የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከምስረታው 1943 ጀምሮ ሞክሮት የማያውቀውንና የኢትዮጵያን እግርኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የሚያደርገውን የፊርማ ስምምነት ትላንት በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ተፈራረመ፡፡ የቡድኖችን የእግርኳስ አቀራረብ በዘመናዊ መልኩ ከሚተነትነው R&D GROUP ጋር ለሁለት አመታት አብሮ ለመስራት የተስማማው እግር ኮስ ፌደሬሽኑ አብረው በሚሰሩበት ወቅት የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማሳደግ ብሎም የክለቦቻችንን ደረጃ እና እግርኳሳዊ አቀራረብን ከፍ ለማድረግ ይረዳል በሚል ከድርጅቱ ጋር መስማማቱን አስታውቋል፡፡ በስምምነቱ ወቅት R&D GROUPን በመወከል የድርጅቱ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ራሄል ደጀኔ እንዲሁም እግርኳስ ፌደሬሽኑን በመወከል አቶ ጁነይዲ ባሻ ፊርማቸውን አስቀምጠዋል፡፡ The voice of soccer በሚል መሪ ቃል የተነሳው ይህ አዲስ አሰራር የቡድኖችን ብሎም የተጨዋቾችን የብቃት ደረጃ ቁጥራዊ በሆነ መልኩ ለማስቀመጥና የኢትዮጵያን እግርኳስ ወደ ተሻለ ምእራፍ ከፍ ለማድረግ ከ180 በላይ የ2008 እና 2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን (በክልል የሚደረጉ ጨዋታዎችን ጨምሮ) ፣ 37 የብሄራዊ ቡድኑን ጨዋታዎች እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች የሚሳተፉበት የሌሎች ሀገራት ሊጎችን በአጠቃላይ 400 የሚሆኑ ጨዋታዎችን አናላይስ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

R&D GROUP 105,850 ዩሮ በጀት በሁለት አመታት ውስጥ መበጀቱንና ስራውን ለመስራት ይረዳው ዘንድ ገንዘቡን ከስፖንሰር ለማግኘት እንዳሰበም ገልፀዋል፡፡ ምንአልባት ከስፖንሰር የተገኘው ገንዘብ ከ105,850 ዮሮ የሚበልጥ ከሆነ ድርጅቱ ያገኘውን ገቢ ሃምሳ ሃምሳ ከፌደሬሽኑ ጋር እንደሚካፈልም ገልፀዋል፡፡ ምን አልባት ይህ የታሰበው ገንዘብ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከስፖንሰሮች ማግኘት ባይቻል ገንዘቡን ማን ይሸፍናል የሚል ጥያቄ ከሶከር ኢትዮጵያ ቢነሳም የ R&D GROUP ማኔጅንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ራሄል ደጀኔ በእርግጠኝነት ገንዘቡ እንደሚሞላና አሁን ራሱ ከአንዳንድ ድርጅቶች ጋር ድርድር እንደጀመሩም አስታውቀዋል፡፡ ይህ ድርጅት ከእግርኳስ ፌደሬሽኑ ጋር ስራውን ለመስራት ለአራት አመታት ያክል በድርድር ላይ ቆይተው በመጨረሻም ዘንድሮ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

እንደዚህ አይነት ዘመናዊ አሰራር ለሀገራችን እግርኳስ መነቃቃት አይነተኛ ሚና ሲኖረው የተጨዋቾች የምልመላ ሂደትን ለማቅለልና የፕሪምየር ሊጉን ተጨዋቾች ቁጥራዊ መረጃን በቀላሉ ለማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን እግርኳሳችንን ዘመናዊ ለማድረግና ሊጋችንንም ለማስተዋወቅ ብሎም ተጨዋቾቻችን ከሀገር ውጭ የመጫወት እድልንም የሚያመቻች ይሆናል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በፊት የሆላንድን ሊጎች (ኤር ዲቪዝየ) በመተንተን የሚታወቅ ድርጅት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ደግሞ የአሜሪካን ሊግ (ሜጀር ሊግ ሶከር) ለመተንተን ድርድር እያደረጉ መሆኑም ተናግረዋል፡፡

ይህን ዘመናዊ አሰራር በመጪው አመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመር ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ የገለፁት R&D GROUP ስራውን የሚሰሩት ORTEC ከተባለ የውጭ ድርጅት ጋር በመተባበር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ያጋሩ