በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ቀን ውሎ ሶዶ ላይ በዳንጉዛ ደርቢ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠና በእጅጉ የሚርቅበትን 3 ነጥብ ሲያሳካ በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማ አስከፊ የሊጉ ጉዞው ገፍቶበታል።
ከጨዋታው መጀመር በፊት በወላይታ ድቻ የደጋፊዎች ማህበር አማካኝነት የመቀራረብ እና የወንድማማችነት መልካም ተግባር ለማሳየት ኢሻኔ ሚቾ (እህትና ውንድም ነን) የሚል መፈክር ተይዞ የኢትዮጲያ ብሔራዊ መዝሙር ተዘምሯል።
ወላይታ ድቻ ባለፍነው ሳምንት ከኢትዮጲያ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ዘላለም እያሱ ጉዳት በገጠመው አመርላ ደልታታ የተተካ ሲሆን አርባምንጮች በሜዳቸው በሊጉ መሪ ደደቢት ከተሸነፈው ቡድናቸው የስድስት ተጨዋቾች ቅያሪ በማድረግ ሰሞንኛውን የክለቡ የአመራር እና አሰልጣኞች ለውጥ በቡድናቸውም ደግመውታል።
በዚህ መልኩ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች በለሜዳዎቹ ድቻዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ወደ ግብ በመድረስ በኩል የተሻሉ ነበሩ፡፡ ይህም ጥረታቸው ተሳክቶ 9ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሸገረውን ኳስ አንድነት አዳነ ከጎል ክልል ለማውጣት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የሰራውን ስህትተ ተጠቅሞ ዘላለም እያሱ በአግባቡ በመቆጣጠር ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ለሚገኘው አብዱልሰመድ አሊ አቀብሎት ፤ አብዱልሰመድ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ከጵዮን መርዕድ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል። ከዚህች ጎል መቆጠር በኃላ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ አርባምንጭ ከተማዎች ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው ወደ ድቻ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ በዚህም መልኩ በተለይም ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች በመታገዝ በዕለቱ ጥሩ የነበረውን ወንድስን ገርምውን ሲፈትኑት ቆይተዋል። ከጫናዎቹ መነሻነትም አዞዎቹ በተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶችን ሲያገኙ ፤ በተለይም 14ኛው ድቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳው ኳስ በድቻ ተከላካዮች ተመልሶ በድጋሚ እንዳለ ከበድ በጥሩ ሁኔታ አሻምቶት አማካዩ አለልኝ አዘነ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢሞክርም ወንድወሰን ገረመው ግብ ከመሆን ታድጓታል። የአርባምንጮች ጫና ቀጥሎ በ18ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት አንድነት አዳነ ከርቀት አክርሮ የመታዉን አሁንም ወንደስን ገረመው በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። በዚህ አጋጣሚ የተገኘችውን የማዕዘን ምት ወንደስን ሲጨርፈው ላኪ ሳኒ አግኝቶት ቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክር መስመር ላይ የነበረው ሙባሪከ ሸኩር ወደ ዉጪ አውጥቶበታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም አርባምንጮች ረዣዥም ኳሶችን ወደ ድቻ የግብ ክልል መላካቸውን ቢቀጥሉም ይህ ነው የሚባል የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጮች በጨዋታው ብዙም ጎልቶ ያልታየውን ላኪ ሳኒን በተመስገን ካስትሮ ቀይረው በማስገባት በመጀመርያ የነበራቸውን ብልጫ ወደ ጎል ለመቀየር ጥረታቸውን ጀምረዋል። በተቃራኒው ድቻዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን መርጠዋል። ያም ቢሆን ቢሆን ኳስ በአግባቡ አለመደራጀቱ እና ከኃላ ሲመሰረትም ተከላካዮች በተለይም እሸቱ መና እየተው በሚሄዱት ቦታ እና ተክሉ ታፈሰ በተድጋጋሚ የሚስራቸው ስህተቶች አርባምጮች በይበልጥ ጫና እንዲፈጥሩ ረድቷቸዋ ታይተዋል፡፡ ጨዋታው ግልፅ የሆኑ የግብ ዕድሎች ባይፈጠሩበትም በ49ኛው ደቂቃ ተመስገን ካስትሮ ከርቀት የመታትና ወደ ዉጪ የወጣችው ኳስ ስትጠቀስ 84ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳ ኳስ በአርባምጭ ተጨዋቾች ንክኪ ጎል መሆን ቢችልም በንክኪው ሂደት ወንድወስን ገረመው ላይ ጥፋት በመስራቱ ምክንያት የመሃል ዳኛው ለድቻ የቅጣት ምት ሰጥተው አልፈውታል፡፡ በ88 ደቂቃ በወላይታ ድቻ በኩል በመልሶ ማጥቃት የተገኘችዉን ኳስ ደግሞ በዛብህ መለዮ ከርቀት አክርሮ ቢመታትም ጲዮን መርዕድ ወደ ዉጪ አውጥቶበታል።
ጨዋታው በዚህ መልኩ ድቻ 1-0 አሸንፎ ሶስት ነጥብ በማሳካት ነጥቡን 12 አድርሶ ደረጃዉን ሲያሻሽል ፤ በአንፃሩ አርባምጭ ከተማ በ 6 ነጥቦች እዛው የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል፡፡