በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሁለተኛ ቀን መርሃግብር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሊጉ መሪ ደደቢት 8ኛ ደረጃ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ 4-2 በመርታት በ100% ሪከርዱ ቀጥሏል፡፡
8 ሰአት ሲል የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም የጠሩ ግብ ሙከራዎች ላይታዩበት በአመዛኙ ተመጣጣኝ የሆነ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር፡፡ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ባሩዳ ወደ ግብ የላከችውን ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ለማዳን ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተገኘችውን የፍጹም ቅጣት ምት ሎዛ አበራ ወደ ግብነት ቀይራ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
ከዚች ግብ መቆጠር በኃላ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ደደቢቶች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀር ሰናይት ቦጋለ ያሳለፈችላትን አስገራሚ ኳስ በመጠቀም ትእግስት አበራ በቀድሞው ክለቧ መረብ ላይ ማራኪ ግብን በማስቆጠር የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡
ከእረፍት መልስ ጥታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ደደቢቶች በ68ኛው ደቂቃ ላይ ነህሚያ አበራ ባስቆጠረችው ጎል ልዩነቱን ወደ 3 ከፍ ሲያደርጉ በደቂቃዎች ልዩነት በ70ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሄም ሰማን የቅዱስ ጊዮርጊስን ተስፋ ያለመለመች ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ በዚች ግብ የተነቃቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ83ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ መትፋቷን ተከትሎ ያገኘችውን ኳስ ተጠቅማ ተከላኳይዋ አስቆጥራ የቡድኗን ተስፋ ይበልጥ ማለምለም ችላ ነበር፡፡ ሆኖም በ85ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው አልፊያ ጃርሶ ግሩም ጎል ከቆመ ኳስ በማስቆጠር የቅዱስ ጊዮርጊሶችን ተስፋ አጨልማለች፡፡
ጨዋታው በደደቢት የ4-2 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢቶች ነጥባቸውን ወደ 18 በማሳደግ አሁንም በመሪነታቸው ቀጥለዋል፡፡
ሊጉ ነገ እና ማክሰኞ በሚደረጉ ጨዋታዎ ሲቀጥል ሰኞ መከላከያ ከ ኤሌክትሪክ ፣ ማክሰኞ ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጫወታሉ፡፡