​ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ጌዲኦ ዲላ ከሜዳው ውጪ ሲያሸንፍ ድሬዳዋ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 6ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምረዋል። ጌዲኦ ዲላ ከሜዳው ውጪ ድል ያስመዘግብ ድሬዳዋ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል።

ሀዋሳ ከተማ 0-1 ጌዲኦ ዲላ

09:00 ሰአት ላይ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም በተደረገው በዚህ ጨዋታ እንግዶቹ  የእነረቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን አነጋጋሪ የዳኝነት ውሳኔዎች እና ውዝግቦች የጨዋታው አካል ነበሩ።

ጨዋታው እንደተጀመረ 51ኛው ሰከንድ ላይ የጌዲኦ ዲላዋ አምበል ማርያም ታደሰ በግብ ክልል ውስጥ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን የፍ/ቅጣት ምርቃት ፈለቀ ብትመታም ግብ ጠባቂዋ ቤቴልሄም ዮሀንስ መልሳባት ሀዋሳ በፍጥነት መሪ የሚሆንበትን ወርቃሜ እድል አምክናለች። በ13ኛው ደቂቃ ላይ አማካይዋ ፋሲካ ንጉሴ በረጅሙ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል የላከችውን ኳስ የግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ሄርቀሎ እና የተከላካይዋ አረጋሽ ፀጋን ያለመናበብ ተጠቅማ ትንቢት ሳሙኤል ዲላዎችን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ከግቧ በኃላ ጫና መፍጠር የቻሉት ዲላዎች 26ኛ ደቂቃ ፋሲካ ንጉሴ የግብ ጠባቂዋን የአቋቋም ስህተት ተመልክታ የሞከረችውና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣባት ኳስ ልዩነቱን ልታሰፋ የምትችል አጋጣሚ ነበረች። በ38ኛው ደቂቃ ልደት ቶሎአ ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ያመከነቻት ኳስ ደግሞ በሀዋሳ በኩል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳ ከተማዎች በመጠኑም ቢሆን በጌዲኦ ዲላ ላይ ብልጫ ቢወስዱም የፈጠሯቸው የግብ እድሎችን ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በ57ኛው ደቂቃ ልደት ቶሎአ ወደ ሳጥን እየገፋች ገብታ የሞከረችው እንዲሁም ነፃነት መና እና መሳይ ተመስገን ያልተጠቀሙባቸው አጋጣሚዎች ሀዋሰመን ወደ ጨዋታው ሊመልሱ የሚችሉ ነበሩ።

የጨዋታው መደበኛ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማዋ ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ በስመኝ ምህረቴ ላይ አደገኛ አጨዋወት በመጫወቷ የጌዲኦ ዲላው አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ከጥፋት ሰሪዋ ቅድስት ጋር ግብግብን ፈጥረው ዳኛዋ በዝምታ ማለፋቸው ከበርካቶችን ተቃውሞ እንዲገጥማቸው ምክንያት ሆኗል።

ጌዲኦ ዲላ ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ  ነጥቡን 11 በማድረስ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከወትሮወረ አቋሙ በተቃራኒ መንገድ እየተጓዘ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ድሬዳዋ ከተማ 2-2 አዳማ ከተማ 

በድሬዳዋ ስታዲየም ከከፍተኛ ሊግ ጨዋታ በኋላ 10:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ ባለሜዳው ድሬዳዋ ከተማ በሁለት የግብ ልዩነት ከመመራት ተነስቶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በ19ኛው ደቂቃ ሰርካዲስ ጉታ አዳማን ቀዳሚ አድርጋ የመጀመሪያው አጋማሽ በአዳማ መሪነት ሲጠናቀቅ በሁለተኛው አጋማሽ 56ኛው ደቂቃ ዮዲት መኮንን የአዳማን ግብ ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች።

ግብ ለማስቆጠር ተጭነው መጫወት የቻሉት ድሬዎች 59ኛ ደቂቃ ላይ የቀድሞዋ የሲዳማ ቡና እና አአ ከተማ አጥቂ ተራማጅ ተስፋዬ ባስቆጠረችው ጎል ልዩነቱን ሲያጠቡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ብቻ ሲቀረው ያብስራ ይታየው አስቆጥራ ድሬዳዋ ከሽንፈት ታድጋለች።
የአቻ ውጤቱ አዳማ ከተማን በ6 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጠው ድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ልዩነት ተበልጦ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሊጉ የ6ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ነገ ሲቀጥል አአ ስታድየም ላይ በ08:00 ደደበቢት ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ ይርጋለም ላይ ሲዳሜ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ09:00 ይጫወታሉ።

በሊጉ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ | የሴቶች ፕሪምየር ሊግ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *