የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2009 የውድድር አመትን የኮከቦችን የሽልማት ገንዘብ እስካሁን ከፍሎ አለማጠናቀቁ በተሸላሚዎች በኩል ቅሬታ አስነስቷል።
አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ እና ሁሉንም የኮከቦች የሽልማት ስነ ስርአት በአንድ ሆቴል ለማድረግ እንዲሁም የተሸላሚዎችን የሽልማት ክፍያን መጠን ከፍ ለማድረግ በማሰብ ከናታኔም ጋር በመተባበር ለመጀመርያ ጊዜ በተዘጋጀው የ2009 የውድድር አመት የስድስቱ ሊጎች ኮከብ አሰልጣኝ ፣ ተጫዋቾች ፣ ጎል አስቆጣሪዎች እና የምስጉን ዳኞች ሽልማት መርሀ ግብርን ጥቅምት 12 ቀን 2010 ላይ በካፒታል ሆቴል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት መካሄዱ ይታወቃል። ሆኖም በወቅቱ በሽልማት ስነስርአቱ ላይ የተገለፁ የገንዘብ መጠኖች ለተሸላሚዎች ገቢ እንዳልተደረጉ ታውቋል።
ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ ኮከብ ተሸላሚዎች ለሶከር ኢትዮዽያ እንደተናገሩት እስካሁን የሽልማታቸው ገንዘቡ ዛሬ ነገ እየተባለ ከሁለት ወር በላይ ሳይፈፀም መቅረቱ ቅር እንዳሰኘቸው ገልፀው ፌዴሬሽኑ ሽልማታቸውን እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑን አናግረን በተሰጠን ምላሽ ለመዘግየቱ ምክንያት ያላለቁ ጉዳዮች እንዳሉ እና በወቅቱ በፕሮግራሙ ላይ ቃል የተገቡ ገንዘቦች ገቢ አለመሆናቸው የሽልማት ገንዘቡን እንዳዘገየው ተናግረው ታህሳስ 30 ገንዘቡ እንደሚለቀቅላቸው ያሳወቀ ቢሆንም እስካሁን ሊፈፀም አልቻለም ። ለፕሬዝደንት እና ለስራ አስፈፃሚ ምርጫ ትኩረቱን አድርጎ ሌሎች ስራዎችን ዘንግቷቸዋል እየተባለ የሚወቀሰው ፌዴሬሽኑ የኮከቦች ሽልማትን በሁለት ወር ውስጥ አጠናቆ አለመፈፀሙ አስገራሚ ሆኗል።
የሀዋሳ ከተማ እግርኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ጠሀ መሐመድ በአንድ ስብሰባ ላይ ፌዴሬሽኑ ሽልማቶችን በጨበጣ ማድረጉን ማቆም እና በወቅቱ ከፍሎ ማጠናቀቅ አለበት በማለት ተሰብሳቢውን ፈገግ ማድረጋቸው ይታወሳል።