የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን ከተጀመረ ሁለት ወራትን አስቆጥሯል። ሶከር ኢትዮጵያም በወሩ (ታህሳስ) በተደረጉ 5 ጨዋታዎች የላቀ ብቃት ያሳየ ተጫዋች ፣ ውጤታማ አሰልጣኝ እና የወሩ ምርጥ 11 ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጣለች።
የወሩ ኮከብ ተጫዋች – ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)
ደደቢት በተቀዛቀዘበት የመጀመሪያው ወር ጌታነህም ከግብ አስቆጣሪዎች ተርታ ስሙ ጠፍቶ ቆይቷል። ሆኖም በታህሳስ ወር ክለቡ አምስቱን ጨዋታዎች ሲያሸንፍ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር አሁንም የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች መሆኑን አሳይቷል። በተለይም ኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ላይ ያስቆጠራቸው ግቦች ደደቢት ስድስት ነጥብ እንዲያገኝ በቀጥታ ያገዙ ነበሩ።
ጌታነህ ዘንድሮ በአስገራሚ ሁኔታ የአጨዋወት ለውጥ በማምጣትም ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ግብ የሆኑ ኳሶችን እስከማቀበል የደረሰ ሰፊ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። ይህም እንደ አቤል ያለው አይነት ወጣት አጥቂ ከጎኑ እንዲፈጠር ምክንያትም እየሆነ ነው።
የወሩ ኮከብ አሰልጣኝ- አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ (ደደቢት)
በተጨዋቾች ስብስቡ ጥያቄ ይነሳበት የነበረው ደደቢትን በአመቱ መጀመሪያ የተረከቡት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ፈታኝ የውድድር ዘመን ሊገጥማቸው እንደሚችል የብዙሀን ግምት ነበር። ሊጉ በጀመረበት ወርም ቡድኑ ከአምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፉ ይህን ግምት እውነት ሊያደርገው ተቃርቦም ነበር። ሆኖም የታህሳስ ወር ደደቢት ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ያሸነፈበት እና እስራ ሶስት ግቦችን ያስቆጠረበት ወር መሆኑን ተከትሎ በቅድሚያ የተሰጠውን ግምት ፉርሽ ማድረግ ችሏል። በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ በተለይ አማካይ መስመር ላይ በሊጉ ባልተለመደ መልኩ ሰፊ ልምድ ካላቸው ተጨዋቾች ይልቅ ነጥረው ለወጡ ወጣት ተጨዋቾች ተከታታይ ዕድል በመስጠት እና እያየናቸው ተሻሽለው ለቡድኑ መዋቅር ወሳኝ እስኪሆኑ ድረስ በመታገስ አሁን ላሉበት ደረጃ እንዲበቁ የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ውሳኔ ሰጪነት አስፈላጊ ነበር። በዚህም የአብስራ ተስፋዬ ፣ አቤል እንዳለ ፣ አለምአንተ ካሳ እና አቤል ያለው በግላቸው ያሳዩትን ዕድገት ማንሳት በቂ ነው። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም እንደተጋጣሚው ሁኔታ ቡድኑ ላይ መጠነኛ ለውጦችን በማድረግ ትልቁን ሀላፊነት የተወጡት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ደደቢት ሜዳው ላይም ሆነ ከሜዳው ውጪ በተጋጣሚዎች ብልጫ በሚወሰድበት አጋጣሚዎች እንኳን ሳይቀር ጨዋታዎችን በማሸነፍ የሻምፒዮንነት ባህሪ እንዲላበስ አስችለውታል። ከውጤት ባለፈም አሰልጣኙ ባለፉት ጨዋታዎች ባስመዘገቧቸው እነዚህ ስኬቶች ምክንያት የወሩ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው ሲመረጡ ያለምንም አከራካሪ ሀሳብ ነው።
አሰልጣኝ ንጉሴ ከዚህ ቀደም በ2007 የሶከር ኢትዮጵያ የጥቅምት ወር ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል።
የወሩ ምርጥ 11 (4-2-3-1)
ግብ ጠባቂ
ክሌመንት አዞንቶ (ደደቢት)
ደደቢት በታህሳስ ወር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ሲያሸንፍ ጉዞው ቀላል ነበር ማለት አይቻልም። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ቡድኑ በተጋጣሚ የተበለጠባቸው እና በርካታ የግብ ሙከራዎችን ያስተናገደባቸው የጨዋታ ደቂቃዎች ነበሩ። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በተደረገው ጨዋታ ብቻ ሰባት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ያዳነው ክሌመንት አዞንቶም በዚህ ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ሚናን ተወጥቷል። ግብ ጠባቂው ያለቀላቸው የሚባሉ ሙከራዎችን በሚያስገርም ቅልጥፍና በማዳንም ቡድኑ በተበለጠባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ግብ የሚቆጠርበት አይነት እንዳይሆን አድርጓል።
በወሩ ጥሩ አቋም ያሳዩ ሌሎች ግብ ጠባቂዎች ሮበርት ኦዶንካራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ሚኬል ሳማኬ (ፋሲል ከተማ)
የተከላካይ መስመር
ደስታ ደሙ (ደደቢት)
በቡድኑ የሳሳ የተጨዋቾች ስብስብን ተከትሎ ከመስመር ወደ መሀል ተከላካይነት ለውጥ ያደረገው ደስታ ከከድር ኩሊባሊ ጋር ጥሩ ጥምረት በማሳየት ለደደቢት አስገራሚ ጉዞ ተጠቃሽ ተጨዋች ለመሆን በቅቷል። ደደቢት አመቱን ሲጀምር የኩሊባሊ አጣማሪ የነበረው ኩዌኪ አንዶህ ከተጎዳ በኃላ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መግባት የቻለው ደስታ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ኩዌኪ ከጉዳት ቢመለስም ቦታውን ማስከበር ችሏል። በመስመር ተከላካይነት ቦታ ላይ ብዙ አማራጮች አለመኖራቸውን ተከትሎ ደስታን በዚሁ ቦታ ላይ የመረጥነው ሲሆን ተጨዋቹ ከመከላከል ብቃቱ ባሻገር በወሩ አንድ ግብ ማስቆጠር መቻሉም የሚታወስ ነው።
አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ወር ምንም ግብ ያላስተናገደ ክለብ ነው። በዛው ልክ ደግሞ አስጨናቂ የሚባሉ የግብ ሙከራዎችም አልተደረጉበትም። ይህ እንዲሆን የመሀል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ እገዛ ከፍ ያለ ነበር። በብዛት ከሳላዲን ባርጌቾ እንዲሁም ደሞ ከደጉ ደበበ ጋር በመጣመር የተጋጣሚ አጥቂዎች ከባድ ሙከራዎችን እንዳያደርጉ በመግታት ሮበርት ኦድንካራ ጨዋታዎች ቀለውት እንዲወጡ የአስቻለው የመከላከል ብቃት እጅግ ወሳኝ ነበር። አስቻለው ከጉዳት ነፃ የሆነ ወር በማሳለፍ እና ጥሩ የሆነ የአካል ብቃት ደረጃ ላይ በመገኘትም ጭምር ግብ የማስቆጠር ችግር የነበረበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፍ ባልቻለባቸው ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሏል።
ካድር ኩሊባሊ (ደደቢት)
በሊጉ በወጥነት ከሳምንት ሳምንት መዝለቅ ብርቅ የሆነ ይመስላል። በህዳር ወር ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቶ የነበረው ከድር ኩሊባሊ ግን በዚህኛውም ወር የሚያስመርጠውን ብቃት ከማሳየት ወደ ኃላ አላለም። ንቁ የሆነው የመሀል ተከላካይ የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀድሞ በማንበብ እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ፈጥኖ እርምጃ በመውሰድ ደደቢትን ከብዙ አደጋዎች ታድጓል። ኩሊባሊ ቀድሞ ይታማበት የነበረው የሀይል አጠቃቀሙም መሻሻልን አሳይቷል። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው በአስር ሳምንታት ውስጥ ሶስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ብቻ መመልከቱ ነው።
አበባው ቡታቆ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
አበባው ቡታቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኃላ ወደ ድል ሲመለስ ጅማ አባ ጅፋር ላይ ሁለት የቅጣት ምት ጎሎችን ማስቆጠሩ ይታወሳል። ከዚህ ውጪ ተጨዋቹ በማጥቃት ተሳትፎው ቡድኑ በሚፈልገው መጠን ተሳትፎ ሲያደርግ ባይታይም ግብ ባላስተናገደው የፈረሰኝቹ የኃላ መስመር ላይ በቋሚነት ሲሰለፍ ከመቆየት ባለፈም ከመስመር የሚነሱ ጥቃቶችን በመከላከል ከፍ ያለ አስተዋፅዖ አበርክቷል።
በወሩ ጥሩ አቋም ያሳዩ ሌሎች ተከላካዮች ከድር ኸይረዲን (ፋሲል ከተማ) ፣ ምኞት ደበበ (አዳማ ከተማ) ፣ ሰለሞን ሀብቴ (ደደቢት)
አማካይ መስመር
ሙሉአለም መስፍን (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ሙሉአለም መስፍን በሊጉ ከሚገኙ የተከላካይ አማካዮች በአንፃራዊነት ጥሩ የሚባል ወርን አሳልፏል። ሙሉአለም በሁሉም የቅዱስ ጊዮርጊስ የወሩ ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ የቻለ ሲሆን ቡድኑ የሚተገብረው አጨዋወት መነሻ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግልም ቆይቷል። ከተከላካዮች ፊት እንደሚሰለፍ ተጨዋች ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ መላበስ የቀድሞው የሲዳማ ቡና ተጨዋች የራሱን አስተዋፅዖ እያደረገ ነው። የአካል ብቃቱ የአየር ላይ ኳሶችን ለመመከት ያስቻለው ሲሆን የተጋጣሚ የጨዋታ አቀጣጣይ ተጨዋቾችም በጨዋታው የሚኖራቸው ተፅዕኖ የጎላ እንዳይሆን ወሳኝ ሚና ሲጫወት
ይሁን እንዳሻው (ጅማ አባ ጅፋር)
ጅማ አባጅፋር ሲያስመዘግብ ከነበረው ደካማ ውጤት ወጥቶ በፍጥነት ደረጃውን ባሻሻለበት በዚህ ወር ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ተጨዋቾች መሀከል አንዱ ይሁን እንዳሻው ነው። አማካይ ክፍል ላይ ከአሚኑ ነስሩ ጋር የፈጠረው ጥምረትም በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ዋነኛ ተሳታፊ ለሆኑት የመስመር አማካዮች ዮናስ ገረመው እና ሔኖክ ኢሳያስ በሚሰጠው ነፃነት ለተቆጠሩት በርካታ ግቦች በተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ እንዲኖረው አድርጎታል። ይሁን በዚሁ አጨዋወቱ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ጭምርም ተጋጣሚ መሀል ለመሀል በሚሰነዝራቸው ጥቃቶች በቀላሉ እንዳይሰበር በማድረጉ በኩል ዋና ተዋናይ ሆኖ ወሩን አገባዷል።
አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)
በሲዳማ ቡና ከአምናው ፍፁም መልኩን የቀየረ ደካማ የውድድር አመት ውስጥ በጥሩ ጎን የሚነሱ ጥቂት ነጥቦች ብቻ ናቸው ያሉት። ከእነዚህ ውስጥ አዲስ ግደይ ዋነኛው ነው። በቡድኑ የተሻለ አስፈሪነት ያለው ከመስመር የሚነሳ ጥቃት ላይ ከአብዱለጢፍ መሀመድ ጋር በሁለቱም አቅጣጫዎች ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ጥቃት እንዲሰነዝር የአዲስ ሚና ተጠቃሽ ነበር። ተጨዋቹ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ላይ ያለውን ፍጥነት በመጠቀም ከመስመር ይዟቸው የሚገቡ ኳሶች ቡድኑ ግብ እንዲያገኝ ምክንያት ሲሆኑ ይታያል። አዲስ በወሩ የመጨረሻ ጨዋታ በወንድማማቾች ደርቢ ላይ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ለረዥም ሳምንታት ከድል ርቆ የቆየውን ሲዳማ ቡናን በወሩ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ እንዲሆን ያስቻለች ነበረች።
ካሉሻ አልሀሰን (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)
ከጌታነህ ከበደ ጋር በመሆን በሰባት ግቦች የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ የሚገኘው ጋናዊው አማካይ እንደ ህዳር ወር ሁሉ በታህሳስም ድንቅ በሚባል አቋሙ ገፍቶበታል። ምናልባትም ተጫዋቹ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለሚገኝ ክለብ እየተጫወተ ቢሆን ኖሮ ከዚህም በላይ በተሞካሸ ነበር። ሆኖም እንደተለመደው ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ በሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ውስጥ መገኘቱ ክለቡ ከዚህም በባሰ ሁኔታ ላይ እንዳይገኝ ድጋፍ አድርጎለታል። ካሉሻ ጥሩ ከሚባለው የመከላከል ተሳትፎው ባለፈ በእንቅስቃሴ ከፊት ለፊቱ የሚጫወቱ አጥቂዎች በሚሰጡት ክፍተት ላይ እየተገኘ ግቦችን የማስቆጠር ብቃቱ ትኩረትን የሚስብ ነው። በዚህ አኳኃን በኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ላይ ያስቆጠራቸው ግቦችም ተጨዋቹ ያለውን ክፍተትን ፈልጎ የማግኘት ክህሎት ከማመላከታቸው ባሻገር የአጨራረስ ብቃቱንም ያሳዩ ነበሩ።
አቤል ያለው (ደደቢት)
በታህሳስ ወር አምስት ግቦችን ያስቆጠረው አቤል ያለው በወሩ መነጋገሪያ ሆነው ከቆዩ ወጣት ተጨዋቾች መሀል ዋነኛው ነው። አቤል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ተሳትፎ በኃላ ወደ ክለቡ ሲመለስ የግብ ማስቆጠር ብቃቱ በእጅጉ አድጓል። ከዛ በፊት የነበረው በእንቅስቃሴ ተከላካዮችን የማስጨነቅ ብቃቱ እንዲሁም አዕምሯዊ እና አካላዊ ፍጥነቱን በመጠቀም ለሌሎች የቡድን ጓደኞቹ ክፍት ቦታ የመስጠት አጨዋወቱም አብሮት ቀጥሏል። በዚህም በተለይ ቡድኑ ወደ 4-3-3 አሰላለፍ ከመጣ አንስቶ በመስመር አጥቂነት ድንቅ የሚባል ጊዜን እያሳለፈ አምስት ግቦችን ከመረብ ማገናኘት ችሏል።
በወሩ ጥሩ አቋም ያሳዩ ሌሎች አማካዮች ሔኖክ ኢሳያስ (ጅማ አባ ጅፋር) ፣ ዮናስ ገረመው (ጅማ አባ ጅፋር) ፣ አቡበከር ሳኒ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ (ፋሲል ከተማ) ፣ ያስር ሙገርዋ (ፋሲል ከተማ) ፣ የአብስራ ተስፋዬ (ደደቢት) ፣ አቤል እንዳለ (ደደቢት)
የአጥቂ መስመር
ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)
በዚህ ወር በርካታ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች በየክለባቸው ጥሩ ጊዜን አሳልፈዋል። እንደ ጌታነህ በወጥነት ደምቆ የወጣ ተጨዋች አለ ማለት ግን አይቻልም። ቡድኑ በተከታታይ 5 ጨዋታዎች ሲያሸንፍ 6 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል።
በወሩ ጥሩ አቋም ያሳዩ ሌሎች አጥቂዎች ዳዋ ሁቴሳ (አዳማ ከተማ) ፣ ምንይሉ ወንድሙ (መከላከያ) ፣ ኦኪኪ አፎላቢ (ጅማ አባ ጅፋር)