው።

በዛሬው የክፍል አንድ መሰናዷችን ባለፈው ወር 7ኛ የሙት አመታቸው ስለተከበረው መንግስቱ በስራቸው ሰልጥነው ያለፉ እና በአሰልጣኝነትም አብረው የሰሩት አስራት ኃይሌ ፣ ስዩም ከበደ እና ንጉሴ ገብሬ ያላቸውን ትውስታ ይነግሩናል።

አስራት ኃይሌ 

(በ1960ዎቹ በስራቸው የሰለጠኑ)

በቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫዋች አሰልጣኝነት ከሚሰራበት ጊዜ አንስቶ (1966) ነበር የቅርብ ትውውቅ የመሰረትነው፡፡ መንግስቱን እወደውና አከብረው ስለነበር ለእርሱ ምንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል አልሳሳም ነበር፡፡ በ1968 ከመቻል ጋር ስንጫወት አንድ የመቻል ተጫዋች እሱ (መንግስቱ) ወደተቀመጠበት ቦታ ኳሱን ይመታል፡፡ ኳሱ መንግስቱን ባይነካውም እጅግ እልኸኛ ባህሪ ስለነበረው በንዴት ወደ ሜዳ ለመግባት ሲነሳ በጊዜው በሜዳ ውስጥ ስርዓት የሚያስከብሩት የጦር ሰራዊት ወታደሮች መንግስቱን ለመማታት መሮጥ ጀመሩ፡፡ ያኔ እኔ ከመጫወቻ ሜዳው ሊመታው ያለውን ወታደር እጅ በመያዝ መንግስቱን ከጀርባዬ አድርጌ ‹‹ዞር በሉ፡፡ እኔን ገድላችሁ ነው እሱን የምትነኩት›› ብዬ ተከላከልኩት፡፡ ወቅቱ የቀይ ሽብር ጊዜ እንደመሆኑ ህይወትህ በቀላሉ የሚቀጠፍበት ዘመን ነበር፡፡ ሁሉም መሳርያ የታጠቁ በመሆናቸው ሊመቱኝ ይችሉ ነበር፡፡ እኔ ግን ያ አልታየኝም፡፡ ከዛም የሰራዊቱ አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል አበራ አያና ከትሪቡን ወርደው ነገሮችን አረጋገግተው ጨዋታው ቀጠለና እኛ አሸንፈን ዋንጫውን አነሳን፡፡ እንግዲህ ይሄ ሁሉ ያደረኩት ለአሰልጣኜ ያለኝን ፍቅር እና ከበሬታ ለመግለፅ ነበር፡፡ በጊዜው የብሀርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት የሴልስ ፕሮሞተር ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ ደግሞ የመቻል ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ ጨዋታው በተደረገ በማግስቱ ሰኞ ወደ ስራ ገባሁ፡፡ ፈረምኩና ያሉትን ዶክመንቶች ሰብስቤ ወደ ውጪ ለመውጣት ስዘጋጅ ከስራ አስኪያጁ ቢሮ እንደሚፈልጉኝ ተነግሮኝ ቢሯቸው ተገኘሁ፡፡ ‹‹ትላንት የሰራኸው ጥሩ ነበር ?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ‹‹በእኔ እይታ ትክክል ነበርኩ፡፡ አሰልጣኜ እንዳይመታብኝ ተከላከልኩ፡፡ እኔ ወጣት ነኝ የሚደርስብኝን ሁሉ መቋቋም እችላለሁ፡፡ እሱ ግን ከእኔ በእድሜ የገፋ በመሆኑ እሱን ለመከላከል ፈልጌ ነው›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ብትሞትስ ?›› ብለው ጠየቑኝ፡፡ ‹‹ምንም አይደለም፡፡ እንደውም ለእኔ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ይሆንልኛል፡፡ አስራት በስታድየም ውስጥ በጥይት ተመታ የሚለው ለእኔ ክብር ነው፡፡›› ብዬ መለስኩላቸው፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉም ተጫዋቾች ለመንግስቱ ተመሳሳይ የሆነ ፍቅር ነበራቸው፡፡ በዛን ወቅት እኔ ባስጀምረውም ሁሉም ተጫዋቾች ለእርሱ ሊሞቱለት ዝግጁ ነበሩ፡፡

መንግስቱ ይህን ያህል በተጫዋቾቹ እንዲወደድ ዋንኛው ምክንያት የሚመስለኝ ሁሉንም ተጫዋቾች እኩል ማየቱ ነው፡፡ በስራህ ውጤታማ እንድትሆን ከፍተኛ እገዛ ያደርግልሀል፡፡ ከበሬታም ይሰጥሃል፡፡ በልምምድ ወቅትም ይሁን ከልምምድ ውጪ የሚሰጥህ አባታዊ ምክር ትልቅ ደረጃ ደርሰህ ሀገርህን እንድትጠቅም የሚያደርግህ ነው፡፡ ሁሌም የተሻልክ ተጫዋች እንድትሆን ይጥራል፡፡

በተጫዋችነት ልምዱ ያገኛቸውን ነገሮች በሙሉ ያለ ስስት ያካፍላል፡፡ ለሙያው ባለው ክብርም የተለየ ቦታ እንሰጠው ነበር፡፡ በወቅቱ ከእግርኳስ የሚገኘው አናሳ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከስራው አላሸሸውም፡፡ ጥሩ ገንዘብ እና ኑሮ የነበረው ቢሆንም በትንሽ ክፍያ ነበር ያን ሁሉ ስራ የሚሰራው፡፡

በአብዛኛው ባህሪው ከሉቻኖ ቫሳሎ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ውሳኔ ላይ ቆራጥ በመሆን ደግሞ ከሁሉም ይለያል፡፡ ፊት ለፊት ተናጋሪ ነው፡፡ ከጀርባ መሄድን አይመርጥም፡፡ መናገር የሚፈልገውን ነገር እዛው ይነግርሃል፡፡ ተለማምጦ መኖር እና መስራት አይታይበትም፡፡ ትክክለኛ ነው ብሎ ባመነበት መንገድ ይጓዛል፡፡ ካልፈለገህም በምክንያት አስደግፎ አልፈልግህም ይልሃል፡፡ ጣልቃ ገብነትን ደግሞ በፍፁም አይቀበልም፡፡ እንግዲህ እኔም ብዙዎቹ ባህርዎቹን ወስጄ በስራዬ ላይ ተግብሬያቸዋለሁ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሰልጠን ስጀምር የ300 ብር ደሞዝተኛ ነበርኩ፡፡ ሙያ እና እውቀት መገብየት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አምንም ነበር፡፡ ይህ ከነ መንግስቱ ያገኘሁት ነው፡፡ መንግስቱ ከፍተኛ በራስ መተማመን የነበረው ሰው ነው፡፡ በስራውም እምነት ነበረው፡፡ ላመነበት ጉዳይ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ለሚፈጽማቸው ስህተቶች የሚያቀርበው የይቅርታ ጥያቄ ደግሞ እጅግ ያስገርመኛል፡፡

ንጉሴ ገብሬ 

(በ1970ዎቹ የአሰልጣኝ መንግስቱ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች)

መንግስቱ ስብዕናው ከታላላቆቹ ከነ ይድቃቸው ተሰማ አይነት ሰዎች ጋር የሚቀራረብ ነበር፡፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በተለያዩ ሀገራት በምንጓዝበት ጊዜ ስለ እሱ ብዙ ይባል ነበር፡፡ በፈረንሳይ በአንድ መጽሄት ላይ ስለ እሱ የተጻፈ ፅሁፍንም ተመልክቼ ነበር፡፡ መንግስቱ ታላቅ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ከመሆኑ ባለፈ ጎበዝ የአስተዳደር ሰው ነበር፡፡ በአጠቃላይ የብዙ ችሎታዎች ባለቤት ነበር፡፡ በአሰልጣኝነት ስራው በዲሲፕሊን የሚያምን እና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውም ነበር፡፡ እኛን ወደ ስልጠናው አለም ሲያመጣንም በእሱ አስተሳሰብ ቀርፆን ነው፡፡ ስራው ላይ የሚያሳየው ትጋት እና ሙያውን አክባሪ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ በሚኒስቴር ደረጃ የነበሩ አንድ የስራ ኃላፊ ወደ ልምምድ ቦታ መጥተው ያስጠሩታል፡፡ መልእክቱን ላደረሰው ግለሰብ የሰጠው ምላሽ አሁን ድረስ በጣም ያስገርመኛል፡፡ ‹‹ በኋላ ቢሯቸው እመጣለሁ፡፡ እሁን ስራ ላይ ነኝ ብለህ ንገራቸው ›› ነበር ያለው፡፡ ይህ የሚያሳየው ለስራው የነበረውን ዋጋ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ጠንካራ የስራ ፍቅር እና ክብር አይቼ አልፌ ዛሬ የሚታየውን የተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ሁኔታ ስታዘብ እጅጉን አዝናለሁ፡፡

ከመንግስቱ ብዙ ነገሮችን ተምሬ በአሰልጣኝነት ስራዬ ላይም ተጠቅሜበታለሁ፡፡ እኛን በሚያሰጥንበት ወቅት በብዙ ስራዎች ላይ ተሳታፊ ነበር፡፡ በሆቴል ፣ በመኝታ እና አመጋገብ ስርአት ላይ የራሱ የሆኑ መርሆች ነበሩት፡፡ በሱ የልምምድ ፕሮግራም ላይ ዘግይቶ መድረስ ብዙ ዋጋ ያስከፍል ነበር፡፡ አሰልጣኝ ተከባሪ እና ተፈሪ መሆን አለበት፡፡ መፈራት ስልህ እንዲሁ መሸሽን የሚመለከት አይደለም ፤ ተጫዋቾቹን የሚወድ እና ሲያጠፉም የሚገስጽ መሆን አለበት፡፡ መንግስቱ ተጫዋቾቹን በጣም ይወዳቸው እና ያከብራቸው ነበር፡፡ እነሱም ይወዱታል፣ ይፈሩታል እንዲሁም በትልቁ ያከብሩታል፡፡

መንግስቱ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የካፍ ኢንስራክተር ነው፡፡ ይህን ሲያሳካም ከሁሉም የተሻለ ውጤትን አምጥቶ ነው፡፡ አብረውት ይማሩ ከነበሩት አሰልጣኞች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበውም እርሱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ቢን ኮፊ የተባሉ ጋናዊ ኢንስትራክተር በመንግስቱ ቡድን ውስጥ ስለነበርን ተጫዋቾች ከጠየቁን በኋላ ስለ እርሱ የነበራቸውን አድናቆት እና ከበሬታ በሚገርም መልኩ ነበር የመሰከሩት፡፡ መንግስቱ በጀርመን የነበረውንም የአሰልጣኝነት ኮርስ በከፍተኛ ብቃት ነበር የጨረሰው፡፡

በአሰልጣኝነት ዘመኔ እኔ ኦሜድላ እሱ ደግሞ በአየር መንገድ አሰልጣኝነት በተቃራኒነት ተገናኝተናል፡፡ የኔ ቡድን አሸንፎ ለተጫዋቾቼ እንዲህ አልኳቸው፡፡ ‹‹ ስሙ ፤ ዛሬ በተገኘው ድል እኔ መንግስቱን አላሸነፍኩም፡፡ ያሸነፋችሁት እናንተ አየር መንገድን ነው፡፡ የእርሱ ተጫዋቾች ያላቸውን ስላላደረጉ እና እናንተ ደግሞ እኔ ያልኳችሁን በትክክል ስለፈፀማችሁ የተገኘ ድል እንጂ እኔ መንግስቱን በመብለጤ የመጣ አይደለም፡፡ ›› ያኔ እኔ ኦሜድላን ሳሰለጥን ብዙ ምክሮች እና አስተያየቶችን ይሰጠኝ ነበር፡፡

በመንግስቱ ወርቁ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ዘመን በርካታ ተጫዋቾች ለኢንተርናሽናል ጨዋታ በሚሄዱበት ሀገራት በዛው ይጠፉ ነበር፡፡ በምትካቸው የሚመረጡ ተጫዋቾችን በመፈለግ ብሔራዊ ቡድኑን በቶሎ ነበር የሚገነባው፡፡ የ12ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ቡድን ደግሞ ጊኒ ሄደን ተጫውተን ስንመለስ ትራንዚት ያደረግነው አይቮሪኮስት ላይ ነበር፡፡ ከዛም ወደ 7 የሚሆኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ጠፉብን፡፡ የሚገርመው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጠፉት ተጫዋቾች ምትክ ሌሎችን መርጦ እና አዘጋጅቶ ያንን ቡድን አቀረበ፡፡ ያንን ከባድ ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ለአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን በማሳለፍ ረገድ የመንግስቱ ድርሻ የላቀ ነበር፡፡ አንድ ቡድን ውስጥ አይደለም ሰባት ተሳላፊዎች ጠፍተው ይቅርና አንድ ተጫዋች ሲጎድል እንኳን ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ስዩም ከበደ 

(በስራቸው የሰለጠኑ፣ አብረው በአሰልጣኝነት የሰሩ)

ለአሰልጣኝ መንግስቱ ወርቁ በጣም ቅርብ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ የተጫዋችነት ዘመኔን በእርሱ ስር ነው የጀመርኩት፡፡ በኋላም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢ ቡድንን ሳሰለጥን እሱ የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ነበር፡፡ ሁለት አመት የሚሆን ጊዜ ደግሞ አብሬው በምክትልነት አሳልፌያለው፡፡ ስለዚህም ቅርበት ነበረን፡፡ አንድ ጊዜ እምነት ከጣለብህ እስከ መጨረሻው እያነሳሳህ እንድትሻሻል እና እንድታድግ የሚጥር ሰው ነበር፡፡ ያለውን ነገር የሚያካፍል ነው፡፡ እኔ በአሰልጣኝነት ስራዬ እዚህ ለደረስኩበት ደረጃ ከሱ ብዙ ነገሮችን አግኝቻለሁ፡፡

መንግስቱ ትዕግስተኛ ነው፡፡ ይህን ስል ውጤትን ለማሳካት እስከመጨረሻው ድረስ ይጥራል፡፡ ድክመትም ቢኖር ሽንፈትም ቢከሰት ያን ያህል ተስፋ የመቁረጥ ነገር አያሳይም፡፡ በወጣት ተጫዋቾች ላይ ያለው እምነት የተለየ ነበር፡፡

የመንግስቱ ስብዕና ትልቅ ነው እንድል የሚያደርገኝ የጊዜ አጠቃቀሙ ነው፡፡ ጊዜ ማክበር ላይ ያለው አቋም ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለልምምድ 8፡00 ከቀጠረህ እርሱ 7፡30 የመገኘነት ልምድ አለው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በእርሱ ስር ያለፉት ታላላቅ አሰልጣኞች እንደእነ ስዩም አባተ ፣ አስራት ኃይሌ እና ሌሎቹም ምስክር ይሆናሉ፡፡ ትዝ የሚለኝ በ50ዎቹ ክለቦች ወቅት (1975) በትንሿ ስታድየም ማለዳ 12፡00 ለልምምድ ተገኙ ብሎ እሱ 11፡30 ይገኝ ነበር፡ ከተጫዋቾቹ አጥብቆ የሚፈልገው መሰጠትን እና ዲሲፕሊንን ነው፡፡ ተጫዋቾች ራሳቸውን በአግባቡ በስራ እንዲገልፁ እና በሜዳ ውስጥ ያላቸውን ሁሉ ለቡድናቸው እንዲሰጡ ይፈልጋል፡፡ በልምምድ ወቅት ይህን የሚተገብሩ ተጫዋቾችንም እንክብካቤ ያደርግላቸዋል፡፡ እንዲሁም አድናቆትን ይቸራል፡፡

በሀምሳዎቹ ክለቦች ምስረታ ዘመን በሚያሰለጥንበት ወቅት ዝነኛ በነበሩ ተጫዋቾች ዘንድ የሚሰጠው ከበሬታ የተለየ ነበር፡፡ በተጫዋችነት ዘመኑ የገነባው ስም እንዳለ ሆኖ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ሙያው እንዲከበር የሚያደርገው ጥረት ከተጫዋቾቾቹ ከበሬታን እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
የትምህርት አቀባበሉ በጣም ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ በተለያዩ የአሰልጣኝነት ኮርሶች ላይ የሚያመጣው ውጤት ከሰልጣኞቹ ሁሉ የላቀ ነበር፡፡ ለዛም ነው የመጀመርያው ኢትየጵያዊ የካፍ ኢንስትራክተር ለመሆን የበቃው፡፡ ከራሱ ባሻገር ሌሎቹ እውቀት እንዲያገኙ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በጀርመናዊ ኢንስትራክተር በተሰጠ ስልጠና ላይ ተካፍዬ በቀዳሚነት ሳጠናቅቅ የመንግስቱ ድጋፍ ከፍተኛ ነበር፡፡ በወቅቱ የጀርመናዊው ኢንስትራክተር ረዳት በመሆኑ ሰውየውን አሳምኖ የትምህርት ዕድል እንዲመቻችልኝ አድርጓል፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ አገዝ እግርኳስ ላይ ቢሰራ ኖሮ የበለጠ መስራት ይችል ነበር ብዬ አስለሁ፡፡
ቴክኒካል ሰው በመሆኑ በቴክኒክ የላቁ ተጫዋቾችን ይወዳል፡፡ ነገር ግን በቴክኒኩ የበቁ ተጫዋቾች ያላቸውን ችሎታ አውጥተው እንዲጠቀሙ የአካል ብቃት ላይ መስራት ይኖርባቸዋል ብሎ የሚያምን አሰልጣኝ ነው፡፡ በሚሰራቸው ቡድኖች ውስጥ ለምሳሌ በመድን ክለብ ውስጥ እንደ አብዲ ሰኢድ ያሉትን አብዶኛ ተጫዋቾች የሚያበረታታ ነበር፡፡

እድሜው ከገፋ በኋላ የረጅም አመት ልምዱን የማካፈል እና ሌሎች ትልልቅ አሰልጣኞችን የማፍራት ዕድልን አጥተናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ይቀጥላል…

[ በክፍል ሁለት የሌሎች አሰልጣኞች አስተያየት ይቀርባል]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *