ወንድሜነህ አይናለም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የውድድር አመቱን እያሳለፈ ይገኛል። ከርቀት በሚያስቆጥራቸው ኳሶች የሚታወቀው የሲዳማ ቡና አማካይ ባለፈው ሳምንት ፋሲል ከተማ ላይ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አንደኛዋ ጎል ከርቀት በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ነበረች።
ትውልዱ በጂንካ ከተማ የሆነው ወንድሜነህ በከተማው በሚገኝ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ታቅፎ ባሳየው ፈጣን እድገት የደቡብ ኦሞ ዞንን በመወከል ዲላ ላይ በ2004 በተደረገ ውድድር ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ይህንን ተከትሎም ወደ ብሔራዊ ሊጉ ክለብ ጂንካ ማምራት ችሏል። ከሁለት አመታት ቆይታ በኋላም ምርጥ የውድድር አመታት ወዳሳለፈበት ደቡብ ፖሊስ አምርቷል። ወንድሜነህ በተለይ በደቡብ ፖሊስ ሁለተኛ አመት ቆይታው ከአማካይ ስፍራ በመነሳት 20 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በእግርኳስ ህይወቱ አስደሳቹን ጊዜ ያሳለፈበት ክለብ እንደሆነ ይናገራል።
“የደቡብ ፓሊስ ቆይታዬ በጣም ጥሩ የሆንኩበት እና በርካታ ግቦችን ያስቆጠርኩበት በመሆኑ የሚረሳ አይደለም። ከርቀት በምመታቸው ኳሶች በርካታ ግብን አስቆጥሬያለሁ። ከዛም ባለፈ ከቅጣት ምት ጎሎችን ማስቆጠር ችያለሁ። በ2008 በደቡብ ፓሊስ ያስቆጠርኩት ጎል 18 ሲባል እሰማለሁ። ሆኖም ያስቆጠርኩት 20 ጎል ነበር። አሜ መሐመድ በአንድ ግብ ብቻ በልጦኝ ነበር ያጠናቀቀው። ”
ከአማካይ ቦታ በመነሳት በርካታ ጎል ማስቆጠር ባልተለመደበት የኢትዮጵያ እግርኳስ ግብ አዳኝ መሆን የቻለው ወንድሜነህ በፖሊስ ያሳየው ግሩም አቋም ወደሌላኛው የከተማው ክለብ ሀዋሳ ከተማ አሻግሮታል። በውቧ ከተማ ህይወት የተደላደለ ያልሆነችለት ወንድሜነህ በጉዳት እና የመሰለፍ እድል ባለማግኘት ምክንያት በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሰልፎ ተጫውቷል። ክለቡን የተቀላቀለው በሁለት አመታት ኮንትራት ቢሆንም በክረምቱ የዝውውር መስኮት ውሉን አፍርሶ የሀዋሳ ጎረቤት ወደሆነው ሲዳማ ቡና አምርቷል።
” በሀዋሳ እንዳሰብኩት መሆን አልቻልኩም። ሁለት አመት ነበር የፈረምኩት ፤ ነገር ግን በተደጋጋሚ እድሎችን አላገኘሁም። እንደመጣው ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። ከዛ ባገግምም ያሰብኩት ሊሆንልኝ አልቻለም። ከከፍተኛ ሊግ እንደመምጣቴ ሊጉን ልለምድ አልቻልኩም ነበር። በጊዜ ሂደት ግን በሊጉ ጥሩ ብቃትን አሳያለሁ ብዬ ባስብም ያ ሊሆን ባለመቻሉ እና ከአሰልጣኙ ጋር የነበረኝ ግንኙነትም ጥሩ ስላልሆነ ሀዋሳ ከተማ ውል እያለብኝ ልለያይ ችያለሁ። በጊዜው በቡድኑ ነባር ተጫዋቾች በመኖራቸው በኔ ላይ እምነት ማጣታቸው እንጂ ከኔ የተሻሉ ተጫዋቾች ኖረው አይደለም። ያ መሆኑ ግን የተለየ ነገር አልፈጠረብኝም፡፡”
በክረምቱ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ያጣው ሲዳማ ቡና ቀጣይ የወንድሜነህ ማረፍያ ነበር። በሀዋሳ ያጣውን የመሰለፍ እድል በሲዳማ እያገኘ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ 3 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በሲዳማ ቡና ደስተኛ እንደሆነ እና ቡድኑም እየተሻመለ እንደሆነ ይናገራል። ” ሲዳማ ቡና በጣም ጥሩ ቡድን ነው። የቡድን ህብረታችን መልካም ነው። በውህደት ችገር አጀማመራችን መጥፎ ቢሆንም በሂደት ግን በጋራ በመስራታችን ክለቡ ካለበት ደረጃ ወጥቶ በጥሩ ፎርም ላይ ይገኛል። በውስጣችንም ፍቅር ስላለ ይህን ተከታታይ ውጤት ማምጣት ችሏል። በግሌ በሚሰጠኝ እድልም እጅግ ደስተኛ ነኝ።
” በክለቡ እስካለሁ ድረስ ቡድኑን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ እፈልጋለሁ። ለዋንጫ መፎካከር የሚያስችል አቅም አለን። ያን ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን። አሁን ላይ ወገብ ላይ ነን ፤ በርግጠኝነት በአንደኛው ዙር ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘን እናጠናቅቃለን። ”
ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ከመጥፎ አጀማመሩ በመውጣት ወራጅ ቀጠናውን ተላቆ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ እንዲጠጋ አስዋፅእ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ወንድሜነህ ነው። በፈጣን የመስመር ተጫዋቾቹ ላይ ጥገኛ በሆነው የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ወንድሜነህ ከርቀት አክርሮ የሚመታቸው ጠንካራ ሙከራዎች ለግብ ጠባቂዎች ፈተና ከመሆኑ በተጨማሪ ለቡድኑ ተጨማሪ የማጥቃት መሳርያ ሆነዋል። እንደ ወንድሜነህ እምነት የጠንካራ ምቶቹ ምስጢር የተደጋጋሚ ልምምድ ውጤት ነው።
” ከርቀት በምመታቸው ምቶች ላይ በተለየ ሁኔታ በልጅነቴ ትኩረት አድርጌ እሰራ ነበር። አሰልጣኜ ከሚያሰራኝ እና ከመደበኛ የልምምድ መርሀ ግብሮች በተጨማሪ ራሴ ባዶ ጎል ላይ እየመታው እለማመድ ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜያት በሜዳም ላይ እሞክር ነበር። ያ ጥረቴ አድጎ ነው ዛሬ ላለሁበት ደረጃ እና መለያዬ ለማድረግ የበቃሁት። ከርቀት ማስቆጠሬ በረጅም ጊዜ ያዳበርኩት የግል ልምምዴ ውጤት ነው ብዬ ማስቀመጥ እችላለሁ። ”
ወንድሜነህ ከመጣበት አካባቢ አንፃር በሊጉ መጫወት መቻሉ ትልቅ ስሜት ፈጥሮበታል። የእሱ ትልቅ ደረጃ መድረስም ለአካባቢው ወጣቶች ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥርም ያምናል።
” እውነት ለመናገር እዚህ እደርሳለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። እግር ኳስን በቅርብ ነው የጀመርኩት። እስካሁን የተጓዝኩበት መንገድም ጥሩ ነው። ታታሪ ነኝ ፤ የመጣሁበት ቦታም አውቃለሁ። ከደቡብ ኦሞ ጂንካ በፕሪምየር ሊጉ የምጫወተው እኔ ብቻ ነኝ። ስለዚህም አካባቢውንም ሆነ ራሴን ለማስጠራት እጥራለሁ። የእኔን ፈለግ ተከትለው በርካታ ተጫዋቾች እንዲወጡ የግሌን ጥረት አድርጋለሁ፡፡ አሁን ላይ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በታችኛው የሊግ እርከን ላይ መጫወት ጀምረዋል። ጂንካ ከተማም በአንደኛ ሊግ እየተሳተፈ ይገኛል። ከዚህ በመነሳት እነዚህን ለመርዳት እና በግሌ ደግሞ በሲዳማ ቡናና ቋሚነቴን አስጠብቄ የብሔራዊ ቡድን ማልያን የመልበስ ፍላጎት አለኝ። እዛ ላይ ለመድረስ ግን በጣም ገና ነኝ። ጥቂቷን ብቻ ነው የሰራሁት። በቀጣይ ጠንክሮ መስራትም ይጠበቅብኛል፡፡ ”
በትልቅ ደረጃ ለመጫወት የልጅነት አሰልጣኙ መድብል ለገሰን የሚያመሰግነው ወንድሜነህ ከጎኑ ለነበሩ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል።
” ከልጅነት ጀምሮ እኔን ሲያሰለጥነኝ የነበረው አሰልጣኝ መድብል ለገሰ (አሁን አሜሪካ ይገኛል) ለእግር ኳስ ህይወቴ እዚህ ለመድረሴ ትልቅ ቦታ አላቸው። በአንድ ወቅትም የጂንካ ከተማ አሰልጣኝ በመሆንም ሰርቷል። አሁን ላለሁበት የእግር ኳስ ህይወቴ ከፍተኛውን ሚና የሚወስደው እሱ ነው። በተጫዋችነት ዘመኑ ግብ ጠባቂ የነበረ ቢሆንም እያየሁ ያደኩት እሱን ነበር። ከሱ በፊት ተጫውተው ሳላሳለፉት ጠንክር እና አዳነ የሚባሉ ተጫዋቾች እየነገረኝ ያበረታኝ ነበር። ያንንም በመስማት እና ተግባራዊ በማድረግ ነው እድገቴን የጀመርኩት። ከጎኔም በመሆን የት መድረስ እንደምችል ይገለፅልኝ ነበር። ሌላው እዚህ እንድደርስ ለረዱኝ እና ላበረታቱኝ የመላው የደበብ ኦሞ ዞን ህዝብ እየደወሁ ለሚያበረታቱኝ በሙሉ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፡፡ “