ዛሬ በተካሄዱ ሁለት የብሄራዊ ሊግ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፍ ቡድን አግኝቷል፡፡
በ4 ሰአት ወልዲያ ከነማ ድሬዳዋ ከነማን 1-0 አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መቀላቀሉን አረጋግጧል፡፡ ተስፋዬ ነጋሽ የወሎውን ክለብ ብቸኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ አጥቂው የጨዋው ኮከብ ተብሎም ሽልማት ተቀብሏል፡፡
በ8 ሰአት የውድድሩ አስተናጋጅ ከተማ ክለብ የሆነው ባህርዳር ከነማ በወልቂጤ ከነማ በመለያ ምት ተሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሳይገባ ቀርቷል፡፡ የመደበኛው 90 ደቂቃ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጥታ ወደ መለያ ምቶች አምርተዋል፡፡
በመለያ ምቶቹ ወልቂጤ ከነማዎች ሁሉንም ሲያስቆጥሩ ባህርዳሮች አንድ ግብ አምክነው ጨዋታው በወልቂጤ ከነማ 6-5 አጠቃላይ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ወልድያ ከነማ እና ወልቂጤ ከነማ ከዚህ በፊት በፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፈው የማያውቁ ሲሆን በግማሽ ፍጻሜው ያሸነፈ ክለብ በፕሪሚየር ሊግ ታሪክ የተሳተፈ 42ኛ ክለብ ይሆናል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እሁድ በ8 ሰአት ለፍጻሜ ለማለፍ እና በተዘዋዋሪም ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ወሳኙን ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡