ዛሬ በስድስት የተለያዩ የሀገርቱ ከተሞች የሚደረጉት ስድስት ጨዋታዎች የሊጉ 11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን መርሀ ግብሮች ናቸው። በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በርካታ ለውጦችን እንደሚያስከትሉ የሚጠበቁትን እነዚህን ጨዋታዎች በዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።
አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
ሁል ጊዜም ሲገናኙ ጠንካራ ፉክክር የሚያሳዩት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ በሳምንቱ ተጠባቂ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። አምና 4ኛው ሳምንት ላይ ተገናኝተው 1-1 በሆነ ውጤት የተለያዩት አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ በመሀላቸው የሶስት ነጥቦች እና የአራት ደረጃዎች ልዩነት ይታያል። ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3-2 በሆነ ውጤት ድል ማድረግ የቻለው አዳማ ከአራት ተከታታይ አቻ ውጤቶች በኃላ ነበር ወደ አሸናፊነት የተመለሰው። ኢትዮጵያ ቡናም የደረሰበት ተከታታይ ሽንፈት ባይደገምበትም ወላይታ ድቻን ማሸነፍ ሳይችል በአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቀው። በዚህም ቡድኑ ዛሬ ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው የሚመራውን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገባ ይመስላል። አዳማ ከተማም ቢሆን እንዳለፉት አመታት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመግባት ከዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥቦችን ማሳካት ግድ የለዋል።
ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ሱለይማን መሀመድ ፣ አዲስ ህንፃ እና ሚካኤል ጆርጅ በአዳማ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ ያሉ ተጨዋቾች ሲሆኑ በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት ያልነበረው ኤፍሬም ዘካሪያስ ወደ ሜዳ ይመለሳል፡፡ ዛሬ ወደ ስፍራው የሚያየመራው ኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ቶማስ ስምረቱ ፣ አክሊሉ አያናው እና አለማየው ሙለታ ከጉዳት ቢያገግሙም ለጨዋታው እንደማይደርሱ ተነግሯል። በተጨማሪም አስናቀ ሞገስ እና ትዕግስቱ አበራ መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዳቸው የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን የጋብቻ ስነስርዐቱን የሚፈፅመው ኤልያስ ማሞም ከቡድኑ ጋር የማይጓዝ ይሆናል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ይህ ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ሀሳብ አምና 30ኛ ሳምንት ላይ ተደርጎ 1-1 ወደ ተጠናቀቀው እና ለወራት የዘለቁ በርካታ ውዝግቦችን ወዳስተናገደው ጨዋታ የሚወስድ ነው። ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው ሀዋሳ ከተማ ፌደረል ዳኛ ሀብታሙ መንግስቴ የሚመራውን የዛሬውን ጨዋታ ሲያስተናግድ በሜዳው ላይ ሲያሳይ የቆየውን ጥንካሬ ስለመመለስ ያልማል። ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ያለውን ደካማ ሪከርድ በማሻሻል ሁለት ጨዋታዎች አቻ መጨረስ ቢችልም ሳምንት ሜዳው ላይ በመቐለ ከተማ ነጥብ በመጣሉ ሀዋሳ ላይ የነበረው የማሸነፍ ጉዞ ማክተሙ ይታወሳል። እንደተለመደው የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ከተቀዳጀው ያልታሰበ ድል በኃላ በወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ተከታታይ ሽንፈት ደርሶበታል። የዛሬው ጨዋታም ክለቡ ካለበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገው ሌላኛው ሙከራው ይሆናል።
ሀዋሳ ከተማ ጋናዊውን ተከላካይ ላውረንስ ላርቴን ፣ ዳንኤል ደርቤን ፣ ካሜሮናዊው ያቡን ዊሊያምን እና አዲስአለም ተስፋዬን በጉዳት የማይጠቀም ሲሆን የዳዊት ፍቃዱ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ደግሞ ዐወት ገ/ሚካኤል ፣ ሀይሌ እሸቱ ፣ ቢኒያም አሰፋ ፣ ዘካሪያስ ቱጂ እና ግብ ጠባቂው ሱለይማን አቡ ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ተስመቷል። ከዚህ ውጪ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ከሀዋሳ እና በሀይሉ ተሻገር ከኤሌክትሪክ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል።
ጅማ አባ ጅፋር ከ መከላከያ
ሁለቱ ቡድኖች ከነበሩበት እጅግ ደካማ አጀማመር መውጣት የቻሉበትን የታህሳስ ወር በሽንፈት ነበር የደመደሙት። በተለይ ከአራቱ የወሩ ጨዋታዎቹ አስር ነጥቦችን ያሳከው ጅማ አባ ጅፋር ከመሪዎቹ ጎራ እስከመቀላቀል ደርሶ ነበር። መከላከያም ቢሆን የነበረበትን የመጨረሻ ደረጃ ለቆ በመጠኑ ከፍ ያለው በዚሁ ወር ባገኛቸው ሰባት ነጥቦች አማካይነት ነው። ሆኖም ዛሬ እርስ በእርስ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ጅማ አባጅፋር በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 መከላከያ ደግሞ በፋሲል ከተማ 1-0 ተሸንፈዋል። ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ በሚመራው የዛሬ ጨዋታም ጅማ አባ ጅፋርን ወደ መሪዎቹ እንዲሁም መከላካያን ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ የማድረግ አቅም ይኖረዋል።
መከላከያዎቹ አዲሱ ተስፋዬ ፣ ኡጉታ ኦዶክ ፣ ሳሙኤል ታዬ እና የተሻ ግዛው ጉዳት ላይ ሲሆኑ መድረሳቸው አጠራጣሪ የሆኑት የአባ ጅፋሮቹ ኦኪኪ አፎላቢ እና ሔኖክ ኢሳያስ የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት አሸናፊ ሽብሩ ፣ ጌቱ ረፌራ እና ዝናቡ ባፋአ ጋር በባለሜዳዎቹ በኩል የሚነሱ ተጨዋቾች ናቸው።
ወላይታ ድቻ ከ አርባምንጭ ከተማ
በሊጉ ካሉ ደርቢዎች በውጥረት የተሞላ ሲሆን የሚታየው በተለምዶው የዳንጉዛ ደርቢ ተብሎ የሚገለፀው ይህ ጨዋታ ዘንድሮ ቡድኖቹ በደካማ አቋም ላይ ሳሉ ነው የሚካሄደው። አምና በተመሳሳይ መርሀ ግብር ሲገናኙ ያለግብ ተለያይተው በነበሩበት ወቅት የተሻለ አቋም ላይ የነበረው አርባ ምንጭ ከተማ በአሰልጣኞች እና አመራሮች ሹም ሽር መሀል አራት ተከታታይ ሽንፈቶችን አስተናግዶ በሊጉ ግርጌ ተቀምጧል። በአንፃሩ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኃላ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ያገኘው ወላይታ ድቻ የተሻለ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃ/ ስላሴ በመሀል ዳኝነት የተመደቡበት ይህን ጨዋታ ማሸነፍ በደርቢነት ስሜቱ የተነሳ ከሚፈጥረው መነቃቃት ባለፈ ቡድኖቹ ያሉበትን ወቅታዊ ውጤት አልባ ጉዞ ለመቀልበስ እንደመንደርደሪያ ሊሆናቸው እንደሚችል ይታሰባል።
ወላይታ ድቻ ፀጋዬ ብርሀኑን ፣ አምረላህ ደልታታን ፣ እርቅይሁን ተስፋዬን እና ቻዳዊውን ማሳማ አሳልሞን በጉዳት የማይጠቀም ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ በኩል ጋናዊው አሌክስ አሙዙ ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና ታዲዮስ ወልዴ በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው የማይደርሱ ይሆናል። በተጨማሪም በሁለቱም በኩል ተስፉ ኤልያስ እና ገ/ሚካኤል ያዕቆብ ብዩት የቀጥታ ቀይ ካርድ ምክንያት ቅጣት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ናቸው። የአርባምንጭ ከተማው አምበል አማኑኤል ጎበና ከረዥም ጊዜ ጎዳት በኃላ ቢያገግምም የመሰለፍ ዕድሉ አለየለትም። በተያያዘ ዜናም አጥቂው ተሾመ ታደሰ ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ ቢጀምርም ቴሴራ ያልተሰራለት በመሆኑ ወደ ሜዳ ለመመለስ የውድድሩን አጋማሽ የሚጠብቅ ይሆናል። ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ባገኘችው ሌላ መረጃ አዲሱ አሰልጣኝ እዮብ ማለ ልምምድ ማሰራት ቢጀምርም የፌዴሬሽን ጉዳይ ባለማጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ በምክትል አሰልጣኙ ማቲያስ ለማ እየተመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
ድሬደዋ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
ከአሰልጣኝ ለውጥ በኃላ በአጨዋወት ረገድ በጥቂቱ መነቃቃት ታይቶበት የነበረው ድሬደዋ ከተማ ሳምንት ወደ መቐለ አቅንቶ 2-0 ተሸንፏል። በመሆኑም 8 ነጥቦችን ይዞ 14ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። በሳምንቱ መጨረሻ የክለቡ ስራ አስኪያጅ የነበሩትን አቶ እስከዳር ዳምጠውን በአቶ አንበሳው አውጋቸው የተኩት ድሬዎች በአሰልጣኝ ስምዖን አባይ እየተመሩ ከሚያደርጉት አራተኛ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻሉ የእፎይታ ጊዜ የሚያገኙ ይሆናል። በአንፃሩ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሽንፈትን ያስወገዱት ሲዳማዎች ሰባት ነጥቦችን በመሰብሰባቸው ከነበሩበት የመጨረሻ ደረጃ ወደ 9ነኛነት ከፍ ብለዋል። በፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ የመሀል ዳኝነት ከሚካሄደው ከዚህ ጨዋታ ሌላ ሶስት ነጥብ ማሳካት ከቻለም ሲዳማ መሪዎቹን የመጠጋት ዕድል ይኖረዋል።
በድሬደዋ ከተማ ለረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት ሀብታሙ ወልዴ እና ዘነበ ከበደ በተጨማሪ አህመድ ረሺድም ለጨዋታው ብቁ ላይሆን የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው። ሲዳማ ቡና ደግሞ ፈጣኑን ጋናዊ የመስመር አጥቂ አብዱለጢፍ መሀመድን እና ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳን በጉዳት ምክንያት የሚያጣ ይሆናል።
ደደቢት ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
የሊጉ መሪ ደደቢት የሚገኝበትን አስደናቂ ጉዞ የሚገታ አልተገኘም። ቡድኑ በተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን ከማሸነፉ ባለፈ ውጤታማነቱ ሜዳው ላይም ሆነ ከሜዳው ውጪ የሚንፀባረቅ መሆኑ አስገራሚ አድርጎታል። 10ኛው ሳምንት ላይ ነጥብ ሊጥል ይችላል ተብሎ የተጠበቀበትን የአርባምንጭ ጨዋታም በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች ታግዞ ማሸነፍ ችሏል። ተጋጣሚው ወልዋሎ ደግሞ ጥሩ የሚባሉ ሳምንታትን ካሳለፈበት የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች በኃላ እየተዳከመ ይገኛል። ካለፉት አራቱ ጨዋታዎቹም ሁለቱ በሽንፈት የተደመደሙ ነበሩ። ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በሚመራው የዛሬ ጨዋታም የደደቢት አይበገሬነት የሚቀጥልበት ወይንም ወልዋሎ የሚያገግምበት እንደሚህምን ይጠበቃል።
የደደቢቱ የመስመር ተከላካይ እና የቡድኑ አምበል ብርሀኑ ቦጋለ ከረዥም ጊዜ ጉዳት በኃላ የተመለሰ ሲሆን አማካዩ ፋሲካ አስፋው ግን ለጨዋታው አይደርስም። በወልዋሎ ዓ.ዩ በኩል ደግሞ እንየው ካሳሁን በቅጣት እንዲሁም በወልድያው ጨዋታ ጉዳት የገጠማቸው ኤፍሬም ጌታቸው እና እዮብ ወ/ማርያም ለጨዋታው አይደርሱም።