በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው አመት ተሳትፎ ጠንካራ ፉክክር እያደረገ የሚገኘው መቐለ ከተማ ለ12 ተጫዋቾች ማስጠንቀቂያ አዘል ደብዳቤ መስጠቱ ታውቋል።
ክለቡ ለተጫዋቾች በሰጠው ደብዳቤ በእስካሁኑ የቡድኑ ጉዞ በጨዋታም ሆነ በልምምድ የተሰጣቸውን የስራ ድርሻ በአግባቡ ባለመወጣታቸው ፣ የአካል ብቃት ደረጃቸው ዝቅተኛ በመሆኑ የሚሰጣውን ታክቲክ ለመተግበር በመቸገራቸው እና ከጨዋታ ፍጥነት ጋር ያለመሄድ ችግር እንዳለባቸው ከዋናው አሰልጣኝ ሪፖርት እንደደረሰው በመግለፅ በፍጥነት እንዲያስተካክሉ አሳስበዋል። መቐለ ከተማ በዚህ ያህል ቁጥር ለተጫዋቾች ማስጠንቀቂያ መስጠቱ በሊጉ እምብዛም ያልተለመደ ተግባር መሆኑ ዜናውን አስገራሚ አድርጎታል።
ክለቡ ይፋ አያድርገው እንጂ በሁለተኛው ዙር ራሱን በተሻለ ሁኔታ ለማጠናከር ይረዳው ዘንድ ከሀገር ውስጥም ከውጭ ብዛት ያላቸውን ተጨዋቾች ለማምጣት በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተከትሎ ምን አልባትም ለ12 ተጫዋቾች ተፅፎ የተሰጠው ደብዳቤ የሚጠቁመው በቀጣይ በሁለተኛው ዙር ተጨዋቾቹ ራሳቸውን ማሻሻል ካልቻሉ ከክለቡ ጋር አብረው ላይ ላይዘልቁ ይችላሉ የሚለውን ግምት አጠናክሮታል።
መቐለ ከተማ እስካሁን ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ተሸንፎ በስድስት ጨዋታ አቻ በመውጣት አራት ጨዋታዎችን በድል አጠናቆ በ18 ነጥብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።