ንግድ ባንክ በተጫዋቾች ዝውውር እየመራ ነው


የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሌሎች ክለቦች ቀድሞ ተጫዋቾችን በማዘዋወር ላይ ተጠምዷል፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ሁሉንም ስፍራዎች በተጫዋቾች ለማጠናከር የቆረጡ ይመስላሉ ፡፡ ከክለቡ የሚወጡ ዜናዎች እንደሚያመለክቱትም ባንክ እስካሁን 7 ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

የቀድሞው የሀረር ሲቲ ግብ ጠባቂ ዳዊት አሰፋን ከመከላከያ አስፈርመዋል፡፡ ዳዊት በውድድር ዘመኑ መጀመርያ የይድነቃቸው ኪዳኔ ተጠባባቂ የነበረ ሲሆን ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ወደ ቋሚ አሰላለፉ በመመለስ የውድድር ዘመኑን አጠናቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ቡና የለቀቀው ስንታለም ተሻገር ሌላው ንግድ ባንክን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው፡፡ ተከላካዩ የአንጋፋውን ሳምሶን ሙሉጌታ ቦታ ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ መሃሪ መና ጥሎት የሄደውን ቦታ በኢትዮጰያ መድኑ ሲሳይ ቶላ ግዢ ሸፍነዋል፡፡ ሲሳይ በደካማው የመድን የውድድር ዘመን ጉዞ በመልካምነት ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ ነበር፡፡

ንግድ ባንክ በማጥቃት ወረዳው 4 ምርጥ ግዢዎችን ፈፅሟል፡፡ በኢትዮጰያ ቡና ማንነቱን የማሳየት እድል የተነፈገው ሰለሞን ገብረ መድህን ፣ ምርጥ የውድድር ዘመን ያሳለፈው የመስመር አጥቂው ኤፍሬም አሻሞ ፣ የሙገሩ የፊት አጥቂ አኪም አካንዴ እና የመብራት ኃይሉ የአጥቂ አማካይ አብዱልከሪም ሃሰን ንግድ ባንክ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የተጫዋቾች ግዢው በፈጠራ እና የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል ደካማ መሆኑን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ያሳየው ንግድ ባንክን አስፈሪ ያደርገዋል ተብሎ ይገመታል፡፡

በተያያዘ ዜና ንግድ ባንክ የዋለልኝ ገብሬ ፣ ታዬ አስማረ እና ዮሃንስ ሽኩርን ኮንትራት አራዝሟል፡፡ የፊሊፕ ዳውዚንም ኮንትራት ለማራዘም እየጣሩ ሲሆን ወሰኑ ማዜ የንግድ ባንክን የውል ማራዘምያ ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቷል፡፡

-ምንጭ – ፕላኔት ስፖርት (ኤፍኤም 96.3)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *