ትናንት በተካሄዱ ሶስት ጨዋታዎች የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬም ሶስት ጨዋታዎች ይስተናገዱበታል ። አዳማ ፣ ጎንደር እና መቐለ ላይ በ9፡00 የሚጀምሩትን እነዚህን ጨዋታዎች በዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።
አዳማ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
በሊጉ ኢትዮ ኤሌክትሪክን እና ኢትዮጵያ ቡናን በተከታታይ የመሸነፍ ተመሳሳይነት ያሳዩት አዳማ እና ወልዋሎ ከእነዚህ ድሎች በኃላ ውጤት የቀናቸው አይመስልም። ባለፉት አመታት በነበረው ደረጃ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ መቆየት ያልቻለው አዳማ ከተማ አርባምንጭ ላይ ከገጠመው ሽንፈት በኃላ ዛሬ ወልዋሎን ያስተናግዳል። አዳማ ሁለቱ ክለቦች ላይ ካስመዘገበው ውጤት በኃላ ነበር የአርባምንጩ ሽንፈትን የገጠመው። ወልዋሎም ጥሩ አቋም ባሳየበት የመጀመሪያ ወር ሁለቱን የመዲናዋን ክለቦች ማሸነፍ ቢችልም ከዛ በኃላ ግን ከድል ጋር ተራርቆ ሰባት ሳምንታትን አሳልፏል። ይህን ተከትሎም ባሳለፍነው ሳምንት አሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚያብሄር ጋር መለያየቱ የሚታወስ ነው። ዛሬ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ክለቦቹ በፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ የመሀል ዳኝነት ሲገናኙም ባለሜዳዎቹ ዳግም ከመሪዎቹ ጋር ለመጠጋጋት እንዲሁም ወልዋሎዎች ወደ አሸናፊነት በመመለስ ከወራጅ ቀጠናው ርቆ ለመቀመጥ የሚፋለሙበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
የአዳማ ከተማዎቹ ሚካኤል ጆርጅ ፣ በረከት ደስታ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ጃኮ ፔንዜ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽም መጠነኛ ህመም ስለገጠማቸው ቡድናቸውን ላይመሩ የሚችሉበት ዕድል አለ። በወልዋሎ ዓዲግራት በኩል ለጨዋታው የማይደርሰው ደግሞ ጉዳት የገጠመው የፊት አጥቂው ሙሉአለም ጥላሁን ነው።
አዳማ ከተማ አሁንም ሙሉ ስብስቡን ከጉዳት ነፃ ማድረግ አለመቻሉ ትክክለኛውን አቀራረቡን ለመለየት እንድንቸገር አድርጓል። ለቡድኑ ውጤት ወጥ አለመሆንም ይህ ችግሩ ግንባር ቀደም ምክንያት ሆኖታል። ሆኖም የተሻለ ወጥነት ያለው የኃላ ክፍሉ ውጤቱ ከዚህም በላይ እንዳይወርድ አስተዋፅዖ አድርጓል። በተደጋጋሚ ጉዳቶች የሚጠቃው ከወገብ በላይ ያለው የቡድኑ ክፍል ግን ለአዳማ የማጥቃት አቀራረብ መለያየት እና እንደ ዳዋ ሁቴሳ ባሉ አጥቂዎች ወቅታዊ ብቃት ላይ መረኮዝን ተከትሎ ተጋማችነቱን ቢቀንሰውም በወጥነቱ ላይ ድክመት እንዲኖር ማድረጉ ግን አልቀረም። በዚህ የተነሳም በዛሬውም ጨዋታ ቡድኑ በሚጠቀመው የትኛውም የማጥቃት አማራጭ ሀላፊነት የሚሰጣቸው ተጨዋቾች የግል ጥረት ወሳኝነት ይኖረዋል። በምክትል አሰልጣኙ ሀፍቶም ኪሮስ እየተመራ ወደ ሜዳ የሚገባው ወልዋሎ ዓ.ዩ ከሜዳው ውጪም የሚከተለው ለቀቅ ያለ እና በራሱ አጨዋወት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ ለተከታታይ ሽንፈቶች ሲዳርገው ቆይቷል። በመሆኑም ምንአልባት አሰልጣኝ ብርሀኔ ከቡድኑ ከተለያዩ በኃላ በሚደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ የተወሰነ ጥንቃቄን የተላበሰ ቡድን ሊያስመለክተን ይችላል። ይህም የመስመር አጥቂዎቹ እና የመሀል አማካዮቹ ቡድኑ ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ወቅት በብቸኛው የተከላካይ አማካይ ግራ እና ቀኝ የሚኖሩ ክፍተቶችን በቶሎ በመዝጋት እንደነ ከንአን ማርክነህ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ያሉ የባለሜዳዎቹ አማካዬች በቅብብል ከፊት አጥቂዎቹ ጋር እንዳይገናኙ እገዛ ሊያደርግ ይችላል። ወልዋሎም በሜዳው ከማይቀመሰው አዳማ ጋር በሚኖረው ፍልሚያ እንደ ወላይታ ድቻ እና አርባምንጭ ከተማ ሁሉ ከአሰልጣኝ ለውጥ በኃላ በፍጥነት ወደ ውጤት ይመለሳል ወይ የሚለው ጥያቄ የሚመለስበት ፉክክር በጨዋታው እንደሚስተናገድ ይጠበቃል።
ፋሲል ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
አምና ጎንደር ላይ በ8ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀግብር 0-0 የተለያዩት ፋሲል ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዛሬ በውጤት ቀውስ ውስጥ ሆነው ፌደራል ዳኛ ሳህሉ ይርጋ በሚመራው ጨዋታ እርስ በእርስ የሚገናኙ ይሆናል። ፋሲል ከተማ ከአስር ተከታታይ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ በኃላ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና አምስት ግቦችን አስተናግዶ ሲሸነፍ ኳስ እና መረብን ካገናኘም ሶስት ዘጠና ደቂቃዎች ተቆጥረዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም እንዳለፉት አመታት ሁሉ ውጤት አልባ ጉዞውን የተያያዘው ሲሆን ትናንት አርባምንጭ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ በሊጉ ግርጌ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። ክለቡ እንደተጋጣሚው ሁሉ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች የደረሱበት ቢሆንም 11ኛው ሳምንት ወደ ሀዋሳ ተጉዞ አንድ ነጥብ ይዞ መመለሱ የሚታወስ ነው። ፋሲሎች የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፉ እስከ ሶስትተኛነት ከፍ ማለት የሚችሉ ሲሆን አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡም የእፎይታ ጊዜ የሚያገኙ ይሆናል። በአንፃሩ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስር ሁለተኛ ጨዋታውን የሚያደርገው ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ዕድል የሚያገኝበት ጨዋታ ይሆናል።
ቀለል ያለ ልምምድ የጀመረው ያሬድ ባየህ እንዲሁም አይናለም ሀይለ በጉዳት የማይኖሩ የአፄዎቹ ተጨዋቾች ሲሆኑ ሀይሌ እሸቱ ፣ ቢኒያም አሰፋ ፣ ዐወት ገ/ሚካኤል እና ዘካሪያስ ቱጂም በኤሌክትሪክ በኩል ከጉዳታቸው ያላገገሙ ተጨዋቾች ናቸው። ከዚህ ውጪ ግብ ጠባቂው ሱሊማን አቡ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እየገባ ባለመሆኑ ከክለቡ ጋር ባለመግባባቱ ምክንያት ወደ ጎንደር አልተኳዘም። የፋሲል ከተማው አብዱርሀማን ሙባረክ እና የኢትዮ ኤሌክትሪኩ በሀይሉ ተሻገር ደግሞ ከቅጣት መልስ ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።
ፋሲል ከተማ ባለፉት ጨዋታዎች የመሀል አጥቂ ቦታ ላይ ራምኬል ሎክን እና ፊሊፕ ዳውዝን እንዲሁም በመስመር አጥቂነት ራምኬል ሎክ ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ ፣ ኤፍሬም አለሙን እና ናትናኤል ጋንቹላን በመቀያየር ሲጠቀም የቆየ መሆኑ ሊኖረው የሚገባውን የሜዳ ላይ ውህደት እያሳጣው ያለ ይመስላል። በተለይ ዋነኛ ጥንካሬው የነበሩት የመስመር አጥቂዎቹ ተፅዕኖ ፈጣሪነት መውረድ እና ከግብ አስቆጣሪነት መራቅ ለውጤት መንሸራተቱ እንደምክንያትነት የሚነሳ ነው። ይህ ችግር ከአማካይ ክፍሉ ደካማ የመከላከል ተሳትፎ እና የማጥቃት ሽግግር ፍጥነትን መቀነስ ጋር ተዳምሮ የፋሲልን ጥንካሬ እንዳንመለከት አድርጓል። በዚህ ረገድ የአብዱርሀማን ሙባረክ ለዚህ ጨዋታ መድረስ ለአፄዎቹ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ትልቅ መሻሻል ሊያመጣ እንደሚችል መናገር ይቻላል። የተጨዋቹ መኖር ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመከላከል ቅርፁን ከመያዙ በፊት ከነዳዊት እስጡ
ጢፋኖስ የሚነሱ ኳሶችን ወደ ጥሩ አጋጣሚ የመቀየር ዕድልን ይፈጥራል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ይጠበቃል። ከሜዳ ውጪ የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ቡድኑ ወደ ራሱ ጎል ተጠግቶ በመከላከል ከፋሲሎች የአማካይ ክፍል የሚነሱ ኳሶችን በማቋረጥ ለፊት አጥቂዎቹ በማድረስ ባለፉት ጨዋታዎች ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰራ የታየውን የባለሜዳዎቹን የኃላ ክፍል እንደሚፈትን ይጠበቃል። የአዲሱ አሰልጣኝ ዋነኛ ፈተና የሆነው የቡድኑ የተሸናፊነት መንፈሰ እንዲስተካከልም ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ መሰል ጠንካራ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ትልቅ አስተዋፅዖ የሚኖረው በመሆኑ ይህ ጨዋታ ለኢትዮ ኤሌክትሪኮች የራሱን መልካም ዕድል ይዞ ሊመጣ የሚችልበት አጋጣሚ የሰፋ ነው።
መቐለ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
በሳምንቱ መጨረሻ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መሀከል በፌደራል ዳኛ ሰለሞን ገ/ ሚካኤል መሪነት መቐለ ላይ የሚደረገው ይህ ጨዋታ ሁለት የተነቃቃ መንፈስ ላይ የሚገኙ እና ተቀራራቢ ነጥብ የሰበሰቡ ክለበችን የሚያፋጥጥ ይሆናል። መቐለ ከተማም ሆነ ሲዳማ ቡና ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ መሪ ደደቢት ከደረሰባቸው ሽንፈት በኃላ ረዘም ላሉ ሳምንታት ተጠናክረው በመቀጠል ነጥቦችን ሲሰበስቡ ከርመዋል። ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በሜዳቸው በደደቢት 2-0 ከተረቱ በኃላ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ዕኩሌታውን በማሸነፍ ቀሪውን ደግሞ ነጥብ በመጋራት አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሲዳማ ቡናም በደደቢት የደረሰበትን የ5-2 ሽንፈት ተከትሎ ሶስት የሜዳውን ጨዋታዎች በማሸነፍ እና ከሜዳው ውጪ ደግሞ ሁለቴ ነጥብ በመጋራት ደረጃውን በሚገባ አሻሽሎ ወደ ስድስተኛነት መጥቷል። የዛሬው ጨዋታም መቐለዎችን እስከ ሁለተኛነት ሲዳማዎችን ደግሞ እስከ ሶስተኛነት ከፍ የማድረግ አቅም ያለው በመሆኑ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
የሲዳማ ቡናዎቹ ፈቱዲን ጀማል እና ፍፁም ተፈሪ እንዲሁም የመቐለ ከተማው ያሬድ ከበደ በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው እንደማይደርሱ ሰምተናል።
ጨዋታው በቡድኖቹ ወቅታዊ አቋም ብቻ ሳይሆን በሚከተሉት አጨዋወትም ጭምር ፍጥነት የታከለበት ጠንካራ ፉክክርን እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል። በሁለት የተከላካይ አማካዮች ሽፋን የሚያገኘው ጠጣሩ የመቐለዎች የተከላካይ መስመር በተለይ ቡድኑ ጎል አስቆጥሮ ውጤት ማስጠበቅ በሚፈልግባቸው ወቅቶች ላይ በእጅጉ እየጠቀመው ይገኛል። በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት የማይቸገረው የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህለ ቡድን በዚህ ጨዋታ ላይ ደግሞ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች ባለቤት የሆነው ሲዳማ ቡናን የሚገጥም መሆኑ በሜዳው ስፋት የመከላከል ብቃቱ የሚፈተን ይሆናል። እንደነ አዲስ ግዳይ ፣ ሀብታሙ ገዛሀኝ እና አብዱለጢፍ መሀመድ ያሉ ለመልሶ ማጥቃት የተመቹ የመስመር አጥቂዎችን የሚጠቀመው ሲዳማ ቡና ዛሬም ወደ ራሱ ጎል ተስቦ በመጫወት ጠንካራውን የተጋጣሚ የተከላካይ ክፍል ወደ መሀል ሜዳው በሚቀርብባቸው አጋጣሚዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ሁለቱም ኮሪደሮች በሚላኩ ኳሶች ሰብሮ ለመግባት እንደሚሞክር ይጠበቃል። ሰሞንኛ አቋሙ እያስገረመ የሚገኘው የወንድሜነህ አይናለም የረዥም ርቀት ሙከራዎችም እንዲሁ ቡድኑ የግብ ዕድሎችን ከሚፈጥርባቸው መንገዶች መሀከል የሚጠቀስ ነው። በተመሳሳይ ጥሩ የመስመር አማካዮችን የያዘው የመቐለ ቡድንም በአንድ የተከላካይ አማካይ ከሚጠቀመው የተጋጣሚው አቀራረብ መነሻነት እነ መድሀኔ ታደሰ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል በሁለቱ መስመሮች ከተከላካዮች ፊት በሚኖረው ቦታ ላይ ነፃ ሆነው ኳስ ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚዎች በመፈለግ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥሩበት አማራጭ ውጤት ይዘው ለመውጣት ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።