የኢትዮጵያ ከ17 እና 20 አመት በታች ውድድሮች በሳምንቱ መጨረሻ ተጀምረዋል። የወደፊቱን የሀገሪቱ እግርኳስ እጣፈንታን የሚወስኑ ተጫዋቾች የሚገኙበት እነዚህ ሊጎች በተለያዩ ምክንያቶች ከአመት አመት የሚሰጣቸው ትኩረት እና ክብደት እየቀነሰ መጥቶ ስለ ውድድሩ መኖር የሚያውቁ ግለሰቦች እና መገናኛ ብዙሀን እምብዛም ሆነዋል። ይህም የእግርኳሳችን መፃኢ ጊዜ ለሚያሳስበው ሁሉ መልካም ዜና አይደለም።
ውድድሩ ትኩረት እንዲያጣ ገፊ ከሚሆኑ እጅግ በርካታ ምክንያቶች ዋንኛው ከእነዚህ ውድድሮች የሚፈልቁ ተጫዋቾች ፕሪምየር ሊጉን ጨምሮ በሀገሪቱ ትልልቅ የእግርኳስ መድረኮች የመጫወት እድል አለማግኘታቸው ከውድድሩ የሚገኘውን ጥቅም እና የመደረግ ፋይዳውን ማሳነሱ ነው። ጥቅም የሌለውን እግርኳስ ማን ትኩረት ይሰጠዋል?
ያሳለፍነውን ክረምት የዝውውር ዕብደት ያስተዋለ ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ ውስጥ ወጣት ተጫዋቾችን ማየት ህልም ሆኖ እንደቀሚቀር ቢያስብ አይፈረድበትም።
ከምንጊዜውም በተለየ ክለቦቻችን ገበያ ወጥተው ሚሊዮኖችን እያፈሰሱ ለአመታት በተለያዩ ማልያዎች ስንመለከታቸው የቆዩ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ ተመልክተናል። ይህ ባህል ያልነበራቸው ክለቦች እንኳን ዋና ተዋናይ ሆነው ማየት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር። ተስፋ ማስቆረጡ የሚያይለው ደግሞ ወትሮም ቢሆን ለይስሙላ ከሁለተኛ ቡድን አደጉ ተብለው በተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ እጣ ፈንታቸው ለሆነው ወጣቶች ነበር። እንደውም በሌላ መንገድ ሲታሰብ ከታዳጊ ቡድኖች ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ከእግር ኳስ እንደመራቅ ይቆጠራል። በሁለተኛ ቡድን ሳለ በየጨዋታው ላይ በመሳተፍ አቅሙን ሲያሳይ የቆየ ተጫዋች ዋናውን ቡድን ተቀላቅሎ ወደ ተመልካችነት ሲቀየር የተጫዋቹ የእግር ኳስ ህይወት አደገ ከማለት ይልቅ አበቃለት ማለት ይቀላል። በየክለቡ አንጋፋዎቹ ተጫዋቾች ተጎድተው አልያም በሌላ ምክንያት ወጣቶቹ የመሰለፍ ዕድል አግኝተው ውጤት ከጠፋ የአሰልጣኞች ሰበብ ድርደራ ማጠናከሪያ መሆናቸው ነው። “.. እንዳያችሁት ወጣቶችን ነው የተጠቀምነው። ልምድ የላቸውም። ..የስኳድ ጥበት አለብን። .. በሂደት እናሻሻላለን” የሚሉ አስተያየቶች ስንሰማ ከርመዋል። ሂደቱን ሳንፈጥረው እንዴት ሆኖ ነው ተጨዋቾቹ የስኬታችን ፊት አውራሪ የሚሆኑት ? በአደባባይ በእነርሱ ላይ ያለን እምነት የወረደ መሆኑን እየተናገርንስ እንዴት ሆኖ ነው የማሸነፍ ስነልቦናቸው ሊያድግ የሚችለው?
በእርግጥ የዘንድሮው ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር እየተገባደደ ባለበት ወቅት ላይ እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልሱ ጥቂት ምልክቶችን እያየን እንገኛለን። ችግር በቅቤ ያስበላል እንዲሉ በዝውውሩ ላይ መሳተፍ ያልቻሉ እና ተሳትፈውም በርካታ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ያጡ ቡድኖች ለአዳዲስ ፊቶች ዕድል መስጠት ጀምረዋል። ከነዚህ መሀል ግንባር ቀደሞቹ ደደቢት እና አዳማ ከተማ ደግሞ ከመሪዎቹ ጎራ መሰለፍ ችለዋል።
በዝውውር መስኮቱ ፋሲካ አስፋውን ብቻ ያስፈረመው ደደቢት ስድስት ጨዋታዎችን በተከታታይ ሲያሸንፍ አምና በተቀያሪ ወንበር ላይ ያሳለፉት የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ እንዲሁም በውሰት ተሰጥተው የነበሩት አቤል ያለው እና አለምአንተ ካሳ አሰተዋፅኦ አድርገዋል። በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊዎች ለመሆን በቅተዋል። ምን አልባት አምና የተሻለ ዕድል ሲያገኝ ከነበረው አቤል እንዳለ ውጪ የተቀሩት ክለቡ በርካታ ተጨዋቾችን አስፈርሞ ቢሆን ኖሮ በተጠባባቂነትም ባልተመለከትናቸው ነበር። ሆኖም ያ ሳይሆን ቀርቶ የአቤል ያለውን ፍጥነት እና ግብ አስቆጣሪነት እንዲሁም የያብስራ ተስፋዬ እና የአቤል እንዳለ የሰመረ የአማካይ ክፍል ጥምረት ተከትሎ ክለቡ ስኬታማ ጉዞን በማድረግ ላይ ይገኛል። ሰባት የሚደርሱ ተጨዋቾችን ካስፈረመ በኃላ ኢስማኤል ሳንጋሪን ብቻ በቋሚነት እየተጠቀመ የሚገኘው አዳማ ከተማ ደረጃውን ሲያሻሽል ግብ በማስቆጠር እና በቡድኑ አጨዋወት ላይ ወሳኙን ሚና በመጫወት ከፊት የተሰለፉት ዳዋ ሁቴሳ ፣ በረከት ደስታ ፣ ሱሌይማን ሰሚድ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም ቡልቻ ሹራ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ተጫዋቾች በራሳቸው ከጉዳት ጋር እየተጋሉ መሆኑ እንጂ ሙሉ የጤንነት ደረጃ ላይ ሆነው ከሳምንት ሳምንት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ቢካተቱ አዳማ ከዚህም በላይ ነጥቦችን በሰበሰበ ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተስፋዬ በቀለ ፣ የመከላከያው አቤል ከበደ ፣ የሲዳማ ቡናዎቹ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ሐብታሙ ገዛሀኝ ፣ የአርባምንጭ ከተማው ብርሀኑ አዳሙ እና የድሬዳዋው ዘካርያስ ፍቅሬም እየተሰጣቸው ባለው ዕድል ተስፋ እያሳዩ ያሉ ተጫዋቾች ናቸው። ባሳለፍናቸው ሁለት የውድድር አመታት ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ጎልተው የወጡት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቡበከር ሳኒ ፣ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ ፣ የመቐለ ከተማው አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና የሀዋሳ ከተማው መሳይ ጳውሎስን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ደግሞ አሁንም እድገታቸው ቀጥሎ የየክለቦቻቸው የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋች መሆናቸውን ገፍተውበታል።
ሆኖም ትልቁ ስጋት የሚሆነው አንጋፋዎቹ ተጫዋቾች ከጉዳት ሲመለሱ ወይንም ክለቦቹ በተለመደው የስኳድ ጥበት ሰበብ መነሻነት የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን ወይም ሌሎች አንጋፋ ኢትዮጵያዊያንን ማስፈረም ቢጀምሩ እየተሰጣቸው ያለው ዕድል ይቀጥል ይሆን ? አሰልጣኞቻችንስ እነዚህ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ስህተቶችን ቢሰሩ እንኳን አሻሽለዋቸው ዕድገታቸው እንዲቀጥል ያደርጋሉ ወይስ ወደተለመደው ተጠባባቂነት ያወርዷቸዋል? ከክለብ ባሻገር ስንመለከት ደግሞ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በተለምዶ ልምድን ሰበብ አድርጎ ለአመታት የተመለከትናቸውን ተጨዋቾች ከመምረጥ ባለፈ ቡድኑን በእነዚህ ተጫዋቾች ላይ አመዝኖ ይሰራል ወይ? የሚለው ጉዳይ መታየት ይኖርበታል። እነዚህ ጥያቄዎች ወጣቶቹን በሚጠቅም መልኩ ካልተመለሱ የአንድ ሰሞን ትዝታ ሆነው መቅረታቸው አይቀርም። ለዚህም ከማንም በላይ የየክለቦቹ አሰልጣኞች ኃላፊነት እጅግ ከፍተኛ ነው።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚታየው ቀርፋፋ የጨዋታ ፍጥነት እና ፍላጎት አልባ እንቅስቃሴ በዋነኝነት በየክለቡ ከሚገኙ ተጫዋቾች እድሜ መግፋት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው። የነባር ተጫዋቾች ልምድ እንዳለ ሆኖ በወጣት ተጫዋቾች ላይ የሚታየው የጨዋታ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ሲታከልበት ደግሞ ለእግርኳሳችን የሚጨምሩት ነገሮች በርካታ ናቸው።
ወጣት ተጫዋቾች ወደ ስኬት የመጓዝ ፍላጎታቸውን ተከትሎ የሚያሳዩት ታታሪነት በልምምድ ወቅት ከአሰልጣኞች የሚመጣን ሀሳብ ተቀብሎ ደጋግሞ በትጋት በመስራት እንዲሁም በጨዋታ ወቅት ትዕዛዞችን ተቀብሎ ለመተግበር ከፍተኛ ተነሳሽነትን በማሳየት በኩል ዕድል ተነፍጓቸው የቆዩቱን ወጣቶች ያህል ማንም አይኖርም። የሚና ለውጦችን ለማድረግም እነዚህ ተጫዋቾች ምቹ ናቸው። ለማደግ ያላቸው ፍላጎት የተሰጣቸው ቦታ ላይ ሁሉ አቅማቸውን አውጥተው አሰልጣኞቻቸውን ለማስደሰት መሞከራቸው አይቀሬ ነው። እዚህ ላይ በመስመር ተከላካይነት እና በመስመር አጥቂነት እየተጫወተ የሚገኘው ሱሌይማን ሰሚድን ፣ ከተከላካይ እስከ አጥቂ አማካይነት ሲሰለፍ ያየነው የአብስራ ተስፋዬን ፣ በፊት አጥቂነት እና በመስመር አማካይነት የሚያገለግለው በረከት ደስታን እና በተለያዩ የአማካይ መስመር ሚናዎች ላይ የተመለከትነውን አቤል እንዳለን በምሳሌነት ማንሳት እንችላለን። ከዚህ በተጨማሪ ወጣት ተጨዋቾች በቡድናቸው ውስጥ በተካተቱ ቁጥር አሰልጣኞች የሚመርጡት አጨዋወት በፍጥነት የተሞላ እና ጉልበት ያለው እንደሚሆን ግልፅ ነው። ተጫዋቾቹ ያላቸው ቅልጥፍና እና የጨዋታ ፍላጎትም ከኳስ ውጪ በሚደረግ እንቅስቃሴ ተጋጣሚን አፍኖ ኳስ ለመቀማትም ምቹ ያደርጋቸዋል። በአጠቃላይ አሰልጣኞች የሚቀርፅጿቸው ስትራቴጂዎች በሜዳ ላይ በአግባቡ እንዲተገበሩ አስፈላጊ የሆኑ አካላዊ እና ዐዕምሯዊ ቅድመ ሁኔታዎች በአግባቡ ተሟልተው የሚገኙት እነዚህ ወጣት ተጫዋቾች ጋር ነው።
ከላይ የተጠቀሱት ከወጣት ተጫዋቾች የሚገኙ ትሩፋቶችን ለማግኘት ግን በአዳዲስ ፊቶች ላይ ያለንን አመለካከት ፣ አሰራር እና እምነት መቀየር ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ እግር ኳሱን የሚያስተዳድረው አካል ጉዳዩ ሊያሳስበው ይገባል። የሀገር እግር ኳስ እድገት ተወደደም ተጠላም በወጣቶች ላይ የተመሰረተ ነው። የነገው ብሔራዊ ቡድን በወጣቶች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ክለቦች ለታዳጊዎቹ ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያስገድዱ ህጎችን ማውጣት እና ተፈፃሚነታቸውንም በጥብቅ መከታታል ከፌዴሬሽኑ የሚጠበቅ ነው። በዚህም በክለቦቹ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በአስገዳጅነት በአካዳሚዎች ላይ እንዲሰሩ ማስገደድ ፣ ከውጪ በሚያስፈርሟቸው ተጨዋቾች ቁጥር ዕኩል ከወጣት ቡድኑ የማሳደግ ግዴታ እንዲኖርባቸው ማድረግን ሊያካትት ይገባል። ማሳደጋቸው ብቻ ሳይሆን በአመት ውስጥ ሊያገኙ የሚገባቸው አስተኛው የደቂቃ መጠንም መካተት ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ ከ20 እና 17 አመት በታች ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ታዳጊ ተጫዋቾች በየትኛውም ጊዜ ለዋና ቡድኖች ሲጠሩ የመጫወት ፍቃድ እንዲራቸው ማድረግም ወሳኝ ነጥብ ነው።
ሌላው የአሰልጣኞቻችን ጉዳይ ነው። አሰልጣኞች በነዚህ ተጫዋቾች ላይ የሚኖራቸው እምነት ለእግር ኳስ ህይወታቸው ዕድገት ወሳኝ ነው። ከዕድሜያቸውም አንፃር እምነት አሳድሮ ኃላፊነት የሚሰጣቸው ደፋር አሰልጣኝ ሲያገኙ መሻሻላቸው የማይቀር ነው። ይህን ለማድረግ ግን በአሰልጣኞች በኩል ከፍተኛ ድፍረት እና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። አሰልጣኞች የክለብ አመራሮችን እና የሲኒየር ተጨዋቾችን ከባድ ተፅዕኖ በመቋቋም ለወጣት ተጨዋቾች ዕድል ቢሰጡ ለስራቸው ውጤታማነት የሚኖራቸው ድርሻ ከፍተኛ እንደሚሆን የሰሞኑ የሊጉ ሁኔታ በቂ ምስክር ነው። ከዚህ ባለፈ የዋና ቡድን አሰልጣኞች ከታዳጊ ቡድኖች አሰልጣኞች እንዲሁም ቴክኒክ ዳይሪክተሮች ጋር በየጊዜው እየተገናኙ የታዳጊዎችን ወቅታዊ አቋም እየገመገሙ ዕድል ሊያገኙ የሚገባቸውን ልጆች ወደ ዋናው ቡድን በማቅረብ በልምምዶች እና ጨዋታዎች ላይ እያሳተፉ እድገታቸው እንዲቀጥል መስራት ይኖርባቸዋል። ይህ እንዲሆን ግን የየክለቡ አመራሮች ጊዚያው ውጤትን ከመሻት ይልቅ የማልያ ፍቅርም የሰረፀባቸውን እና ክለቡን ለረዥም ጊዜ የሚያገለግሉ ብቁ ተጨዋቾችን ለማፍራት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል። በዚህ አይነት መልኩ ለመጓዝ የሚያስቡ አሰልጣኞች ሲኖሩም በቂ ጊዜ በመስጠት በትዕግስት አብረዋቸው ሊሰሩ ግድ ይላል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሚዲያው ኃላፊነት መረሳት አይገባውም። በተለይ የወጣቶች እና የታዳጊዎችን ውድድሮች ሽፋን በመስጠት ነጥረው የሚወጡ ተጫዋቾችን ደግሞ ከእግር ኳስ እና ከክለቦች ጋር የማስተዋወቅ ስራ ከሚዲያዎች ይጠበቃል። ወጣት ተጫዋቾች በጨዋታ ላይ ስህተት ሲሰሩ እንዲሁም ከአንዳንድ አሰልጣኞች የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ሲደርሳቸው በተቃውሞ ድምፅን ከማሰማት ይልቅ የልጆቹን ስነልቦና በጠበቀ መልኩ ነገ ለሚኖራቸው የእግር ኳስ ህይወት መቃናት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት።