‹‹ በህክምና ስህተት ተጫዋቾች ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ››

 

(ዜናው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተላከ ነው)

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነትና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በመካሄድ ላይ በሚገኘው የ24ቱ የብሔራዊ ሊግ ክለቦች የማጠቃለያ ውድድር በህክምና ስህተት የተጨዋቾች ህይወት እንዳይጠፋና ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የተወዳዳሪ ክለቦች ወጌሻዎች፣ የድሬደዋ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የስፖርት ህክምና ሙያተኞችን ባሳተፈውና ሰሞኑን በድሬደዋ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስፖርት ሕክምና ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነስረዲን አቡዱራሂም እንዳስገነዘቡት የድሬደዋው የብሔራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ጠንካራ ፋክክር የሚታይበት በመሆኑ የህክምና ሙያተኞች ለውድድሩ ዝግጁ በሆኑት ሐኪሞችና መሳሪያዎች በመገልገል ተጨዋቾችን ከአስከፊ ጉዳት መታደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የዘንድሮው የብሔራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር በርካታ ክለቦችን ያሳተፈ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የድሬደዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከከተማው የጤና ቢሮ ጋር በመተባበር አንድ ሀኪምና ስድስት ነርሶች እና ሁለት አምቡላንሶችን ጨምሮ ለውድድሩ ዝግጁ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ድንገተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት አልጋዎች በሆስፒታል ለስፖርተኞች ለ24 ሰዓት መዘጋጀታቸውን የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኘሬዚዳንት አቶ መኮንን ደስታ አስታውቀዋል፡፡ ሰሞኑን በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄዱት የብሔራዊ ሊግ የማጠቃለያ ጨዋታዎች የክለብ ወጌሻዎች ለሁሉም አይነት ጉዳት ውሃ ብቻ በመያዝ ወደ ሜዳ ሲገቡ መታየታቸው መታረም እንዳለበት ያሳሰቡት ዶ/ር ነስረዲን፤ ከአንገት በላይ ጉዳትና የደም መፍሰስ እንዲሁም ከልብ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት በሜዳ ውስጥ በሚገኙት ሙያተኞች አማካኝነት ተጐጂዎች በ90 ሰኮንድ ውስጥ ተገቢውን እርዳታ እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ወጌሻዎች የሚችሉትን ብቻ ማድረግ እንዳለባቸውም ምክር ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ነስረዲን እንዳሉት የከፋ ከአንገት በላይ ጉዳት ሲያጋጥም በእጅ ምልክት ጨዋታውን እስከ ሦስት ደቂቃ ማቋረጥ እንደሚቻል በፊፋ አማካኝነት ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል፡፡ የስፖርት ሕክምና ጉዳይ በብሔራዊ ደረጃ ተገቢውን ትኩረት ያላገኘ ቢሆንም በተቻለ መጠን የሰው ልጅ ሕይወት በሕክምና አሰጣጥ ችግር ምክንያት እንዳያልፍ አምቡላንስና ሌሎች መገልገያዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡

የየክለቡ ወጌሻዎች በሰጡት አስተያየትም የሁሉም ተወዳዳሪ ክለቦች ኃላፊዎች ለስፖርት ሕክምና መሳሪያዎችና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጡ፤ አርቢትሮች ከሰዓት ማባከን ጋር አያይዘው የህክምና ሙያተኞች ወደ ሜዳ እንዳይገቡ የሚያደርጉትን ክልከላ እንዲያስቡበት በተጨማሪም ለክለብ ወጌሻዎች ሥልጠና እንዲሰጥና የሙያ ማህበር ለማቋቋም፣ተገቢው ድጋፍ እንዲሰጣቸው ጥያቄዎች አቅርበው በዶ/ር ነስረዲን ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

ዶ/ር ነስረዲን እንዳስገነዘቡት ለስፖርት ሕክምና ሥልጠና በፊፋና በካፍ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለክለቦች አመራር ፣ለኘሪሚየር ሊግ ወጌሻዎች ፣ ለ26 ሴት ነርሶች በ2007 ዓ.ም ተካታተይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ወደፊትም በብሔራዊ ሊግ ደረጃ ሥልጠናው ይቀጥላል፡፡ የጤና ባለሙያዎችን ከተገቢው የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ጋር የማያሟላ ማንኛውም ክለብ ተመዝግቦ የመጫወት እድል እንደማያገኝም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

ያጋሩ