የዝውውር ጭምጭምታዎች እና ዜናዎች


— የመከላከያው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በጦሩ ቤት እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል፡፡ ያለፉትን 2 የውድድር ዘመናት በመከላከያ ያሳለፉት ገብረመድህን ከዳሽን ቢራ ጋር ስማቸው ሲያያዝ ቢከርምም ለከርሞ መከላከያን ይዘው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

— አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ያሰናበተው ኢትዮጵያ መድን አንጋፋው አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባን ለመቅጠር ፍላጎት አሳይቷል፡፡ ጊዜያዊው አሰልጣኝ መሳይ በየነ እና ኢትዮጵያ መድን አብረው የመጓዛቸው ነገር አጠራጣሪ በመሆኑ አሰልጣኝ አባይነህ የወርቁ ምክትል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

— በተያያዘ መድን ተጫዋቾቹን የማጣት አደጋ ተደቅኖበታል፡፡ ዘንድሮ ጥሩ አቋም ያሳየው ተከላካዩ ወንድይፍራው ጌታሁን በደደቢት የሚፈለግ ሲሆን ብሩክ ጌታቸው እና ወሰኑ አሊ ወደ መከላከያ ሊያመሩ ይችላሉ፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ወደ መድን የተመለሰው መሃመድ ናስር በዱባይ ክለቦች ሙከራ ሲያደርግ ፣ ዳንኤል ደምሴ እና አብርሃም ሳኒ ደግሞ ወደ ሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከነማ አልያም ዳሽን ቢራ ሊዛወሩ ይችላሉ፡፡

— ደደቢት የአዳማ ከነማውን አጥቂ በረከት አዲሱን እንዳስፈረመ እየተነገረ ነው፡፡ የቀድሞው የባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ለፊርማው ከ800 እስከ 900 ሺህ ብር እንደተከፈለው ተነግሯል፡፡

— ወደ ንግድ ባንክ እንደተዛወረ ሲወራ የነበረው ፍሬው ሰለሞን የመከላከያ ኮንትራቱን ለማራዘም በድርድር ላይ ነው ተብሏል፡፡ መከላከያ ለፍሬው ኮንትራት ማራዘምያ ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

— ደደቢት የሁለቱን ጋናውያን ኮንትራት አራዝሟል፡፡ሰማያዊው ጦር ለ አዳሙ መሃመድ የ1 አመት ውል ማራዘምያ 400ሺህ ብር የከፈለ ሲሆን ለ ሻይቡ ጋብሬል ደግሞ ለ1 አመት 500 ሺህ ብር ከፍሏል፡፡

-ምንጭ – ፕላኔት ስፖርት (ኤፍኤም 96.3)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *