ያለፉትን አመታት ከህመማቸው ጋር እየታገሉ የሚገኙት አንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም አባተ ከሰሞኑ ህመማቸው አገርሽቶ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያቀኑ ሲሆን ያለፉትን ሦስት ቀናት በልዩ የህክምና ክትትል ክፍል ውስጥ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው አሁንም እዛው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስምንተኛ ፎቅ በአልጋ ላይ ተኝተው እንደሚገኙ ሰምተናል።
የአሰልጣኝ ስዩም ወቅታዊ ሁኔታንን አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጡን ከወንድማቸው አሰልጣኝ ሰለሞን አባተ ጋር ሶከር ኢትዮዽያ ባደረገችው አጭር ቆይታ “አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። ያለፉትን ሁለት ሦስት ቀናት ጥሩ አልነበረም። ክፉኛ ታሞ አይሲ ክፍል ውስጥ ነበር። ትላንት ከሰአት በኋላ ወደ አልጋ ክፍል ሄዷል። አሁን ከህመሙ እያገገመ ይገኛል” ብለዋል።
በኢትዮዽያ እግርኳስ ታሪክ በተጨዋችነት እና አሰልጣኝነት ከ50 አመታት በላይ የቆዩት አንጋፋው የእግርኳስ ሰው ጤንነታቸው በተሟላ ሁኔታ እንዲመለስ ሶከር ኢትዮጵያ ትመኛለች።