​የአሰልጣኞች ገፅ | የመንግስቱ ወርቁ አሰልጣኝነት ዘመን [ክፍል 3]

ሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


በሁለት ክፍል መሰናዷችን አሰልጣኝ መንግስቱ በስራቸው ከመጀመርያ አመታት እስከ መጨረሻዎቹ ጊዜያት ድረስ በስራቸው ሰልጥነው ያለፉ እና በአሰልጣኝነትም አብረው የሰሩት አስራት ኃይሌ ፣ ስዩም ከበደ ፣ ንጉሴ ገብሬ ፣ ገብረመድህን ኃይሌ ፣ ወርቁ ደርገባ እና ደብሮም ሀጎስ ስለ መንግስቱ የአሰልጣኝነት ዘመን ያላቸውን ትውስታ አካፍለውን እንደነበር ይታወሳል። በክፍል ሶስት ደግሞ መንግስቱ ወርቁ በ1986 የኢትዮጵያ መድንን አስደናቂ የአፍሪካ ውድድር ጉዞ ተመርኩዞ በወጣው “መድን ኢንተርናሽናል” መፅሔት ላይ የሰጡትን ቃለመጠይቅ አቅርበንላችኋል።

በሁለት አጋጣሚዎች (ከ1980 እስከ 1982 እንዲሁም በ1992) የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ሆነው የሰሩት መንግስቱ ወርቁ ክለቡ በ1980ዎቹ ለነበረው ተወዳጅነት ትልቁን መሰረት የጣሉ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። በመድን የ1985-86 በካፍ ካፕ እስከ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰ አስደናቂ ጉዞ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ተጫዋቾችን ለትልቅ ደረጃ ያበቁትና በቡድን ግንባታ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን ያመነው መፅሔቱ ባደረገላቸው ቃለምልልስ ስለ አሰልጣኝነት፣ ስለ ተጫዋቾች፣ ስለ እግርኳስ ፍቅር፣ ስለ ተጫዋቾች እና አጠቃላይ እግርኳስን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ቆይታ አድርገዋል። እኛም ቃለ መጠይቁ ለአሰልጣኞች ገፅ አምዳችን በሚሆን መልኩ አሰናድተነዋል።

ስለ ወጣት/ታዳጊ ተጫዋቾች

በወጣቶች ላይ ያለኝ እምነት የፀና ነው፡፡ አንድ ተጫዋች በተቻለ መጠን እግርኳስን መጫወት መጀመር ያለበት ገና በልጅነቱ መሆን አለበት፡፡ እኛ አልታደልንም እንጂ በሰለጠኑት ሀገራት በ5 እና 6 ዓመታችው ከእግርኳስ ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ ደረጃ በደረጃ ተገቢው ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ በሕፃናቱ ችሎታ እና ፍላጎት ፣ በአሰልጣኞች ግምገማ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚደረግ ምክክር በየትምህርት ቤቶች እንዲሰለጥኑ ይደረጋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ  እንደውጪው አለም ባይሆን እኳን በሀገራችን ይህ መሞከር ይኖርበታል፡፡ እኔ መብራት ኃይል እና መድን እያለሁ እንደነ አብዲ ሰዒድ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ለማሰባሰብ ሥራዬ ብዬ ወደ ህፃናት አካባቢ ብዙ እመላለስ ነበር፡፡ በመጠኑም ቢሆን ተሳክቶልኛል እላለሁ፡፡ ከልጅነት የተጀመረ ኳስ ዘለቄታ ይኖረዋል፡፡ በሚገባ ለማረቅ እና ለማስተካከል ከአዋቂዎች ይልቅ የታዳጊዎች ሰውነት እና አዕምሮ የተመቸ ነው፡፡


ስለ ኢትዮጵያ መድን የአሰልጣኝነት ቆይታ

ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት በችሎታ (ስኪል) በወቅቱ በመድን ቡድን ውስጥ የነበሩት ተጫዋቾችን አደንቃለሁ፡፡ ነባሮቹን እና አዳዲስ ተጫዋቾችን በመያዝ ለሁለት ወር ያልተለመደ አይነት ዝግጅት ነበር ያደረግነው፡፡ ከመሰረታዊ የእግርኳስ ህግጋት አንስቶ እስከ ሥነ-ልቡና ትምህርት ድረስ ያካተተ ዝግጅት ነበር ያደረግነው፡፡ በአሰልጣኝነት ሙያዬ በከፍተኛ ደረጃ የደከምኩበት እና ያለኝን እውቅት በሙሉ ያፈሰስኩት በመድን ላይ ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ ያነሳሳኝም ተጫዋቾቹ ‹‹ድንግል መሬት›› ሆነው ስላገኘኋቸው ነበር፡፡ የምሰጣቸውን ስልጠና ለመቀበል ፍቃደኞች ከመሆናቸው በተጨማሪ ድርጅቱ ሙሉ ትብብር አድርጎልኛል፡፡ በልምምድ ፕሮግራሞች ላይ በርካታ ሰዎች እንደሚመሰክሩትም በፀሃይ እና ዝናብ ፣ ቁምጣ ለብሼ መርሃ-ግብር ሳላዛባ ተጫዋቾቹ በነበራቸው ስነምግባር እና ችሎታ ላይ ተጨማሪ ህንፃ ገንብቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ለመድን ያደረግኩት ትግል እና የደከምኩት ድካም በፍፁም አይቆጨኝም፡፡ ቡድኑ በነበረው የጨዋታ ስልት እረካ ነበር፡፡ መድን ‹‹ሀገር ቤት የተሰራ ብራዚል›› የተባለለት ቡድን ነበር፡፡ በእርግጥ ቡድኑ ችግሮች ነበሩበት ፤ በተለይ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ አልነበረውም፡፡ ሆኖም የታሰበውን ሲስተም በተግባር የሚያውል እጅ እና እግር ያለው ጨዋታ ይጫወት ነበር፡፡ የእንቅስቃሴው ይዘት እና ቅርፅ የሚለይ እንደነበር ቡድኑን የተታተሉ የእግርኳስ አዋቂዎች ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ በግል ክህሎትም ቡድኑ የያዛቸው ዓብይ፣ ሲራክ፣ ጌቱ፣ ደረጄ አብዲ እና አብርሃም የሚዘነጉ አይመስለኝም፡፡

መድንን ከሀገር ውስጥ አልፎ በአፍሪካ ታላላቅ ክለቦች ተርታ የማሰለፍ እቅድ ነበረኝ፡፡ ይሁንና ጥሩ ስራ መሰናክል ስለማያጣው ችግሮች አጋጥመውኛል፡፡ በተለይ ከውጪ የነበረው ግፊት ከባድ ነበር፡፡ ነገር ግን ያኔ ለመድን የጣልኩት መሰረት አሁን ቡድኑ ለደረሰበት ውጤታማነት እና ተወዳጅነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገ አምናለሁ፡፡ (ቃለመጠይቁ በ1986 እንደተደረገ ልብ ይሏል)

ስላሰለጠኗቸው ክለቦች ልዩነት

መብራት ኃይል እና መድን ተመሳሳይ አጨዋወት እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ ይህም የመጣው በቡድኖቻቸው ውስጥ የሚገኙት ተጫዋቾች ከልጅነታቸው አብረው ያደጉ በመሆናቸው ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ መሰረቱ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ የክለቡ ረጅም አመት እድሜ፣ ውጤቱ፣ በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ምርጥ ተጫዋቾች ብዛት ከሁለቱ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ የሀገራችን ክለቦችም ይለየዋል፡፡ ልዩነቶቹንም በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ለይቶ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

የመጀመርያው ቡድኑ ሁልጊዜም ትልልቅ ተጫዋቾች አሉት፡፡ ቡድኑ አቋሙ ቢወርድ እንኳን ተጫዋቾቹ በልምድ እና በስነ-ልቡና የበላይ ሆነው ስለሚታዩ በተደጋጋሚ ማሸነፋቸው የተለመደ ነው፡፡ እኔ በተጫዋችነት ዘመኔ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ ጎሎች አስቆጥሬያለሁ፡፡ እነፍስሐ ወልደ አማኑኤል፣ ሽዋንግዛው አጎናፍር፣ ጌታቸው አብዶ እና ጥበበ መንክር የመሳሰሉ ተጫዋቾች በየዘመናቱ ይህንን እያስቀጠሉ አሁን እነ አሸናፊ ሲሳይ ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡

ሁለተኛው የሌሎች ክለቦች ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያላቸውን አመለካከት ስንመለከት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚጫወቱ ቡድኖች ለጨዋታው የተለየ ግምት በመስጠት በውስጣቸው ያለውን ኃይል ይጨርሳሉ፡፡ ለምሳሌ በእኔ ተጫዋችነት ጊዜ እኔን ለመያዝ የተረገውን ልዩ ዝግጀት የማውቀው ጨዋታው በተጀመረ በጥቂት ደቂዎች ውስጥ ነው፡፡ ከዛም ያቀዱትን ስትራቴጂ በቀላሉ ሰብሬ ጎል አስቆጥር ነበር።

ጥሩ ተጫዋች ምን አይነት ነው?

ለእኔ ትክክለኛ ተጫዋች ማለት ለለበሰው ማልያ እስከመጨረሻ የሚታገል እና በመጨረሻም ውጤት የሚያስመዘግብ ሲሆን ነው፡፡ አንድ ተጫዋች ኳስን ማፍቀር አለበት፡፡ እንደ ልጅነት ፍቅር ማለት ነው፡፡ የልጅነት ጓደኛ ምንግዜም አይረሳም፡፡ በፍቅር እና ስነ-ስርዓት ያደገ ሰው በሚፈልገው የህይወት አቅጣጫ ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳል፡፡ ኳስ ማፍቀር ማለት ኳስን በተደጋጋሚ መጫወት ብቻ አይደለም፡፡ ውጤታማ ለመሆን እግርኳስ የሚጠይቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ኳስ መጠጥ ፣ ዝሙት ፣ ሲጋራ እና ሌሎች መጥፎ ባህርያትን አትፈልግም፡፡ ራስን መጠበቅ ፣ የልምምድ እና የእረፍት ፕሮግራምን ማክበር ፣ የአሰልጣኝን ምክር መቀበል እና ተግባራዊ ማድረግ ፣ ተመልካች እና የዳኛ ውሳኔን ማክበር ፣ ራስን ከአዳዲስ ነገሮች ጋር ማላመድ ትፈልጋለች፡፡ እነዚህን ሲያሟላ ነው አንድ ተጫዋች የኳስ ፍቅር አለው የሚባለው፡፡


ስለ አሰልጣኝነት እና ኢንስራክተርነት

ጥሩ አሰልጣኝ ለመሆን የተጫዋችነት ዘመኔን ብዙ ተምሬበታለሁ፡፡ ተጫዋችነት፣ አሰልጣኝነት እና ኢንስትራክተርነት የተያያዙ ስራዎች ናቸው፡፡ ሆኖም የአሰልጣኝነት ስራ ከባድ ነው፡፡ አሰልጣኝ ስትሆን በውስጥም በውጪም ከበርካታ አካላት ጋር ትገናኛለህ፡፡ በክለብ ደረጃ እነኳን ተጫዋቾች ፣ የቡድን መሪው ፣ ኮሚቴው፣ አስተዳደሩ፣ የአሰልጣኝ ቡድኑ፣ ወጌሻው ፣ ከውጪ ደግሞ ደጋፊው እና ሚድያው ይኖራሉ፡፡ አንድ አሰልጣኝ ከእነዚህ ሁሉ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያደርጋል፡፡ ሁሉም ወገኖች ውጤት ይፈልጋሉ፡፡ ውጤት ከተገኘ ተመስጋኙ ብዙ ነው፡፡ ውጤት ከጠፋ ግን የሁሉም ዓይን የሚያተኩረው በአሰልጣኙ ላይ ይሆናል፡፡ አሰልጣኙ ተሳስቷል የተባለባቸው ጉዳዮችም በየፈርጁ እየተለዩ እንዲኮነን ይደረጋል፡፡ የአሰልጣኝነት ስራ ክብደትን ለማብራራት አንዳደንድ ነጥቦችን መዳሰስ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

የምትይዛቸው ተጫዋቾች ከላይ እንደጠቀስኩት የኳስ ፍቅሩ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ እንዲኖራቸው ደግሞ የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መሰረት ተመጣጣኝ ክፍያ እና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ራሳቸውን ባሻሻሉ ቁጥር ለቡድናቸው ውጤታማነት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እየታየ እንክብካቤ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ይህን ለማድረግ እና ብቁ ተጫዋቾችን ለማውጣት ደግሞ ከቴክኒካል ስራዎች በላይ ብዙ ድካም ይጠይቃል፡፡ ሌላው ተጫዋቾች እንዳይከፋፈሉ እና በመሃላቸው ጥሩ መንፈስ የማድረግ ስራ ነው፡፡ ይህ ቀላል ሊመስል ቢችልም ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ አሰልጣኝ 6 ቁጥር የለበሰውን ተጫዋች ለተወሰነ ጨዋታ ባያሰልፈውና ሌላ ተጫዋች ቢተካ ቀሪዎቹ ቋሚ ተሰላፊዎች ከ6 ቁጥሩ ጋር የተለየ ግንኙነት ሊኖራቸው ስለሚችል ተክቶት የገባው ተጫዋች የማይችል መሆኑን ለማረጋገጥ ቡድኑን በሙሉ ሊገድሉት ይችላሉ ፤ እኔ ከልምድ ብዙ አይቻለሁ፡፡ አሰልጣኙ ይህንን እንዳይከሰት ለማድረግ ሁኔታውን ማስረዳት እና ማሳመን ይኖርበታል፡፡ በፕሮፌሽናል ደረጃ ይህ ላይሰራ ይችላል፡፡ ጃክ ገባ ፒተር እያንዳንዱ ተጫዋች የሚጫወተው ለህልውናው መሆኑን ስለሚረዳ እና ይህን ባያደርግ የሚመጣውን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው፡፡ በአማተር እግርኳስ ግን ችግሩ ይጎላል፡፡

የክለብ አስተዳዳሪዎች እና አሰልጣኙ በተመሳሳይ ቋንቋ ለመነጋገር ኃላፊዎቹ በስፖርት አለም ያሳለፉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ተግባብቶ ሥራን በትክክል መስራት ያዳግታል፡፡

በሌላ በኩል ደጋፊው ፣ ጋዜጠኛው እና ሌላውም ከአሰልጣኙ የዕለት ተዕለት ስራ ጋር በቀጥታ ባይገናኝም ለማሞገስም ሆነ ለመውቀስ ቅርብ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለውጤት መጥፋት ምክያቶችን በቅርበት ሆነው ስለማያውቁ በይበልጥ አሰልጣኝ ላይ ትችት መሰንዘር ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡

እኔ አሰልጣኝ ሆኜ በቀጣዩ ቀን ጨዋታ ካለብኝ ተኝቼ ማደር እቸገር ነበር፡፡ ሁሉም ነገሮች በአዕምሮዬ ስለሚመላለሱ ትልቅ ጭንቀት ነበረብኝ፡፡ እንግዲህ እግርኳስ የቡድን ስፖርት በመሆኑ የአሰልጣኞች የስራ ሁኔታ ጠለቅ ስለሚል ውስብስብ እና ከባድ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በአሰልጣኝነት ዘመኔ ከምገናኛቸው ሁሉም ወገኖች ጋር መሠረታዊ ቅራኔ ውስጥ ገብቻለሁ ብዬ አላምንም፡፡ ይልቁንም ስላደረጉልኝ ትብብር አመሰግናለሁ፡፡

ከእግርኳሱ አካባቢ ውጪ አሰልጣኝ የመሆን ተግዳሮት የቤተሰብ ህይወት ነው። አሰልጣኝነት በባህሪው ከቤተሰብ ጋር ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ያፋልሳል፡፡ እኔ በአሰልጣኝኘት ዘመኔ ልጆቼ ምን እንደሚበሉ እንኳን ተመልክቼ አላውቅም ነበር፡፡

ወደ አሰልጣኞች አሰልጣኝነት (ኢንስትራክተር) ስመጣ እኔ ይህን ደረጃ ያገኘሁት ህዝብ ስለሚወደኝ ወይም ስሜ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለካፍ ስለተላለፈ አይደለም፡፡ (መንግስቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያው የካፍ ኢንስራክተር ነበሩ) እዚህ ለመድረድስ ብዙ ሰርቻለሁ፡፡ በሀገር ውስጥ አሰልጣኝነት ያካበትኩት ልምድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በወሰድኳቸው ከፍተኛ ትምህርቶች ሁሉ ብልጫ ያለው ውጤት በማስመዝገቤም ጭምር ነው፡፡ እዚህ ላይ የካፍ ኢንስትራክተር ሆኖ መመረጡ ብዙ ደረጃዎችን ማለፍ የማስፈለጉን ያህል ይህን ኃላፊነት ጠብቆ መቆየት ደግሞ ሌላው ብቃትን የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ የኢንስትራክተርነት ስራዬን በብቃት እየተወጣሁ እንዳለሁ ምስክሩ ካፍ ነው፡፡ ናይጄርያን ለምሳሌ እንውሰድ ፤ ናይጄርያ ከአፍሪካ ሀገራት በእግርኳስ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ አንድ በኳስ ኋላ ከቀረች ሀገር መምህር ተመድቦላት እንዲሰለጥኑ ሲደረግ ለመቀበል ጥርጣሬ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ በኋላ ግን የትምህርቱን አሰጣጥ እና ደረጃ ገምግመው ያበረከቱልኝን የምስጋና ሽልማት አልረሳውም፡፡

የመድን ተጫዋቾች በግል ህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ስለማገዝ

የመድን ተጫዋቾችን እንደወለድኳቸው ልጆቼ ነበር የምመለከታቸው፡፡ ቡድኑን በማሰልጠን ላይ እያለሁ ከተጫዋቾቼ ጋር በተናጠልም ሆነ በጋራ ውይይት እናደርጋለን፡፡ ብዙዎቹ ተጫዋቾች ከወደፊት ኑሯቸው ጋር በማያያዝ አማክረውኛል፡፡ እኔም ሁኔታውን በመረዳት የድርጅቱን ማኔጅመንት ተጫዋቾቹ የሽያጭ ሰራተኛ ሆነው ቢመደቡ የተሻለ እንደሆነ አስረድቼ ተፈቀደላቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች የሽያጭ ሰራተኛ በመሆን ከመደበኛ ደሞዛቸው ተጨማሪ 200 ብር አበል በአዲሱ ስራቸው ማግኘት ጀመሩ፡፡ ዕረፍት በሚሆኑበት ጊዜ ወደተመደቡበት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመሔድ ስራቸውን ይለማመዱ ነበር፡፡ መክብብ ፣ ደረጄ ፣ ዓለማየሁ ፣ ሲራክ ፣ ነጋሽ እና የመሳሰሉት ተራ በተራ ከኳስ አለም ሲገለሉ ወደ መደበኛ ስራቸው ተመልሰዋል፡፡ አሁን ደሞዛቸው ከፍተኛ መሆኑን ስሰማ ያስደስተኛል፡፡ ያን ጊዜ የተጣለው መሠረት አሁንም በመጫወት ላይ ለሚገኙ ተጫዋቾች ማነቃቂያ ሊሆን ይችላል፡፡


ልዩ አድናቆት የሚሰጡት ተጫዋች

ዐብይ ነጋሽ በተፈጥሮው ካገኘው ፀጋ በተጨማሪ በጨዋታ ባካበተው ልምድ ልዩ ችሎታ የያዘ ተጫዋች ነው፡፡ በሁለት እግሮቹ በእኩል ደረጃ መጫወት የሚችል ፣ ወደ ግብ የሚመታቸው ኳሶች ትክክለኛነት እና ጥንካሬ ፣ የቦታ አያያዝ እና አሸፋፈኑ ፣ ኳስ ቁጥጥሩ… በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ እኔ የአውሮፓ ተጫዋች ነበር የሚመስለኝ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች እግርኳስን ማፍቀሩን ተወና ጨዋታው ሁሉ ተበላሽቶበት አቆመ እንጂ እስካሁን ከማውቃቸው የአዲሱ ትውልድ ተጫዋቾች መካከል ቅድሚያውን የምሰጠው ለዐብይ ነው፡፡ በእርግጥ ሌሎች ሊጠቀሱ የሚገባቸው ተጫዋቾች አሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የነበራቸው ችሎታ የተሟላ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ በግብ የማስቆጠር ችሎታቸው ጥሩ ይሆናሉ፡፡ ሌላው የጠንካራ ምቶች ባለቤት ይሆናል ፤ ሌሎቹ ደግሞ የኳስ ቁጥጥር እና የማቀበል ችሎታ ብቻ ይኖራቸዋል፡፡ ዐብይ ግን የተሟላ ተጨዋች ነበር፡፡ በተለይ በሁለት እግሩ በእኩል ሁኔታ መጫወቱ ያስደንቀኝ ነበር፡፡ ቢያውቅበት ኖሮ ኢትዮጵያዊው ፔሌ መባል ደረጃ ይደርስ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡

ስለ ክቡር  ይድነቃቸው ተሰማ

ጋሼ ይድነቃቸው በአፍሪካ የእግርኳስ ታሪክ ለዛለለሙ ሲወደስ የሚኖር የአፍሪካ ልጅ ነው፡፡ በሚሄድባቸው የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ስሙ ህያው ነው፡፡ ከእሱ ጋር የነበረኝ ቀረቤታ የተለየ ታሪክ ያለው በመሆኑ እዚህ ላይ የግል ግንኙነታችንን ማንሳት አልፈልግም፡፡ ጋሼ ይድነቃቸው በእኛ ጊዜ ለነበሩት ተጫዋቾች በሙሉ ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ እሱ በሚያሰለጥንበት ወቅት ከ3ኛው – 6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጊዜ የነበርነውን ተጫዋቾች ‹‹ በታሪክ አጋጣሚ የተሰባሰቡ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች ›› ማለትን ያዘወትር ነበር፡፡

በአንድ ወቅት የመብራት ኃይል አሰልጣኝ ሆኜ በአጋጣሚ ፌዴሬሽን አካባቢ ተገናኘን ፤ በወቅቱ ቡድኔ ውጤቱ ደከም ያለበት ጊዜ ነበር፡፡ ‹‹ መንግስቱ – ምነው መብራቱ ወደኋላ ያበራል፡፡ ›› አለኝ፡፡ በአነጋገሩ በጣም ብደነቅም የነበረኝን አንዳንድ ችግሮች ገለፅኩለት፡፡ ቀጥሎም ‹‹ ቅመሳት፣ አሰልጣኝነት ቀላል ስራ እንዳይመስልህ፡፡ ከአሁኑ ቀበቶህን ጠበቅ አድርገህ ስራ፡፡ ›› በማለት ተሰናበተኝ፡፡ ከዛ እለት ጀምሮ እሱን ምክር በመጠየቅ ሥራዬን ለማሸነፍ ለፍቻለሁ፡፡ ለእኔ እዚህ መድረስ ብዙ ረድቶኛል፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ በ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካለፍን በኋላ ሊቢያ ላይ የመጀመርያውን ጨዋታ በናይጄርያ 3-0 ተሸነፍን፡፡ በማግስቱ ጠዋት 11፡00 ላይ የመኝታ ቤቴ በር ተንኳኩቶ ከፍቼ ስመለከት ጋሼ ይድነቃቸው በር ላይ ቆሟል፡፡ ጋሼ በጧቱ … አልኩት። ‹‹ ለቅሶ የሚደረሰው በጠዋት አይደለም እንዴ? ›› ብሎ እኔኑ ጠየቀኝ፡፡ በጊዜው በጣም ደንግጬ ማን ሞተ አልኩት። ‹‹ በል ለማንኛውም በሌሎቹ ጨዋታዎች እባካችሁ በርቱ፡፡ በዚህ ዓይነት አልጄርያዎች 8-9 ጎል ነው የሚያስቆጥሩት፡፡ ›› በማለት ወደ ጨዋታው ጉዳይ መለሰኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *