ከ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ጨዋታዎች መሀከል አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በተደረገው የአዳማ ከተማ እና የወልዋሎ ዓ.ዩ ጨዋታ አዳማ 3-0 በማሸነፍ በሜዳው አይበገሬነቱን ቀጥሎበታል።
በአዳማ ከተማዎች በኩል ባለፈው ሳምንት በአርባምንጭ ከተሸነፈው ስብስብ መካከል ዳንለል ተሾመን በጃኮ ፔንዜ፣ በረከት ደስታን በሱሌይማን ሰሚድ ምትክ በመጀመርያ አሰላለፍ በማካተት ወደ ሜዳ ሲገቡ ወልዋሎዎች ከድቻ አቻ ከተለያየው ስብስብ ሮቤል ግርማን በሙሉአለም ጥላሁን ምትክ ተጠቅመዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርከት ያሉ ሙከራዎች የታዩበት ባይሆንም በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ሙከራ በማድረግ ቅድሚያውን የወሰዱት ወልዋሎዎች ሲሆኑ 4ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪኒስ ሰቨሪንሆ ያሳለፈለትን ኳስ በቀኝ መስመር አጥቂነት ጨዋታውን የጀመረው እንየው ካሳሁን በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታም ኢላማውን መጠበቅ አልቻለም። ከዚህ ውጪ ቢጫ ለባሾቹ በሁለት አጋጣሚዎች ወደ ግራ ካደሉ የሮቤል ግርማ የመሀል ሜዳ ቅጣት ምቶች ከተሻሙ ኳሶች አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ከመሞከራቸው ውጪ ንፁህ የግብ ዕድል አላገኙም። ወልዋሎዎች ተጋጣሚያቸው መሀል ሜዳ ላይ ኳስ ሲይዝ በቶሎ አፍኖ በማስጣሉ በኩል የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም የሚቀሟቸውንም ሆነ ከኃላ የሚመስርቷቸውን ኳሶች ይዘው መሀል ሜዳውን ቢያፉም ጠንካራዉን የአዳማን የተከላካይ መስመር ለማለፍ ግን አልተቻላቸውም። ባልተለመደ መልኩ የተከላካይ አማካይነት ሚና ከተሰጠው አፈወርቅ ኃይሉ ፊት የነበረው የዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ጥምረት ከኳስ ጋር ባለ እንቅስቃሴ ጥሩ አለመሆን እና በፊት አጥቂነት የተሰለፈው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አብዛኛውን ሰዐት ጅርባውን ለአዳማ ጎል ሰጥቶ እና ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ መጫወቱ ለወልዋሎዎች በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ዘልቆ ያለመግባት ምክንያት ሆነው የሚጠቀሱ ችግሮች ነበሩ።
ባለሜዳዎቹ አዳማዎችም በተጋጣሚያቸው አቀራረብ ምክንያት ኳስ መስርተው ከሜዳቸው መውጣት ባይችሉም በሙጂብ ቃሲም ጉዳት እንኳን ያልተከፈተው የኃላ መስመራቸው ጃኮ ፔንዜን ተክቶ ግቡን ሲጠብቅ የነበረውን ዳንኤል ተሾሞን አሳልፎ አልሰጠም። ሆኖም መሀል ላይ ለእስማኣል ሳንጋሪ ቀርቦ ይጫወት የነበረው ከንአን ማርክነህ በዋለልኝ ገብሬ በመያዙ ኳስ የማሰራጨት ሀላፊነቱ ቀላል አልሆነለትም። ነገር ግን የአዳማዎች አስፈሪነት ከመስመር ተከላካዮች በቀጥታ ወደ ቡልቻ እና ዳዋ በሚጣሉ ኳሶች ላይ ጎልቶ ይታይ ነበር። ከዚህም ባለፈ ጨዋታውን በግራ መስመር ጀምሮ ከ20ኛው ደቂቃ በኃላ ወደቀኝ የዞረው በረከት ደስታ ከአንዳርጋቸው ይልሀቅ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ለአዳማዎች የመስመር ጥቃት ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል። በረከት 28ኛው ደቂቃ ላይ ከከንዐን ማርክነህ ጥሩ ኳስ ደርሶት ሳይቆጣጠረው ቀረ እንጂ ግብ የሚያስቆጠር ዕድልም አግኝቶ ነበር። በረከት ይህ ዕድል ቢያልፈውም ከአንድ ደቂቃ በኃላ በዛው ቀኝ ክንፍ በፍጥነት ኳስ ይዞ ወደ ወልዋሎ ሳጥን ሊገባ ሲል በአፈወርቅ ኃይሉ በመጎተቱ ምክንያት የተሰጠው ቅጣት ምት ነበር አዳማን ቀዳሚ ያደረገው። የቅጣት ምቷ አስቆጣሪ ደግሞ ልማደኛው ዳዋ ሁቴሳ ነበር። በረከት አማረ ኳሷን ለማደን ምንም እንቅስቃሴ ከማድረጉ በፊት መረብ ላይ ያረፈችው ይህች የዳዋ ቅጣት ምት ከእረፍት በፊት አዳማን ቀዳሚ አድርጋ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ወልዋሎዎች በርካታ የቦታ ልውውጥ አድርገው የቡድኑ አጠቃላይ መልክ በአሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚያብሃር ጊዜ እንደነበረው ሆኗል። በዚህም መሰረት እንየው ካሳሁን ወደ ቀኝ መስመር ተከላካይነት ፣ አሳሪ አልመሀዲ ወደ ተከላካይ አማካይነት ፣ ፕሪንስ ሰቨሪንሆም ወደ ቀኝ መስመር አጥቂነት ሲሸጋሸጉ የዋለልኝ ገብሬ እና የአፈወርቅ ኃይሉ የአማካይ ክፍል ጥምረትም ቦታውን ይዟል። ያም ቢሆን ቡድኑ እንደመጀመሪያው ሁሉ የአዳማን የኃላ መስመር ማስከፈት ተስኖት ታይቷል። በተቃራኒው የወልዋሎዎች የማጥቃት ሂደት ወደ አዳማ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው እንዲገኙ በማድረጉ እና ወደ መከላከል የሚያደርጉት ሽግግርም ፍጥነት የታከለባት ባለመሆኑ ወደ መሀል ሜዳው ከተጠጋው የተከላካይ ክፍላቸው ጀርባ የነበረው ሰፊ ክፍት ቦታ ለአዳማ ከተማዎች ምቹ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ፈጥሯል። አዳማዎች መሰል አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ጎል ማስቆጠር እንደሚችሉ ምልክት መስጠት የጀመሩት 62ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በዚሁ ደቂቃ ምኞት ደበበ ከወልዋሎዎች የነጠቀውን ኳስ በአስደናቂ ፍጥነት ወደፊት እየገፋ ሄዶ ለበረከት ደስታ ካሳለፈለት በኃላ በረከት በግሩም ሁኔታ መልሶለት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ስቷል። በመቀጠል የተፈጠሩትን ተመሳሳይ ዕድሎች ግን ከንአን ማርክነህ እና በረከት ደስታ ወደ ግብነት መቀየሩ ተሳክቶላቸዋል። 74ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ከመሀል ሜዳ በረዥሙ ያሻገረለትን ኳስ ከንአን የወልዋሎ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው ሲዘናጉ በፍጥነት በማምለጥ በግንባሩ ጨርፎ በግብ ጠባቂው በረከት አማረ እግሮች መሀል በማሳለፍ ከግቡ አፋፍ ላይ በእግሩ ጨርሶ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ከሰባት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ አንዳርጋቸው ይልሀቅ በተመሳሳይ ከወልዋሎ ተከላካዮች ጀርባ የጣለውን ኳስ በረከት ደስታ ቺፕ አድርጎ በማስቆጠር የአዳማን አሽሸናፊነት አረጋግጧል። ሱሊማን ሰሚድ እና ኤፍሬም ዘካሪያስን ቀይረው በማስገባት የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቻቸውን ወደ አምስት ከፍ ያደረጉት አዳማዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በመጠኑ ወደ ኃላ ቀረት ብለው አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ጫና እየፈጠሩ የሶስት ጎል መሪነታቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል። በነዚሁ ደቂቃዎች የተሻሉ የሚባሉ ዕድሎችን ባገኙት ወልዋሎዎች በኩል 86ኛው ደቂቃ ላይ አፈወርቅ ኃይሉ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር የ89ኛው ደቂቃ የመኩሪያ ደሱ ቅጣት ምት ደግሞ በግቡ ቋሚ ተመልሷል። በመሆኑም ወልዋሎዎች የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ሳይችሉ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት የቻለ ሲሆን ወልዋሎዓ.ዩ በነበረበት የ11ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ
ውጤቱን እንፈልገው ነበር ካለፈው ምሳንት በመነሳት። በተነጋገርነው መሰረትም ልጆቹ በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። በቡና እና በአርባምንጭ ጨዋታ ያልነበሩ ተጨዋቾቻችን ከጉዳት መመለሳቸው ጠቅሞናል።
አሰልጣኝ ሀፍቶም ኪሮስ – ወልዋሎ ዓ.ዩ
ጨዋታው ጥሩ ነበር አዳማዎች ከኛ በልጠው ሳይሆን ያሸነፉት ያገኙትን የግብ ዕድል በመጠቀማቸው ነው፡፡ የሙሉአለም መጎዳት የተጫዋቾች ለውጥ እንዳደርግ አስገድዶኛል። የቡድን ቅርጽ ግን ከበፊቱ አልተለወጠም፡፡