በሀላባ ሤራ በዓል ምክንያት ከእሁድ ወደ ማክሰኞ የተዘዋወረው ጨዋታ በሀላባ ስታድየም 09:00 ተካሂዶ ሀላባ ከተማ በአቦነህ ገነቱ ብቸኛ ግብ ታግዞ ቡታጅራ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
አዲስ በተሰራው የክቡር ትሪቡን እና በተለምዶ ካታንጋ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በተገነባው መቀመጫ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ ፋጣን እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በጨዋታው በጎልም ሆነ በሙከራ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ሀላባዎች ነበሩ። በዚህም በ6ኛው ደቂቃ ስንታየው አሸብር ያሻገረውን ኳስ ስንታየው መንግስቱ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ጎል ሲመታ አንጋፋው ተጫዋች አፋወርቅ ሀይሉ ተደርቦ ቢያውጣውም በቅርብ ርቀት ላይ እና ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አቦነህ ገነቱ አክርሮ በመምታት አጋጣሚውን ወደ ግብነት በመቀየር ሀላባ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ በድጋሜ አቦነህ ገነቱ ተመሳሳይ ኳስ አግኝቶ ቢሞክርም የቡታጅራው ግብ ጠባቂ ልዩ ብቃት ታክሎበት ግብ ከመሆን ድኗል። በ10ኛው ደቂቃ በቡታጅራ ከተማዋች በኩል ክንደ አብቹ በግንባሩ ግብ ቢያስቆጥርም የዕለቱ ዳኛ የነበሩት ጌጡ ተፈሪ ቀደም ተብሎ ጥፋት ተሰርቷል በሚል ግቡን ሳይፅድቀው ቀርቶል። በዚህም ምክንያት ቡታጅራዎች ክስ አስይዘው ጨዋታው ካቆመበት ቀጥሎል።
ኳስ መስርተው ለመጫወት ጥረት የሚደርጉት ቡታጅራዋች ኳስን ወደ መሀል ሜዳ ይዘው ከደረሱ በኃላ ገፍተው ወደ ሀላባ የጎል ክልል መድረስ ተስኖቸው ታይተዋል። በ22ኛው እና በ25ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ቶማስ ከርቀት በመታቸው ኳሶች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርጎ ነበር። በ 31ኛው ደቂቃ ላይ ይኸው ተጨዋች ላይ ጥፋት በመሰራቱ የቅጣት ምት ቢሰጥም በውሳኔው ያልተደሰቱት የሀላባ ተጨዋቾች የዳኛውን ውሳኔ ተቃውመዋል። በቅጣት ምት የተሻማው ኳስ የቡታጅራው ክንዴ አቡቸ በእጁ በመንካቱ አልቢትሩ ፍፁም ቅጣት ምት ለቡታጅራ በመስጠታቸው ተጫዋቾቹ እና የሀላባ አመራሮች የዳኛውን ውሳኔ ፍፁም ተቃውመዋል። ፌደራል ዳኛ ጌጡም የሁለቱንም በድን አምበሎች እና የቡድን መሪዎች ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን ሲመክሩ ቆይተው የፍፁም ቅጣት ምቱን ያስመቱ ሲሆን በዘንድሮ አመት ከሻሸመኔ ከተማ ወደ ሀላባ ከተማ የተዘዋወረው ግብ ጠባቂው ሶፊንያስ የተመታውን ኳስ አድኖታል።
ከፍፁም ቅጣት ምቱ በኃላ ሀላባ ከተማዋች ጨዋታውን አስቁመው ክስ አስይዘዋል። በመቀጠል ከፍተኛ መነቃቃት የታየባቸው ሀላባዋች ወደ ቡታጅራ የግብ ክልል ሲጠጉ የነበረ ሲሁን 44ኛው ደቂቃ አብነት ተሾመ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ የቡታጅራው ወንደሰን ዮሐንስ ተደርቦ ቢያድናትም በዛው ቅፅበት ባስተናገደው ጉዳት መነሳት ሳይችል በመቅረቱ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል እንዲያመራ ተደርጓል፡፡በተቀሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ተጨማሪ ሙከራዎች ሳይደረጉ ቡድኖቹ ከዕለቱ አወዛጋቢ ዳኝነት ጋር ታጅበው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
የሀላባ ደጋፊዎች ማህበር ድጋፊዎቻቸውን ከስፖርታዊ ጨዋናት ውጪ የሆነ ማንኛውም አይነት ድርጊት እንዲቆጠቡ እና ድጋፋቸው እንዴት መህምን እንዳለበት ሲያስተምሩ ተስተውለዋል። እንደዚህ አይነቱ ድርጊት ይበል የሚያስብል እና ለእግር ኳሶ ሰላማዊነት እና እድገት የሚንምረው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።
ከዕረፍት መልስ ሀላባዋች ወደ መከላከሉ አመዝነው መጫወት ሲመርጡ ቡታጅራዋች ውደ ፊት ገፍተው የአቻነት ግብ ለማግኘት ሙከራ አድርገዋል። ሆኖም በክንዴ አብቹ እና ኤፍሬም ቶማስ ያደረጓቸው ሙከራዎች እንዳሰቡት ውጤታማ ሳያደርጓቸው ቀርተዋል። ሀላባዋች ረዥም ኳሶችን ወደፊት በመላክ በረዥሙ አጥቂ ስንታየው መንግስቱ ለመጠቀም ሲንቀሳቅሱ የነበረ ሲሁን በ76ኛው ደቂቃ ላይ ተጨዋቹ ግብ ማስቆጠር ቢችልም ከጨዋታ ውጭ ሆኖ በመገኘቱ ሳይፀድቅ ቀርቶል። በዚህ ሁኔታም ጨዋታው በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል። በሁለተኛው አጋማሽ ከሀላባ የግብ ክልል በስተጀርባ የነበረው ኳስ አቀባይ የኳስ የማቀበል ፍጥነቱ መዘግየትም ሌላው የጨዋታው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ አልፏል።