አርባምንጭ ከተማ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከተቀላቀለበት 2004 ወዲህ አስከፊውን አጀማመር ዘንድሮ አድርጓል። ከ10 ሳምንታት በኋላም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ክለቡ በተለይ ያለፉትን ሶስት አመታት የፋይናንስ እና አስተዳደራዊ ችግሮች በተደጋጋሚ እየተከሰተበት የመዝለቁ ውጤት ዘንድሮ እየታየ ይመስላል። በተጫዋቾች እና በዙርያው የሚገኙ ግለሰቦች ላይ ቅሬታን ከማሳደሩ በተጨማሪም በደጋፊው ዘንድ የማያቋርጥ ተቃውሞ እያስተናገደ ይገኛል።
የበርካታ ኮከቦች መፍለቂያ የሆነው አርባምንጭ ከተማ በክረምቱ ባልተለመደ ሁኔታ በአካባቢው ከሚገኙ ውጪ በርካታ ተጫዋቾችን ከሊጉ ክለቦች እና ከውጪ ሀገራት በማስፈረም ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በአሰልጣኝነት በመሾም የውድድር አመቱን ቢጀምርም ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ ዋና አሰልጣኙን ጨምሮ የአሰልጣኝ ቡድኑን አባላት እና የቴክኒክ ኮሚቴውን እንዲሁም ስራ አስኪያጁን በማሰናበት በአዳዲስ ሰዎች ተክቷል።
በክለቡ ወቅታዊ ለውጦች እና ቀጣይ እቅዶች ዙርያ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ እና የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አርባምንጭ ላለፉት ሶስት አመታት በተደጋጋሚ ለተጨዋቾች ደሞዝ የመክፈል ችግሮች እና የፋይናንስ አቅም መዳከም የሚታይበት ክለብ ሆኗል…
ከዚህ ቀደም በእርግጥ ክለቡ ላይ እነዚህ ችግሮች ይታዩ ነበር። የፋይናንስ እጥረት እየተፈታተነን ለተጫዋቾች ደሞዝ ለመክፈል ስንቸገር ቆይተናል። ዘንድሮ ግን በየወሩ ነው የሚከፈለው። ለተጫዋቾቹ ደሞዝ ያልተከፈለበት ጊዜም አልነበረም። በዚህ አመት እስከ አሁን በሙሉ ተከፍሏል፡፡ አልተከፈለም የሚለው ከዕውነት የራቀ ነው።
ክለቡ የሚታወቀው ተጨዋቾች ከታች በማሳደግ እና በትንሽ ወጪ ተጨዋቾችን በማምጣት ነበር። አሁን ግን ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ወደ ውጪ ተጨዋቾች በማዞር ቀድሞ ከነበረበት ባህሉ ሊወጣ የቻለበት ሁኔታን እንዴት ያዩታል?
ማንም እንደሚያውቀው የአርባምንጭ ከተማ በሀገሪቱ ካሉ የእግር ኳስ ዕምቅ አቅም ካላቸው አካባቢዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ለአርባምንጭ ክለብ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ላሉ ሌሎች የእግር ኳስ ክለቦች አስተዋጽኦ ያደረገ ነው። ነገር ግን አሁን ከክለቡ ውጤት ቀውስ ጋር ተያይዞ ተጫዋቾችን በሚገባ የማስተዳደር እና የአሰልጣኞቹ እንዲሁም ቴክኒክ ኮሚቴ አካባቢም የሚታዩ ችግሮች አሉ። በአጠቃላይ ደግሞ በተጫዋቾች በኩል ራሳቸውን ያለመጠበቅ ችግሮች ነበሩ። በአጭር ጊዜም ይህን ለማስተካከል ከተለያዩ ቦታዎች ተጫዋቾች ማስፈረም ስለነበረብን ነው ከሌሎች ክለቦች እና ከሀገር ውጭ ያስፈረምነው። በቀጣይነት እና በዘላቂነት ግን በፕሮጀክት እና በቢ ቡድን ላይ ሰርተን ለክለቡም ሆነ ለሀገሪቱ ሌሎች ክለቦች ለማበርከት አቅጣጫ አስቀምጠን እየሰራን እንገኛለን። በአጭር ጊዜ እቅድ ግን በቀጣዩ የዝውውር መስኮት አንድ ሶስት ተጫዋቾችን ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ለማስፈረም ተዘጋጅተናል፡፡
ያለፉትን ሶስት አመታት በውስጥ አመራሮች ፣ በተጫዋቾች እና በአሰልጣኞች ላይ ተደራራቢ ችግሮች በክለቡ ውስጥ ነበሩ። ሆኖም ለረጅም ጊዜ ሳይፈቱ እስከ አሁን የቆዩበት ሁኔታ ነበር። እስካሁን ለምን ዝምታን መረጣቹሁ ? እርምጃዎችን በጊዜው ያልወሰዳችሁት ለምንድ ነው ?
እርምጃ አወሳሰድ ላይ ፈጣን እርምጃ ይወስዳሉ ከሚባሉ ክለቦች መሀከል አርባምንጭ ከተማ ቀዳሚው ነው። ለአብነት በተለያዩ ጊዜ የመጡ አሰልጣኞች ነበሩ። ውጤት ባለማምጣታቸው እርምጃ ወስደናል። በክለቡ ቦርድ እና ቴክኒክ ኮሚቴ ጋርም በተያያዘ እርምጃዎችን ወስደናል። ከተጫዋቾችም አንፃር ቶሎ ቶሎ እየገመገምን እርምጃ በመውሰድ በኩል ብዙ ሰርተናል። ችግሮችን በማስታመም እርምጃ ሳይወሰድ የቀረበት ጊዜ የለም። ግን ክለቡ በዘላቂነት ራሱን ችሎ በሁለት እግር ቆሞ ህዝባዊ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር በርካታ ችግሮች ነበሩ። ሰስራዎችን በወጥነት ያለመስራት እና ችግሮችን ለመፍታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ህዝባዊ መሠረት እንዲይዝ ከማድረግ አኳያ በርካታ ችግሮች ነበሩ። አሁን ግን ደጋፊ ማህበር አደራጅተን ህብረተሰቡ የክለቡ ባለቤት እንዲሆን ባለቤት ብቻ መሆን ሲባል ሜዳ ገብቶ ቲፎዞ መሆን ብቻ ሳይሆን በተለያየ አግባብ ክለቡን መደገፍ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ እና ክለቡ የተሻለ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል እየተካሄደ ያለ ስራ አለ። ዋናው ጉዳይ ግን ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት ራሱን ችሎ እንዲቆም በርካታ ስራዎች እየሰራን እንገኛለን።
ክለቡ አሁን ካለው የውጤት ቀውስ አንፃር ቶሎ ይሻሻላል ብላችሁ ታስባላችሁ? እንደበፊቱ ክለቡን የተረጋጋ ለማድረግስ ምን ታስቧል ?
የመጀመሪያው ዙር ሊያልቅ አምስት ያህል ጨዋታዎች ነው የሚቀሩት። እነዚህ አምስት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤትን በማምጣት ከወራጅ ቀጠናው ወጥተን በቀጣይ በሁለተኛው ዙር ላይ ደግሞ በተሻለ ሁኔታ ለመቅረብ ተጫዋቾችን ወደ ክለባችን የምናመጣበት ሂደት ይኖራል። ይህን አድርገን ለሁለተኛ ዙር ተፎካካሪ እንሆናለን። እስከዛው ድረስ ግን ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ በቦርድ ደረጃ ተነጋግረን ስልቶችን በመቀየስ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ነው የአጭር ጊዜ ዕቅዳችን።
ሰሞኑን በርካታ ስብሰባዎችን አድርጋችኋል። የተለያዩም ውሳኔዎችንም አሳልፋችኃል። አሰልጣኝ ፣ ቡድን መሪ ፣ ስራ-አስኪያጅ እና ቴክኒክ ኮሚቴ በሙሉ በአዲስ መልክ ለውጣችኋል። የአሰልጣኝ ሹመቱ ምክንያታዊነትስ ምን ያህል ነው?
ሰሞኑን ያደረግነው ስብሰባን ተከትሎ አዲስ አሰልጣኝ ሾመናል። በተለይ ትላንት ከአዲሱ አሰልጣኝ ጋርም ሰፊ ድርድር አድርገን ጨርሰናል። የሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ እዮብ ማለን ቀጥረናል። እዮብን በምናይበት ጊዜ ከአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ጀምሮ በተጨዋችነትም ሆነ በተለያዩ መንገዶች እናውቀዋለን። አርባምንጭ ከተማንም ቢሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ በሚገባበት ጊዜ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህን ተከትሎ የአርባምንጭ ነባራዊ ሁኔታን ስለሚያውቅ እና ቡድኑን ቢይዝ ወደተሻለ ደረጃ ሊያመጣው ይችላል ብለን ስላሰብን ተገምግሞ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል፡፡ በምክትል በኩልም የጋሞ ጨንቻ አሰልጣኝ ማቲያስ ለማን አስቀምጠናል። እሱም በጣም ፍላጎት ያለው እና ክለቡንም ይዞ ጥሩ ደረጃ ላይ ያደረሰ አሰልጣኝ ነው። ከሙያ አንፃርም ላይሰንስ አለው። ቴክኒክ ኮሚቴው ለቦርዱ ክፍተቶችን እየገመገመ እንዲያቀርብ ነበር ሀሳባችን። ከዛ ወጣ ያሉ ተግባሮችኝ ስላየን አንስተነዋል። ሌላ አጀንዳ ስለነበራቸው ተገቢ አይደለም ብለን አንስተናቸዋል። ስራ-አስኪያጁን እና ቡድን መሪውንም በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ መልክ አዋቅረናል። በቴክኒክ በኩል ክለቡ ቴክኒክ ኮሚቴ እንጂ ቴክኒካል ዳይሬክተር የለውም። በኮሚቴ ነው አሁንም የሚቀጥለው። በዚህ አይነት ችግር አለባቸው ያልናቸውን አሰናብተን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ነው ያቀድነው፡፡