ሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም
በክፍል አንድ መሰናዷችን ባለፈው ወር 7ኛ የሙት አመታቸው ስለተከበረው መንግስቱ በስራቸው ሰልጥነው ያለፉ እና በአሰልጣኝነትም አብረው የሰሩት አስራት ኃይሌ ፣ ስዩም ከበደ እና ንጉሴ ገብሬ ያላቸውን ትውስታ አካፍለውን እንደነበር ይታወሳል። በክፍል ሁለት ደግሞ ከተለያዩ ትውልድ አሰልጣኞች መካከል የሶስቱን ምልከታ አቅርበንላችኋል።
ወርቁ ደርገባ
የመንግሥቱ ወርቁ አዎንታዊ የአሰልጣኝነት ስብዕና በዋነኝነት ያሳደረብኝ ተፅዕኖ በተለይ በራስ የመተማመኑ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ ትልቁ የስልጠና ግብዓትም ሆኖልኛል ፡፡ ሁለተኛው በከፍተኛ ደረጃ ሙያው ማስከበሩ ነው፡፡፤ ሙያውን በየትኛውም አካል ፊት ያለምንም ፍራቻ ያስከብር ነበር፡፡ስራውን ካለ ይሉኝታ የሚሰራበት እና እንዲሰራ የሚያደርግበት መንገድ ለርሱም ሆነ ለእግርኳሱ በጎ ገጽታን ፈጥሯል፡፡፡፡ሶስተኛው ስራውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የሚያከናውንበት ሒደት ለኔም በአሁኑ ግዜም የምጠቀምበት ነው፡፡እነዚህና ሌሎች መልካም ነገሮች ከመንግስቱ ስብዕና መገለጫዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ጣልቃ ገብነትን በእጅጉ ይቃውም ነበር፡፡ ከመንግሥቱ ጋር በሁለት አመት ኮንትራት ነበር የብሔራዊ ቡድን ስራን የያዝነው፡፡ በመጨራሻዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከናይጀሪያ ጋር አንድ ጨዋታ ነበረን፡፡ በግንቦት 20 ውድድር ላይ ወደ ስድስት የሚደርሱ ቡድኖች ተሳትፈው እኛ ነበርን ዋንጫውን የወሰድነው፡፡ በጣም ደስ የሚል ውድድር ነበር፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ያገኘውን ውጤቱን ለማጣጣል የሚቀርቡበትን አሉባልታ በቀጥተኝነት እና ፊት ለፊት ነበር የሚጋፈጠው፡፡በተፈጥሮም ቁጡ በመሆኑ የሚመስለውን ይናገር ነበር፡፡በዚህ የተነሳም ከሐላፊነቱ እንዲታገድ ተደርጎ ነበር ፡፡በሙያው በሚመጣበት ምንም ነገር ላይ ወደ ኃላ አይልም፡፡እኔም ይህ የሱ ተጽእኖ ተጋብቶብኝ ሙሉበሙሉ የማምንበት ጉዳይ ሆኖልኛል፡፡
ከርሱ የወሰድኩት ትልቁ ነገር የስልጠና አካሄዱን እና ዘዴዎቹን ነው፡፡ የስልጠና መንገዶቹ በእርግጥም አስተማሪ ነበሩ፡፡ ሁሌም የሚናገራቸው አስምህሮዎች ነበሩት፡፡
ስልጠና ፣ድግምግሞሽና ዕርምት የሚላቸው ፡፡ “በስልጠና ውስጥ ድግግሞሽ የግድ ነው፡፡አንድን የስልጠና አይነት በድግግሞሽ ሳትሰራ ሰልጥኛለው አትበል ፡፡”ይል ነበር ፡፡”ከስልጠናው ድግግሞሽ የዕውቀት መስረጽ ይፈጠራል፡፡ይህም ልምምዶችን በእውቀት ወደ መስራት ያመራል፡፡ያለ ድግግሞሽ የሚሰጥ ስልጠናም ፍሬአልባ ነው፡፡”ብሎ ያስተምረን ነበር ፡፡”ከድግግሞሹ በኋላ ደግሞ በጥልቅ እይታ እርምት ስጥ፡፡” ብሎም ያክልልን ነበር፡፡ በድግግሞሽ እና በእርምት ውስጥ የሚያልፍ ስልጠና ወደ ምሉዕነት ያስጠጋል፡፡”ይል ነበር፡፡ይህ እምነቱን ሁሌም በስራዬ እተገብረዋለው፡፡
የመንግሥቱ የልምምድ መርሀ ግብሮች የበለጠ ቴክኒካዊ እና ታክቲካዊ ይዘት ነበራቸው፡፡በርግጥ የአካል ብቃት ላይም ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ነበር፡፡በሜዳ ውስጥ ተጫዋቾች በጋራ የመከላከል እና የማጥቃትን ስራን ከመስራታቸው በፊት በተናጠል በተጫዋቾቹ የአጨዋወት ባህሪ እና የሜዳ ላይ ሚና ተወስኖ በየዲፓርተመንቱ የመጫወቻ ክፍል ለየብቻ ልምምድ ማድረግ አለባቸው::” የሚል ዕምነት ነበረው፡፡ የግብ ጠባቂ ክፍል፣ የተከላካይ ክፍል፣የአማካይ ክፍል እና የአጥቂ ክፍል የመከላከል እና የማጥቃት ስራን በየክፍላቸው ከሰሩ በኃላ እንደገና እነዚህን ክፍሎች የሚያገናኛቸው ስራ መሰራት አለበት፡፡ ግብ ጠባቂው ከ ተከላካይ ፣ተከላካዪ ከ አማካይ እና አማካዩ ከ አጥቂው በግል እና በቡድን የታክቲካዊ ስራዎች ድግምግሞሽ የመግባባት ስራዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡”ብሎ የሚያምን ሰው ነበር፡፡ በትልቅ ትምህርትነታቸው ተቀብዬ እስካሁንም የምጠቀምባቸው ሀሳቦች ነው ፡፡ ሌላው የሚነገርለት እምነቱ “ተጫዋቾች ሁለገብ መሆን አለባቸው ፡፡” የሚለው እሳቤው ነው፡፡ “እኛ ሀገር ተጫዋቾች ያላቸው የተገደበ የሜዳ ውስጥ ሚና እና ችሎታዬ ‘በዚህኛው’ የመጫወቻ ስፍራ ነው” ብለው መደምደማቸው በጣሙን ጎድቷቸዋል፡፡” ይል ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ከአከባቢያቸው ይዘውት በሚመጡት የመጫወቻ ቦታ ላይ ብቻ የመትጋት ዝንባሌን ያሳያሉ፡፡ ሳያውቁት የተሻለ ብቃት የሚያሳዩበትን ቦታ ያልፉታል፡፡ በዚህ በኩል መንግሥቱ ለተጫዋቾች የተሻለ ቦታ ይሰጣቸውና ጥሩ ሆነው ሲወጡ ያያቸዋል፡፡ ተጫዋቾቹም ያምኑበትና በዛው ይቀጥላሉ፡፡ የተሻለ ነገር ለማበርከት ተጫዋቾችን ሁለገብ የማድረግ አሰራር ለኔ ትልቅ ትምህር ነበር፡፡ መንግስቱ በታዳጊዎች ላይ ባለው እምነትም ይታወቅ ነበር፡፡
በ1980 ዓ.ም አካባቢ በአገሪቱ የነበሩ የከፍተኛ ዲቢዚዮን ትልልቅ እና ልምድ ያላቸውን አሰልጣኞች በመጥራት አዲስ አበባን ማእከላዊ ቦታ በማድረግ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ወጣቶችን በመመልመል ትልቅ የወጣቶች ፕሮጀክት የመመስረት ሀሳብን ተግባራዊ የማድረጉ ሰራን ጀምሮ ነበር፡፡ በተጫዋቾች ስነ ምግባር ላይም ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡በቡድን ወስጥ ክፍፍል እንዳይፈጠር በርትቶ ሰርቷል ፡፡ሁሉም ተ፡ጫዋቾች የእኩልነት ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡በተጫዋቾች መካከልም ስለሚኖር መከባበር ትልቅ ዋጋ ይሰጥ ነበር፡፡በብሔራዊ ቡድን በነበረን ቆይታ እንደ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሆኖም አገልግሏል፡፡በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ በእድሜ ደረጃ የተለያዩ የቡድን እርከኖቾ እንዲኖሩት ብዙ እቅዶችን ይነድፍ ነበር፡፡በተጫዋቾች ስነ ልቦና አዕምሯዊ ጉዳዮችም ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡
ገብረመድህን ኃይሌ
ማንም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በእግርኳሱ አከባቢ ስመጥር ከተባሉት መካከል አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ትልቅ አሻራ ያሳረፈ ሰው ነው፡፡ እኔ እንግዲህ ሲጫወት አላውቀውም፤ በስልጠና ሂደት ውስጥ እያለ ነውየተዋወኩት፡፡ በ1982 በጊዮርጊስ እንዲሁም በ1983 በብሄራዊ ቡድን አብረን ሰርተናል ፡፡ እኔ ጊዮርጊስ ሆኜ እሱ ሌላ ክለብ እያሰለጠነ አውቀዋለው፡፡ ግን ሌሎች ክለቦች ሲያሰለጥን ቡድኑን ሲመራ ካልሆነ በስተቀር የማየት ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ እኔን ያሰለጠነኝ የተወሰነ ጊዜ ነበር ፡፡በተለይ በአንደኛው ዓመት ቻምፒዮን የሆንነው በእሱ አሰልጣኝነት አንድም ጨዋታ ሳንሸነፍ ነበር፡፡ ይህ ለየት ያደርገዋል፡፡ መንግስቱ አንዳንድ ልምምዶችን ሲያሰራ ጥሩ ተጫዋች እንደነበረ በደንብ ያስታውቃል ፡፡ ምንም እንኳን እኔን ያሰለጠነኝ እድሜው በገፋበት፣ ነገሮችን በአግባቡ እያሳየ ሊያሰራን የሚችልበት አቅሙ ላይ ባልነበረበት ወቅት ቢሆንም አንዳንድ ግዜ ኳስ የሚቆጣጠርበት እና በደረቱ የሚያበርድበት ሁኔታ ጥሩ ችሎታ እንደነበረው አመላካች ነበሩ፡፡ እንደሰማሁት በኳስ ቁጥጥር እና በግንባር በመግጨት ጥሩ ነበር።ባጠቃላይ ጥሩ ስብዕና የነበረው ታላቅ ሰው ነው፡፡ ሁሉም አሰልጣኝ ይከበራል። ተጫዋቾች በመንግሥቱ ስኬታማ የተጫዋችነት የኃላ ታሪክ ለእሱ የነበራቸው ክብር በጣም የተለየ ነበር፡፡ የእግርኳሱ እውቀቱ ጥሩ ነበር፡፡ በመከላከል እና ማጥቃት መሠረታዊ መረሆዎች የሚሰጣቸው ገለፃዎችን መሳጭ እና ከፍተኛ ዋጋ ነበራቸው፡፡አሁን ላይ ሆኜ በማየው ሳይሆን የምገልጽልህ በወቅቱ እኔ ከነበርኩበት ጊዜ አንፃር ነው፡፡ ስለእሱ የማስታወሰው በጣም በጎ ነገሮችን ነው፡፡ በተጫዋችነት ጊዜያችን ደብተር ይዘን ያስተምረን ነበር፡፡ ስትከላከል ምን ማድረግ እንደሚኖርብን እና በየትኛው መንገድ የማጥቃት አጨዋወትን መተግበር እንዳለብን ያስተምረን ነበር፡፡ ጥሩ እውቀት የነበረው አሰልጣኝ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም፡፡
እሱ መድን አሰልጣኝ ሆኖ እኔ ጊዮርጊስ እየተጫወትኩ በተቃራኒነት ተገናኝተናል፡፡ አስር ዓመት ነው ጊዮርጊስ የተጫወትኩት፡፡ በእነዚህ ግዜያቶች ሁሉ ተቃራኒ ሆነን ተጫውተናል፡፡ መብራት ሐይልም ሲያሰለጥን አውቀዋለው፡፡ በተለይ መድንን ሲያሰለጥን ጥሩ ቡድን ሰርቶ ነበር። ትዝ የሚለኝ ያኔ እኛ የመን ሃገር ሄደናል። እናም ደርሰን ስንመጣ መድን በጣም ያንፀባረቀበት ወቅት ነበር፡፡ ያን ግዜ ሊግ አልነበረም። የአዲስ አበባ ሻምፒዮና ነው የሚባለው።አስር ክለቦች ነው የነበሩት። እናም ከመጣን በኃላ ካታንጋ ገብቼ ያየሁት አንድ ጨዋታ በማታ መድን ከቡና ሲጫወት ነበር። መድን በጨዋታ በልጦ አመሸ። በጨዋታው ኮከብ ሆኖ ያመሸው ታደለ ከፖሊስ የሄደ ተጫዋች ነበር፡፡ ሜዳው አልበቃውም፡፡ በዚያ ጨዋታ የታየው ጠንካራው መድን ቡናን 2-0 ያሸነፈው አሳምኖ ነበር፡፡ ቡድኑ የመንግስቱ ሙሉ ስራ ነው፡፡
ጥሩ ጥሩ አሰልጣኞች አሰልጥነውኛል-አስራት ሃይሌ አና ካሳሁን ተካን የመሳሰሉት፡፡ ስዩም አባተም ለተወሰነ ጊዜ የአዲስ አበባ ምርጥ ላይ አሰልጥኖኛል፡፡በአሰልጣኝነት ህይወቴ የራሴ ነገሮች ቢኖሩኝም የእነዚህ ታላላቅ አሰልጣኞች ተጽእኖ ከፍተኛ ነው። ከእያንዳንዳቸው ጥሩ ነገሮችን ወስጃለሁ፡፡ አሰልጣኝ ከአንድ ሰው ብቻ ትምህርት ሊወስድ አይችልም፡፡ የእያንዳንዱን ቀደምት አሰልጣኞች ጠንካራ ጎኖች ትማርባቸዋለህ፡፡ ከመንግስቱም የወስድኳቸው ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ልምምድ የማሰራት አቅሙ የሚገርም ነበር ፡፡
ደብሮም ሐጎስ
መንግስቱን የማውቀው ለዝግጅት ከመድን ጋር ወደ አዳማ በሄድኩበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ ሁለት ቡድኖች በእኔ ላይ ፍላጎት አሳይተው ነበር፡፡ ከሁለቱ ቡድኖች ለመምረጥ ከመወሰኔ በፊት አባቴን (ሀጎስ ደስታ) አናገርኩት፡፡ ‹‹በቀጥታ መንግሰቱ ጋር ሂድ፡፡ እሱ ይለውጥሃል፡፡ ስለ ገንዘብ ተውና በመንግስቱ የመሰልጠን ዕድልህን ተጠቀም፡፡›› አለኝ፡፡ መንግስቱ በአሰልጣኞችም ዘንድ ከፍተኛ እምነት የሚጣልበት ሰው ነበር፡፡ የእርሱ ታላቅነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ በጥቂት ጊዜ ቆይታዬም መንግስቱ የመሰለውን ፊት ለፊት የሚናገር ፣ ለእግርኳስ እጅግ ጥልቅ ስሜት ያለው ፣ የሚሰራውን ቡድን የሚያውቅ ፣ በተለይ ደግሞ በወጣቶች ላይ በደንብ የሚያምን እና ቡድን መገንባት የሚችል አሰልጣኝ እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ ስለ እውነት አስፈላጊውን ክብር ሳንሰጠው ያለፈብን ትልቅ ሰው እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ እስካሁንም የማዝነው እንደሱ ያሉትን ትልልቅ ባለሙያዎች እግርኳሱ እንዴት እንዳላሰባቸው እና ተገቢውን ክብር እንዳልሰጣቸው ሳይ ነው፡፡
እሱ ጋር ስሰራ በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ትልልቅ ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚጫወቱ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት መንግስቱ በዝግጅት ወቅት “ገና ልጅ ነህ::”ሲለኝ ወደ አየር መንገድ ሄድኩ፡፡ ወዲያውም ከአየር መንገድ ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ እርሱ ደግሞ የአሰልጣኝነት ኮርስ ለመስጠት ሌሶቶ ላይ ተገናኘን፡፡ ወዲያውኑ እርሱ ጋር ሄጄ ‹‹እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አንተ ጋር የሰራሁት ስራ ነው የጠቀመኝ፡፡ ለውጥም አምጥቼበታሁ፡፡ ›› አልኩት፡፡ በጣም ተገርሞ “በስልጠና ስራ ዘመኔ አይደለም እኔ ቀንሼው ስንት በጎ ነገር አድርጌለት እንኳ ያመሰገነኝ ተጫዋች ማንም የለም፡፡›› ነበር ያለኝ፡፡ በዚህም ላደረጉት ነገር ተገቢ ክብር እና ምስጋና እየተሰጣቸው እንዳልነበር ነው የተረዳሁት፡፡ ሁሌም ይህን ሳስብ አዝናለሁ፡፡
መንግስቱ የሚገርም ግርማ ሞገስ ነበረው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ጦር ኃይሎች አግኝቼ ሳናግረው ላብ በላብ ነው የሆንኩት፡፡፡ እንዲሁ አይተህ ክብር እንድትሰጠው የሚያስገድድ ሞገስ ነበረው፡፡ እንኳን ተናግሮህ እና አሰርቶህ በቅርብህ በመሆኑ ብቻ የምትፈራው እና የምታከብረው አሰልጣኝ ነበር፡፡ በወቀቱ በነበሩ ትልልቅ ተጫዋቾች ዘንድ የነበረው ከበሬታም አሁን ድረስ ያስገርመኛል፡፡
ለእግርኳስ የሚሰጠው ዋጋ ከፍተኛ ነበር፡፡ የመብራት ኃይል እና መድን ሜዳዎች እንዲሰሩ ያደረገው እርሱ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የአካዳሚ ስራ ላይ ራሱ ትልቅ እምነት ነበረው፡፡ አየር መንገድ እያለም መደበኛ የድርጅቱን ሰራተኞች ትኩረት ወደ እግርኳሱ ለማምጣት በማሰብ ልጆቻቸውን ያሰለጥን ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ(በ1980ዎቹ) በስታድየም የሚታዩ ጥሩ ጥሩ ጨዋታዎች የመንግስቱ የስልጠና አሻራዎች ነበሩባቸው፡፡ በዝግጅት ወቅት ጠንካራ ስራ በማሰራት ጥራት ያለው እግርኳስ እንድናሳይ ያግዘን ነበር፡፡ መንግስቱ ሙሉ የሚባል አሰልጣኝ ነበር፡፡ ለእግርኳስ ውበትም ያስባል፡፡ ስዩም አባተንም ተመልክቻለሁ፡፡ እንደ መንግስቱ የሚሆን ያለ አይመስለኝም፡፡ ውበት ላለው እግርኳስ የአካል ብቃት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነበረ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሜዲስን ቦል›› የሚባል ልምምድ ያሰራን ነበር፡፡ የእጅ ውርወራ ከጡንቻዎች ጥንካሬ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመረዳት ውርወራውን ከምታደርስበት ርቀት አንፃር መሆንን ያሳየን ነበር፡፡ መንግስቱ ትንንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ትልቅ ዋጋ ያላቸው ጉዳዮችን ትኩረት ይሰጣል።