ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሀከል ጅማ ላይ የተገናኙት ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ 1-1 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።
ጅማ አባ ጅፋር ከመጀመሪያ ተሰላፊዎቹ መካከል ሄኖክ ኢሳያስ እና ኦኪኪ አፎላቢ በጉዳት ባለመኖራቸው እንዳለ ደባልቄን እና ሳምሶን ቆልቻን የተካ ሲሆን ቢኒያም ሲራጅም ወደ ተጠባባቂ ወንበር ወርዶ መላኩ ወልዴ ጨዋታውን የመጀመር ዕድል አግኝቷል። በመከላከያ በኩል ደግሞ አማኑኤል ተሾመ በሳሙኤል ሳሊሶ እንዲሁም ቴውድሮስ በቀለ ከቆይታ በኃላ በዐወል አብደላ የመሀል ተከላካይ ቦታ ሲተኩ ወሳኙ አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ እና ማራኪ ወርቁም ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ተመልሰዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው እንቅስቃሴ መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ ሆኖ ሲያልፍ በርካታ የሜዳ ላይ የተጨዋቾች ሽኩቻዎችን ተከትሎ ተደጋጋሚ የአልቢትሩ ፊሽካ የሚሰማበት እና የቆሙ ኳሶች የተበራከቱበት ነበር። በዚህ ረገድ በጨዋታው ከተመዘገቡት 23 ጥፋቶች ውስጥ 11 የሚሆኑት በመጀመሪያው አጋማሽ የተሰሩ ሲሆኑ ጅማ አባጅፋሮች 6 እንዲሁም መከላከያዎች 5 ጥፋቶችን የመስራት ድርሻ ነበራቸው። ጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ ያስተናገደውም 25ኛው አቂቃ ላይ ሲሆን ኤልያስ አታሮ ከግራ መስመር ካሻማው ኳስ አጥቂው ተመስገን ገ/ኪዳን ከአቤል ማሞ ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም ሙከራው በግብ ጠባቂው ድንቅ ጥረት ወደ ጎልነት ሳትቀየር ቀርታለች። በዚሁ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ ለጎል ከቀረቡበት ከዚህ አጋጣሚ ውጪ ሌላ አንድ ተጨማሪ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን መከላከያዎችም በሶስት አጋጣሚዎች የተጋጣሚያቸውን ግብ ለመፈተሽ ሞክረዋል።
ከእረፍት መልስ ጨዋታው በተወሰነ መልኩ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ፈጠን ያለ እንቅስቃሴን ሲያስተናግድ ቡድኖቹ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦችም መነቃቃትን ፈጥረውለታል። ቀድመው መሪነቱን መውሰድ የቻሉት እንግዳዎቹ መከላከያዎች ነበሩ። 53ኛው ደቂቃ ላይ ከጅማ አባ ጅፋሮች ሳጥን ውስጥ ቴውድሮስ ታፈሰ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ግቧን ማስቆጠር የቻለው መከላከያ በተከታታይ ጨዋታዎች ለሰበሰባቸው ነጥቦች ዋነኛ ተጠቃሽ የሆነው ምንይሉ ወንድሙ ነበር። ከግቧ መቆጠር በኃላ ጅማ አባጅፋሮች ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን በተለይ ጥሩ መንቀሳቀስ ያልቻለውን እንዳለ ደባልቄን በንጋቱ ገ/ስላሴ ቀይረው ካስገቡ በኃላ የማጥቃት ኃይላቸው ተሻሽሎ ታይቷል። በአንፃሩ መከላከያዎች ያገኙትን መሪነት ለማስጠበቅ ያሰቡ በሚመስል መልኩ አፈግፍገው መጫወት የቀጠሉ ቢሆንም ይህ ጥረታቸው ተሳክቶ የቀጠለው እስከ 74ኛው ደቂቃ ድረስ ብቻ ነበር። በዚህ ደቂቃ ላይም ዮናስ ገረመው በረዥሙ ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ሳምሶን ቆልቻ በግንባሩ በመግጨት አባጅፋሮችን አቻ ማድረግ ችሏል። ከዚህ በኃላ በነበሩት የጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች ቡድኖቹ ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ባለመቻላቸውም ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ደጋፊዎች በተጨዋቾች እና በዳኞች ላይ ይሰነዝሩ በነበረው ተቃውሞ ምክንያት የአሰልጣኞችን አስተያየት ለማካተት አልቻልንም። ሲደጋገም የሚታየው ይህ ጉዳይ ክለቦች የደጋፊዎቻቸውን ስነምግባር ለማሻሻል ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው የሚያመለክት ነው።