አርባምንጭ ከተማ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስከፊ 11 ሳምንታት ጊዜያትን ካሳለፈ በኃላ በአዲሱ አሰልጣኝ እዮብ ማለ ስር ከሁለት ጨዋታዎች 4 ነጥብ ሰብስቦ ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ተላቋል።
አርባምንጭ ከተማ በውድድር ዘመኑ ከፍተኛ ክፍተት ከሚታይበት ስፍራ መካከል የአጥቂ መስመሩ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው። አዞዎቹ ያለፉትን 5 ጨዋታዎች ገ/ሚካኤል ያዕቆብን በቅጣት እንዲሁም ከክለቡ ያሰናበቱት ላኪ ሳኒን በማጣታቸው ይህንን ክፈተት ለመድፍን እንደ አማራጭ የወሰዱት የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ተመስገን ካስትሮን በአጥቂነት ማሰለፍ ነው። ተመስገንም በአጥቂነት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በተለይ በሜዳው አዳማን ሲያሸንፍ ለፀጋዬ አበራ ግብ ማስቆጠር ምክንያት ሲሆን በዚህ ሳምንት ደግሞ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳን በገጠሙበት ጨዋታ ቡድኑ ነጥብ የተጋራበትን ወሳኝ ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ለድሬዳዋ ፖሊስ በአጥቂነት ተሰልፎ የሚጫወተው ታላቅ ወንድሙ ከፍያለው ካስትሮን ተምሳሌት አድርጎ እንዳደገ የሚናገረው ተመስገን ለአርሰናል እጫወታለሁ እያለ በልጅነቱ ያልም እንደነበር ይናገራል። ተመስገን የክለብ ተጫዋችነት ዘመኑን ከ2005 ጀምሮ በኦሮሚያ ማረሚያ (አሰላ) ጅማሮውን ካደረገበት ጀምሮ በኮንሶ ኒውዮርክ ፣ እንዲሁም በሻሸመኔ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጫውቶ አሳልፏል። ከታዳጊነቱ ጀምሮ ወጥ ቦታ ላይ አለመጫወቱ በድንገተኛ የቦታ ለውጡ ግራ እንዳይጋባ የረዳውም ይመስላል።
” ገና በልጅነቴ ኳስን ስጀምር ኳስ እጨመወት የነበረው በተለያዩ ሚናዎች ነበር። ቋሚ ቦታም አልነበረኝም። በፕሮጀክት ደረጃ ስጫወት አጥቂ ነበርኩ ፤ ከዛም በኃላ ወደ አማካይ መጣሁ ፤ በመጨረሻ ነው በተከላካይነት መጫወት የጀመርኩት። ” የሚለው ተመስገን የሚና ለውጡ እንደተመቸውም ገልጿል።
” አስቀድሞ የተሟላ ተጫዋች ስትሆን እና የሚና ለውጦች ተፅእኖ የማይፈጥሩብህ ሲሆን በጣም ደስታ ይሰማሀል። እኔም እንዲህ አይነት እድል በመፈጠሩ የተለየ ነገር ይሰማኛል። ጠንክረህ ከሰራህም ደግሞ ማንኛውም አሰልጣኝ በሚያዝህ ቦታ ላይ እንድትጫወት ስትደረግ የተሰጠህንም ሚና መወጣት አስፈላጊ መስሎ ይሰማኛል። የትኛውም ቦታ ላይ ችላለው ብለህ አዕምሮህን ካሳመንክ ትችላለህ። ለዚህም መስራት ያስፈልግሀል እኔም አሁን ላይ ከተከላካይነቱ ይልቅ በአጥቂነት መጫወቴ ተመችቶኛል። አሰልጣኙ እድል እስከሰጠኝም ድረስ በአጥቂነት ከአሁን በኃላ ትልቅ ቦታ ላይ እደርሳለው ብዬ አስባለሁ።
” አሁን ላይ እሱ የአሰልጣኙ ስራ ነው ክለቡንም ስቀላቀልም ሆነ ከዛ አስቀድሞ ተከላካይ ላይ ነው የምጫወተው። ክለቡ ባለው የአጥቂ ችግር ምክንያት ደፍሮ እድሉን ሰጥቶኛል። በአጥቂነት የድቻ ጨዋታ ላይ ነበር የገባሁት። በጨዋታው ጥሩ በመንቀሳቀሴ እና ከሌሎቹ የተሻልኩ ሆኜ በመገኘቴ ነው እንድቀጥል ያደረገኝ። እኔም ሆንኩ ሌሎች አጥቂዎች ገብተን ልዩነቱ ታይቷል። በአዳማው ጨዋታ ላይም ጥሩ በመሆኔ ቀጣይነት እንዲኖረው ፍላጎቴ ጨምሯል። በዚሁ መቀጠልን እፈልጋለሁ።” ሲል በቦታው መቀጠል የመጀመርያ ምርጫው እንደሆነ ተናግሯል።
የተመስገን የቦታ ለውጥ ከክለቡ ስር ነቀል የአመራር እና የአሰልጣኞች ለውጥ እንዲሁም የውጤት መሻሻል ጋር ተገጣጥሟል። ክለቡ ከመጥፎ ሁኔታ ለመውጣት ጠንክረው እየሰሩ እንደሆነ እና ወደተሻለ ሁኔታ እያመሩ እንደሆነ ተመስገን ያምናል። በግሉም አሰልጣኙ በጣሉበት እምነት እንዳልተሳሳቱ ለማሳየት እንደሚተጋ ገልጿል።
” አርባምንጭ ከተማ አሁን ያለበት ደረጃ ክለቡንም ደጋፊውንም ሆነ ተጫዋቾቹን የሚመጥን አይደለም። በቁጭት ሁሌም እንሰራለን እስከ አሁንም ስንሸነፍ የነበረው በራሳችን ስህተት ነው። አሁን ላይ ቢያንስ ስተቶቻችንን አርመናል። ተጫዋቹ ብቻ ሳይሆኑ አሰልጣኙ እና አመራሩ ተቀይሯል። መንፈሳችንም በሚገባ ተለውጦ ጠንክረን እየሰራን ነው ያለነው። ራሳችንን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል በተነሳሽነት ላይ ነን። ከበላዮቻችን ጋር የደረጃ እንጂ የነጥብ ልዩነት የለም። ስለዚህም ወደ ተሻለ ቦታ ለመድረስ በግሌም ከቡድን አጋሮቼ ጋርም እንሰራለን።
” ክለቡን መጥቀም እና ከዚህ ደረጃ እንዲወጣ መርዳት እፈልጋለሁ። በቅድሚያ እኛ እስከ አሁን በጨዋታ ተበልጠን ሳይሆን በራሳችን ጥቃቅን ስህተት ነው የምንሸነፈው። መንፈሳችንሞ ጥሩ አልነበረም። የደጋፊው ጫና በውጤት መጥፋት ምክንያት ነበረ ፤ አሁን ላይ ውጤት ስናመጣ ደጋፊው ከጎናችን ሆኗል። እኔም ከአሁን በኋላ ጎሎች አስቆጥራለሁ ብዬ ነው የማስበው። አሰልጣኙም ሆነ የቡድን ጓደኞቼ ካለኝ አቅም አንፃር ጥሩ መጫወት እንደምችል ያበረቱኛል። ” ከአሁን በኃላ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ትሆናለህ” ይሉኛል። እኔ ግን ገና ምንም በአጥቂነት መጥቼ የሰራሁት ነገር የለም። ቢሆንም ግን ከሚሰጡኝ ማበረታቻ በመነሳት አምኖ ያስገባኝን አሰልጣኝም ሆነ ሁሉንም እክሳለሁ ብዬ አምናለሁ። “