የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ወልድያ ላይ ሊካሄድ ታስቦ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ አአ ስታድየም ዞሮ ዛሬ በተደረገው ጨዋታ መቐለ ከተማ ወልዲያን 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።
ወልዲያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ግብ ከተለያየበት ጨዋታ የነበሩ የመጀመርያ 11 ተሰላፊዎችን ሳይቀይር ወደ ሜዳ ሲገባ በመቐለ ከተማ በኩል ተከላካዩ ዳንኤል አድሀኖም በኃይሉ ገ/ኢየሱስ እንዲሁም በጉዳት ምክንያት አጥቂው ጋይስ አፖንግን በመድሀኔ ታደሰ ተክቶ ገብቷል።
ከጨዋታው አስቀድሞ የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች በጋራ በመሆን ከምንም በላይ ስፖርታዊ ጨዋነት እናስቀድም የሚል ባነር በመያዝ መልክዕት በማስተላለፍ በህብረት በመሆን ፎቶ ተነስተዋል ።
ኢ/ዳኛ ብሩክ የማነህብርሀን በመሩት የዛሬው የ11 ሰአት የአአ ስታድየም ጨዋታ መቐለ ከተማ የማሸነፊያ ጎሉን እስካስቆጠረበት 33ኛው ደቂቃ ድረስ የረባ እንቅስቃሴ ያላየንበት ፣ የተደራጀ የማጥቃት ሽግግር በማድረግ የጎል ሙከራ እድል ያልተፈጠረበት ፣ ከሁለቱም ቡድኖች ብዛት ያላቸው ተጨዋቾች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሚናቸውን በአግባቡ ሳይወጡ የቀሩበት ነበር። በዚህ 33 ደቂቃ ውስጥ ይልቁንም የፀጥታ አካላት በወልዲያ ደጋፊዎች መካከል እርስ በእርስ የተፈጠረውን መጠነኛ ግጭት ለመቆጣጠር የወሰዱት አላስፈላጊ እርምጃ የተወሰኑ ደጋፊዎች ሜዳውን ለቀው ሲወጡ ሲያደርግ በተለይ አድማ በታኝ ፖሊሶች ወደ ሜዳ ሲገቡ ምንም ችግር ባልተፈጠረባቸው በሌሎች የስታድየሙ ክፍል የነበሩ ተመልካቾች ስታድየሙን ለቀው እነረዲወጡ በር ከፍቷል። በኋላም የፀጥታ ክፍል ሀላፊዎች በሰጡት አፋጣኝ ትዕዛዝ መሰረት አድማ በታኞቹ ከሜዳ በመውጣታቸው ጨዋታው እስከ ተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ሰላማዊ የሆነ ድጋፍ ሲያደርጉ አስተውለናል ።
በ33ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደስታ ያሻማውን የማዕዘን ምት በግርግር መሀል አንተነህ ገ/ክርስቶት እግር ስር ገብታ የመስመር ተከላካዩ በግራ እግሩ መሬት ለመሬት መትቶ መቐለን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት መቐለዎች በ42ኛው ደቂቃ ላይ በያሬድ ከበደ አማካኝነት ያገኙትን አጋጣሚ ግብ ጠባቂው ቤሊንጌ አድኖታል። የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በመቐለ 1 – 0 መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ በርከት ካለ የጎል ሙከራ ጋር ሲቀጥል ወልዲያዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት በ53ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ሸዋለም ከርቀት ሞክሮ ለጥቂት በወጣበት አጋጣሚ ነበር።
ወልዲያዎች የራሳቸውን የሜዳ ክፍል ለቀው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሲሸጋገሩ መቐለዎች በሚታወቁበት ጥብቅ መከላከል እምብዛም ክፍተት ያልሰጡ ሲሆን በሚፈጥሩት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግል ፍጥነቱ ታግዞ የሚፈጥረው አደጋ ለወልዲያ ተከላካዮች ፈታኝ ነበር። ለጎል የቀረበ ጠንካራ ሙከራ 61ኛው ደቂቃ ላይ ብቻውን ከሳጥን ውጭ ኳስ አግኝቶ ኳሱን ገፍቶ ይዞ ይገባል ሲባል ከርቀት መትቶ ቤሊንጌ ተፍቶ ያወጣበት አጋጣሚ እንዲሁም በ83ኛው ደቂቃ አለመረነሀ ግርማ ያመከነው የግብ አጋጣሚን ጨምሮ 89ኛው ደቂቃ።ላይ አማኑኤል የወልዲያ ተከላካዮችን በመቀነስ ብቻውን አገባ ሲባል የሳተው የማይታመን ኳስ መቐለን ከአንድ ጎል በላይ በማስቆጠር አሸንፎ የሚወጣበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
በወልድያዎች በኩል በአንድ ደቂቃ ልዩነት 73 እና 74ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገ/ማርያም እና ኤደም ኮድዞ ጎል ለማስቆጠር የፈጠሩት መልካም አጋጣሚዎች በተከላካዮቹ ተደርቦ ከወጣባቸው አጋጣሚዎች በቀር የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ታይተዋል። ወልዲያዎች ጨዋታውን ተረጋግተው የጎል እድል ለመፍጠር ከመጣር ይልቅ ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት መከተላቸው አንዳንድ ተጫዋቾች ለማስጠንቀቂያ ካርድ ሰላባ ከመሆናቸው ባሻገር ጨዋታው በዳኛ ፊሽካ በተቋረጠ ቁጥር ለተጋጣሚያቸው መቐለ የማገገሚያ ጊዜ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል .። ጨዋታውም በመቐለ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ መቐለ ከተማ ደረጃውን አሻሽሎ በ18 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ሲይዝ በአንፃሩ ወልድያ በያዘው 11 ነጥብ ደረጃውን ሳያሻሽል 12ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ተገዷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዮሐንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ
“የምንፈልገውን ውጤት ይዘን ወጥተናል። ይሄን ነበር የምንፈልገው። ትንሽ ጨዋታው ጥፋቶች የበዙበት ነበር ፤ ያንን ለዳኛው እንተዋለን። ከዛ ውጭ ግን ማግኘት የሚገባንን ውጤት ይዘን ወጥተናል።
“ስለፈረሙ የውጭ ተጨዋቾች አሁን መናገር አንፈልግም። ገና በሂደት ላይ ያለ ጉዳይ በመሆኑ አላለቀም። አዎ ተጨዋቾች እንፈልጋለን ገና ያላለቀ ስለ ሆነ እንዲህ ነው ብለን መናገር አንችልም። ”
ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልድያ
የተሳካ ወደ ጎል የሚያደርስ የኳስ ቁጥጥር አልነበረንም። በብዛት ወደ መስመር እንወጣ ነበር። ያ የተሳካ ሙከራ እንዳናደርግ ቢያደርገንም ከእረፍት መልስ ግን ተጭነነን ለመጫወት ሞክረን የተወሰኑ የማግባት አጋጣሚዎች ፈጥነን ነበር። ጎል ማስቆጠር ባለመቻላችን ተሸንፈን ወጥተናል።