ወልድያ እግርኳስ ክለብ በወቅታዊ ጉዳዮች ምክንያት ተጫዋቾቹን በጊዜያዊነት መበተኑ እና መደበኛ የልምምድ መርሀ ግብር ማካሄድ ማቆሙ እንዲሁም የቡድኑ ተጫዋቾቹ ወደሚኖሩበት ከተማ መጓዛቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ምንጮች አረጋግጣለች።
ወልዲያ በ12ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ወደ ጅማ በማቅናት ከጅማ አባጅፋር ጋር ጨዋታውን ካደረገ በኋላ ወደ ወልዲያ መመለስ ያልቻለ ሲሆን የቡድኑ አባላት በአአ የተወሰኑ ቀናትን በመቆየት በክለቡ የበላይ አመራሮች ትዕዛዝ መሰረት የተወሰኑ ተጫዋቾች አአ ቀርተው የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾችና የአሰልጣኝ አባላት በጠቅላላ ሐሙስ ማለዳ ወደ ደሴ በማቅናት ደሴ ካደሩ በኋላ በንጋታው ወልዲያ ደርሰዋል። ሆኖም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት አምስት ተጫዋቾች ብቻ በዚያው ሲቀሩ ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ለደህንነታቸው በመስጋት በሁለት ቀናት ውስጥ በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች በመጠቀም ከወልዲያ ከተማ ለቀው ወጥተዋል።
ክለቡ በአሁኑ ሰአት እንደ ክለብ ተሰባስቦ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑ ሲረጋገጥ እስከ 1ኛው ዙር መገባደጃ ድረስ ሊደረጉ የታሰቡ ጨዋታዎች በሙሉ ወደ ሌላ ጊዜ ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ ተነግሯል። ክለቡም ተጫዋቾቹን ሰብስቦ መቼ ወደ ውድድር ይመለሳል የሚለው በክለቡ የቦርድ አመራሮች በሚሰጥ ውሳኔ የሚታወቅ ይሆናል ።
ወልዲያ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ11 ጨዋታ 12 ነጥቦችን ሰብስቦ በ12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በቀጣይ ከክለቡ አካባቢ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ እየተከታተልን የምናቀርብ መሆን እንገልፃለን።