በሳምንቱ አጋማሽ በተስተካከለው መርሀ ግብር መሰረት ሊጉ ዛሬ በሶዶ ፣ ድሬደዋ እና ሀዋሳ ላይ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች የሚቀጥል ይሆናል። እነዚህን ጨዋታዎችም እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።
ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ የመሀል ዳኝነት የሚካሄደው ይህ ጨዋታ ሁለት ጥሩ መንፈስ ላይ ያሉ ቡድኖች የሚገናኙበት ይሆናል። ምንም እንኳን በመሀከላቸው የሰባት ነጥቦች ርቀት ቢኖርም ወላይታ ድቻም ሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት አራት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን ማሳካት ችለዋል። ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስንብት በኃላ የነበረበትን የመጨረሻ ደረጃ ትቶ ወደ ዘጠነኛነት ከፍ ማለት የቻለው ወላይታ ድቻ ከሁለተኛው ሳምንት በኃላ ከድል ርቆ ቢሰነብትም በሜዳው ያደረጋቸውን የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል። ይህም ዛሬ በሜዳው ለሚያደርገው ጨዋታ የሞራል ስንቅ እንደሚሆነው ይጠበቃል። ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ከቻለም ውጤቱ ሶዶ ላይ የሚያስመዘግበው ሶስተኛ ተከታታይ ድል ሆኖ ደረጃውን እንዲያሻሽል የሚረዳው ይሆናል። እስካሁን ምንም ሽንፈት ያልገጠማቸው ሻምፒዮኖቹ ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማን 2-0 የረቱበት ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ግብ ሳያስቆጥሩ ከተመለሱባቸው የወልዋሎ እና የወልድያ ጨዋታዎች በኃላ ሶስት ነጥቦችን ያሳኩበት ነበር። ይህ በመሆኑም አንድ ጭማሪ ጨዋታ ካደረገው መሪው ደደቢት ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት አምስት ብቻ እንዲሆን አስችሏቸዋል። ዛሬ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጉትን ጨዋታ ማሸነፍ ደግሞ ይበልጥ ወደ መሪዎቹ የሚያስጠጋቸው ይሆናል። አምና 22ኛ ሳምንት ላይ ሲገናኙ ነጥብ 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተው የተለያዩት ዘንድሮ ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ የሚወክሉት ቡድኖች በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ላይ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለድል መሆን መቻሉ የሚታወስ ነው።
ባለሜዳው ወላይታ ድቻ በዛሬው ጨዋታ እርቅይሁን ተስፋዬን ፣ ፀጋዬ ብርሀኑን እና አመረላህ ደልታታን በጉዳት እንዲሁም ተስፉ ኤልያስን በቅጣት የማያሰልፍ ይሆናል። ቀላል ልምምድ የጀመሩትን የረዥም ጊዜ ጉዳት ያጋጠማቸው ሳላዲን ሰይድ ፣ አሜ መሀመድ ፣ ታደለ መንገሻን እና ናትናኤል ዘለቀን የማይጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አበባው ቡታቆን ከቀላል ጉዳት መልስ የሚያገኝ ሲሆን አዳነ ግርማ ግን አለማገገሙን ሰምተናል።
ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ወደ ሀላፊነት መምጣት በኃላ ወላይታ ድቻ በብዙ መልኩ ተቀይሯል። ለአመታት በሶስት ተከላካዮች የሚጀምረው አሰላለፉ ወደ አራት ተከላካዮች ሲቀየር አማካይ ክፍል ላይም የሚና ለውጦች ታይተውበታል። ከኃይማኖት ወርቁ ጎን በመሆን ለተከላካይ ክፍሉ ቀርቦ ይጫወት የነበረው አብዱልሰመድ አሊ ወደፊት የተጠጋ ሚና ለቡድኑ ተጨማሪ የማጥቃት ኃይል ሲሆነው እየታየ ነው። በመከላከሉም በኩል በሀይማኖት ወርቁ እና በፊት አጥቂው ጃኮ አራፋት መሀል የሚገኙት አራት አማካዮች በተለይ ኳስ ተቆጣጥረው የሚጫወቱ ቡድኖችን አማካይ ክፍል አፍኖ በማስቀረት የሚሰነዘርባቸው ጥቃት እስከ ተከላካይ መስመራቸው ድረስ እንዳይዘልቅ የሚያደርጉትም ጥረት የተሳካ ሆኖ ታይቷል። ይህ ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት ለቡድኑ ውጤት እገዛ ማድረጉን ተከትሎም በዛሬውም ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይገመታል። ድቻዎች የተጨዋቾች የግል ብቃት መሻሻልም ለውጤታቸው መቃናት ትልቅ አስተዋፅኦ ኖሮታል። የግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመው ጥሩ አቋም ላይ መገኘት ከአማካዮቹ አብዱልሰመድ ዓሊ እና ዳግም በቀለ ግብ አስቆጣሪነት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው። እንደ ወላይታ ድቻ ሁሉ ከኳስ ውጪ በሚኖር እንቅስቃሴ ተጋጣሚን ጫና ውስጥ የመክተት አቀራረብ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ሲተገበር ይታያል። ሆኖም ሻምፒዮኖቹ ይህን የጨዋታ ባህሪያቸው የሚነፀባረቀው በፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው ነው። በአቡበከር ሳኒ ፍጥነት እና ታታሪነት የሚመራው የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር የተጋጣሚ የተከላካይ መስመር ኳስን ተረጋግቶ እንዳይጀምር በማድረግ እንዲሁም ለስህተት በመዳረግ ከሚገኙ አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎች መፍጠርን እየተጠቀመበት ይገኛል። በፋሲል ከተማው ጨዋታ የቡድኑ ትልቅ ጥንካሬም ይህ ነበር። ከሮበርት ኦድንካራ ጀምሮ ያለው የቡድኑ ይመከላከል ብርታትም እንደ በሀይሉ አሰፋ ካሉ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች እገዛ ጋር ተዳምሮ ግብ የማይቆጠርበት እና ጨዋታዎችን በብልጠት የሚያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስን እያሳየን ይገኛል። ይህ ጠንካራ ጎኑ ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎች ብልጫ ቢወሰድበት እንኳን ውጤት ይዞ ለመውጣት እንዳይቸገር አድርጎታል። ይህ የቡድኑ ባህሪ በዛሬው ጨዋታ ላይም እንደሚነፀባረቅ ሲጠበቅ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የድቻን የተከላካይ መስመር የሚያስጨነቅ የአጥቂ ክፍል እንዲሁም በባለሜዳዎቹ በኩል የፈረሰኞቹን አማካዮች ሰው በሰው በመያዝ እና ከኳስ ውጪ ጫና ውስጥ በመክተት ኳስ ለመንጠቅ የሚሞክር የአማካይ ክፍል የሚታይበት ጨዋታ ይሆናል።
ድሬደዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በ12ኛው ሳምንት በተላለፉት ጨዋታዎች ሳቢያ የሁለት ሳምንታት ዕረፍት ያገኙት ድሬደዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከውጤት ተራርቀው ከቆዩ ክለቦች መሀል ተጠቃሽ ናቸው። አምና 22ኛው ሳምንት ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ሜዳው ላይ አስተናግዶ 3-1 ማሸነፍ ችሎ የነበረው ድሬደዋ ከተማ በመጀመሪያ ጨዋታው ጅማ አባ ጅፋርን ካሸነፈ በኃላ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያሳካበት ጨዋታ የለም። እስከ ስድስተኛው ሳምንት በአቻ ውጤቶች ሲጓዝ ከቆየ በኃላም ሁለት ሽንፈቶች ሲገጥሙት ሜዳው ላይ ከፋሲል ከተማ እና ሲዳማ ቡና ባደረጋቸው ጨዋታዎች ነጥብ መጋራት ችሏል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡናም ያለበት ሁኔታ የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም። ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ሲሆን ዘንድሮ ከሜዳው በወጣባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አንድም ነጥብ ማግኘት አልቻለም። ዛሬ 10፡00 ላይ በፌደራል ዳኛ አማኑኤል ወ/ፃዲቅ መሪነት የሚደረገው ጨዋታም ሁለቱ ክለቦች ካሉበት የውጤት ቀውስ ለማገገም እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ድሬደዋ ከተማ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከተቀመጠበት የወራጅ ቀጠና በጥቂቱም ቢሆን ከፍ ማለት የሚችል ሲሆን ውጤቱ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሚሄድ ከሆነ ደግሞ ቡናማዎቹ ካሉበት የ11ኛ ደረጃ ወደ ስምንት ከፍ ማለት የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። ጨዋታው በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ግን ቡድኖቹ ካሉበት ሁኔታ አንፃር በደረጃ ሰንጠረዡም ሆነ በወቅታዊ ሁኔታቸው ላይ የሚያሻሽለው ነገር ባለመኖሩ ሁለቱም ተጠቃሚ አይሆኑም።
ሳምሶን አሰፋ ፣ ዘነበ ከበደ እና ሀብታሙ ወልዴ በድሬደዋ በኩል ለረዥም ጊዜ ከሜዳ እንደራቁ የሚታወቅ ሲሆን ሳውሪል ኦልሪሽ ደግሞ በመጠነኛ ጉዳት ከዚህ ጨዋታ ውጭ ሆኗል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ አክሊሉ አያናው እና አለማየው ሙለታ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ወደ ጨዋታ ያልተመለሱ ሲሆን ቶማስ ስምረቱ ግን ከቡድኑ ጋር ወደ ድሬደዋ ማምራቱ ተሰምቷል።
እያሳለፉት ከሚገኙት ደካማ ጊዜ አንፃር ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ ብርቱ ፉክክሩ የሚያደርጉበት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል። ድሬደዋ ከተማ በአሰልጣኝ ስምኦን አባይ ስር ሆኖ ለመከላከል ከሚሰጠው ትኩረት ይልቅ ማጥቃትን መሰረት እያደረገ ወደ ሜዳ መግባት ቢጀምርም ወደ ውጤታማነት መምጣት ግን አልቻለም። ለተከላካይ መስመሩ እጅግ ቀበርው ይታዩ ከነበሩት የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ውስጥ ከኢማኑኤል ላርያ ፊት የሚገኙትን ሶስት አማካዮች ለሁለቱ አጥቂዎች ቀርበው እንዲጫወቱ በማድረግ ለቀቅ ያለ አቀራረብን መከተል የጀመረው ድሬደዋ በርካታ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር አሁንም ብዙ ይቀረዋል። ሆኖም ቡድኑ ሲከተለው ከቆየው በጥንቃቄ የተሞላ አጨዋወት በፍጥነት በየጨዋታው ውጤታማ የማጥቃት ሂደትን የሚተገብር ቡድን መገንባት አስቸገሪ ቢሆንም የአጨዋወቱ መስተካከል በራሱ አንዱ ስኬት ሆኖ ይታያል። ኢትዮጵያ ቡናም ቢሆን የመጨረሻ ዕድሎችን ከፈጠረ በኃላ ወደ ግብ የመቀየር ችግሩ እንዲሁም በመከላከሉ የተሻለ የመሀል ሜዳ ጥንካሬ ከተላበሱ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ እና ቁልፍ የሚበሉ አማካዮቹ ማርክ ሲደረጉ ደግሞ ጭራሽ ዕድሎችንም ለመፍጠር ሲቸገር ይታያል። ሆኖም ቡድኖቹ በ12ኛው ሳምንት በተላለፉት ጨዋታዎች ምክንያት ባገኙት የዕረፍት ጊዜ እነዚህን ችግሮቻቸውን ለማስተካከል የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ይታመናል። ከዚህ ውጪ ግን የኢትዮጽያ ቡና አማካዮች በተለይም ኤልያስ ማሞ ከኢማኑኤል ላርያ ጎን እና ጀርባ ባሉት ቦታዎች ላይ መገኘት እና የድሬ ቀሪዎቹ የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች ደግሞ ይህን ክፍተት ለመድፈን የሚያደርጉት ጥረት በጨዋታው ተጠባቂ ፉክክር ይሆናል። በአሰልጣኝ ስምኦን አባይ ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው እንደ ዘላለም ኢሳያስ እና ሱራፌል ዳንኤል አይነት ተጨዋቾችም የኢትዮጽያ ቡና ደካማ ጎን የሆነውን ከተከላካይ መስመሩ ፊት ያለውን ቦታ የሚጠቀሙበት አግባብም ለባለሜዳዎቹ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ
ባሳለፍነው አመት የሊጉ ሁለተኛ ሳምንት መርሀ ግብር ላይ ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ሀዋሳ ከተማ በፍሬው ሰለሞን ሁለት ግቦች በመታገዝ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሎ ነበር። የቡድኑ ይህ ድልም እስከ 13ኛው ሳምንት ድረስ ብቸኛው ሆኖ ነበር የዘለቀው። ዘንድሮ 13ኛው ሳምንት ላይ ሲገናኙ ደግሞ ሀዋሳ ከተማ ከአምናው የተሻለ ጥሩ በሚባል መልኩ ሊጉን ቢጀምርም በውጤት እየተንሸራተተ ባለበት ሰዐት ነው አርባምንጭን የሚያስተናግደው። በሜዳቸው አይበገሬ ሆነው ሙሉ ነጥቦችን ሲሰበስቡ የቆዩት ሀዋሳዎች ከሜዳ ውጪ የነበራቸውን ደካማ ሪከርድ በመጠኑ ማሻሻል ሲጀምሩ የሜዳቸው ጥንካሬ ደግሞ በአቻ ውጤቶች ተተክቷል። ፋሲል ከተማን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያስተናገዱባቸው የመጨረሻ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት የተገደዱባቸውም ነበሩ። ከተጋጣሚው በተለየ መልኩ ሜዳው ላይም ሆነ ከሜዳው ውጪ ውጤት ርቆት እና በበርካታ ሹም ሽሮች መሀል ሆኖ አምስት ጨዋታዎችን በመደዳ የተሸነፈው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ መጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አበቃለት ሲባል ሳምንት አዳማ ከተማን ሳይጠበቅ በማሸነፍ አስገራሚ ውጤት አስመዝግቧል። በርግጥ ድሉ የደረጃ ለውጥ ባያመጣለትም በወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኙት ሌሎች ክለቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬደዋ ከተማ ጋር በነጥብ ያስተካከለው በመሆኑ ቡድኑ ከዛሬው የደቡብ ደርቢ በፊት የተሻለ የአዕምሮ ጥንካሬ ላይ እንዲገኝ የሚያስችለው ነው። በፌደራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በሚመራው ጨዋታ ላይም ሁለቱም ቡድኖች አሸንፈው ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚፋለሙበት ብቻም ሳይሆን ሀዋሳ በሜዳው ወደነበረው ጥንካሬ መመለስን እንዲሁም አርባምንጭ የሳምንቱን ድል ለማስቀጠል የሚያልሙበትም ጭምር ነው።
በሀዋሳ ከተማ በኩል ከጉዳት መልስ መጠነኛ ልምምድ የጀመሩት ዳንኤል ደርቤ እና ላውረንስ ላርቴን ጨምሮ ያቡን ዊሊያም ፣ ሳዲቅ ሴቾ እና ተክለማርያም ሻንቆ ለጨዋታው የማይደርሱ ሲሆን ሶስት ጨዋታዎችን የተቀጣው ፍሬው ሰለሞንንም በቅጣት ሲያጣ በአንፃሩ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከቅጣት ይመለሳል፡፡ የወንደሰን ሚልኪያስንን እና ወንድሜነህ ዘሪሁንን አገልግልግሎት በጉዳት ሳቢያ የማያገኘው አርባምንጭ በበኩሉ ገ/ሚካኤል ያዕቆብን ደግሞ በቅጣት የሚያጣ ይሆናል።
በተጨዋቾቻቸው ተነሳሽነት መውረድ ሳቢያ ማስጠንቀቂያ የሰጡት ሁለቱ ቡድኖች በጉዳዩ በቅርበት መከሰት ምክንትያ በሜዳ ላይ ምን አይነት መንፈስ ያለው ቡድን ይዘው እንደሚቀርቡ ተጠባቂ ሆኗል። በይበልጥ ይህ ጉዳይ ለሀዋሳ ከተማ አጨዋወት ችግር እየፈጠረበት ያለ ይመስላል። በየጨዋታው የኳስ ቁጥጥርን የበላይነትን በማሳካት በተጋጣሚዎቹ ጅርባ ለመግባት የሚጥረው ሀዋሳ ተገማችነቱን ለመቀነስ ተጨዋቾቹ በሙሉ የተነሳሽነት ደረጃ ላይ መገኘት በዕጅጉ አስፈላጊ ነው። በርከት ያሉ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎችን ከሚጠቀሙ እንደ አርባምንጭ አይነት ተጋጣሚዎች ደግሞ ይህን ፈተናውን ይበልጥ ያከብዱታል። በመሆኑም ቡድኑ ወደ ማጥቃት በሚሸጋገርባቸው ቅፅበቶች ከኳስ ውጪ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የተጋጣሚን የመከላከል ቅርፅ ለመበተን እና ክፍተቶችን ለማግኘት የሚሞክርበት አኳኃን ስኬታማ መሆን ይጠበቅበታል። አሰልጣኝ እዮብ ማለ ስር የመጀመሪያ ጨዋታውን ማሸነፍ የቻለው አርባምንጭ የተከላካይ መስመር ላይ ይጠቀምበት የነበረው ተመስገን ካስትሮን ወደ ፊት አጥቂነት ሚና አምጥቷል ። ተጨዋቹ በዚህ ቦታ ላይ ሲዳማ ቡናን ከመቀላቀሉ በፊት በነበረው የአርባምንጭ ቆይታው ወቅት ይጫወት የነበረ ሲሆን በአዳማው ጨዋታ ላይም ጥሩ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል። የዛሬው ፍልሚያ አምና አርባምንጭ ጥሩ የሊግ ጉዞ ባደረገበት ወቅት የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ የነበረው የምንተስኖት አበራ እና አማኑኤል ጎበና ጥምረትም ከረዥም ጊዜ በኃላ ዳግም የሚታይበትም ጨዋታም ይሆናል። አማኑኤል ሳምንት ወደ አንድ አመት የሚጠጋ ጊዜ ከሜዳ ካራቀው ጉዳቱ ተመልሶ ቡድኑ አዳማን እንዲያሸንፍ ሲረዳ ምንተስኖት በአምስት ቢጫዎች ምክንያት በቅጣት መሰለፍ አልቻለም ነበር። የሁለቱ ተጨዋቾች ዳግም መገናኘት ለአሰልጣኝ እዮብ ጥሩ ዜና ቢሆንም ጠንካራ የአማካይ ክፍል ካለው ሀዋሳ ከተማ ጋር በሚረደገው ጨዋታ ምን ያህል የበፊቱ ውህደታቸው ዳግም በስኬት ሊታይ ይችላል የሚለው ጥያቄ ሆኖ ይነሳል።