ፋሲል ከተማ ክለቡን ከከፍተኛ ሊግ አንስቶ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ያደረጉት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስን ካሰናበተ በኋላ በረዳትነት ይሰሩ የነበሩት ምንተስኖት ጌጡን ጊዜያዊ የቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ ቆይቶ በዘንድሮ የውድድር አመት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ በይፋ መቅጠሩ ይታወሳል ።
አሰልጣኝ ምንተስኖት ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት መምራት በጀመሩበት የዘንድሮ የውድድር አመት ካደረጓቸው 11 ጨዋታዎች በሰባቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ ሦስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ መልከም የሚባል ጉዞ ቢያደርጉም በተስተካካይ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳቸው የተሸነፉበት እንዲሁም ትላንት ከደካማ አቋም ጋር በሲዳማ ቡና በሰፊ የግብ ልዩነት መሸነፉ የአሰልጣኙን መንበር አንቃንቆታል።
በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮዽያ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ምንተስኖት ከፋሲል ጋር ሊለያዩ ስለመሆኑ የሰሙት መረጃ እንደሌለ ተናግረዋል። ” ስለ ስንብቴ የማውቀው ምንም መረጃ የለኝም። የክለቡ አመራሮች ነገ 12:00 ላይ የአሰልጣኝ አባላቱን በሙሉ ስብሰባ ጠርተዋል። ከዚህ ውጭ የማውቀው ነገር የለም። ከሁሉም በላይ የሚቀድመው ፋሲል ከተማ ነው። የሚሆነውን እናያለን” ብለዋል።
ነገ የክለቡ አመራሮች በአሰልጣኙ የመቆየት አለመቆየት ዙርያ የሚወሰነው ውሳኔ የሚጠበቅ ቢሆንም አሰልጣኝ ምንተስኖት እና አፄዎቹ የመለያያ ጊዜያቸው መቅረቡ እየተነገረ ይገኛል።
ገና በ12 ሳምንታት ጉዞ ሰባት ክለቦች አሰልጣኝ በመቀየር ባልረጋጋው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይልቅ የአሰልጣኞች ሹም ሽር ትልቅ መነጋገሪያ እየሆነ ይገኛል።