የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቶታል ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ዙር የሚዳኙ ዳኞችን ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያዊያን አርቢትሮችም በውድድሮቹ ላይ ጨዋታዎችን እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡
በቻምፒየንስ ሊጉ ቅድመ ማጣሪያ ዙር ዳሬ ሰላም ላይ የታንዛኒያው ሃያል ያንግ አፍሪካንስ ከሲሸልሱ ሴንት ሉዊ የሚያደርጉትን ጨዋታ በመሃል አርቢትርነት የሚመራው በላይ ታደሰ ነው፡፡ የበላይ ረዳት የሆኑት ትግል ግዛው እና ክንፈ ይልማ ሲሆኑ በአራተኛ ዳኛነት አማኑኤል ኃይለስላሴ ተመርጧል፡፡ በላይ የ2008 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምስጉን ዳኛ ሆኖ የተመረጠ ሲሆን በ2009 የአህጉሪቱ የክለብ ውድድሮች መምራትም ችሏል፡፡ ረዳቶቹ ትግል እና ክንፈም ቢሆን ለእንደዚህ ዓይነት ውድድሮች አዲስ አይደሉም፡፡ ትግል ኬንያ ባስተናገደችው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ላይ ከኢትዮጵያ የተመረጠ ብቸኛው አርቢትር ነበር፡፡ ያንጋ የማለፍ ከፍተኛ ቅድመ ግምት የተሰጠው ጨዋታ እሁድ የካቲት 4 ይደረጋል፡፡
በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ኪጋሊ ላይ የሩዋንዳው ኤፒአር እና የሲሸልሱ አንስ ሪዩኒየንስ የሚያስተናግድበት ጨዋታን ለሚ ንጉሴ በመሃል አርቢትርነት ይመራል፡፡ በረዳት ዳኝነት ተመስገን ሳሙኤል እና ክንዴ ሙሴ ሲገኙ በአራተኛ ዳኛነት ቴዎድሮስ ምትኩ ተሹመዋል፡፡ ለሚ፣ ተመስገን እና ክንዴ በኢንተርናሽናል አርቢትርነት የቆዩ በመሆናቸው በውድድሮቹ ላይ ሲሳተፉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ረዳት ዳኛ ተመስገን ከዚህ በፊት የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ በ2009 ተሳትፎ ማድርጉ የሚታወስ ነው፡፡ በ2010 የፊፋ ኢንተርናሽናል ከሆኑ ኢትዮጵያዊያን አርቢትሮች አንዱ የሆነው ቴዎድሮስ ጨዋታው ለመጀመሪያ ግዜ የኢንተርናሽናል ጨዋታው የሚሆን ይሆናል፡፡ ኤፒአር የተሻለ የማለፍ እድል የተሰጠው ጨዋታ እሁድ የካቲት 4 ይደረጋል፡፡
ካፍ የአርቢትሮችን ክፍያ በአባል ሃገራት በኩል የመክፈል አሰራሩን በማስቀረት ሃላፊነቱን ወደ ኮንፌድሬሽኑ ያዛወረው በያዝነው አመት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደምም እንደሚመራበት ሁሉ ካፍ የሃገራትን ቅርበት መሰረት አድርጎ አርቢትሮችን ለቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ሾሟል፡፡