በኢትዮዽያ ከፍተኛ ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ በኦሜድላ ሜዳ በተካሄደ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ሽረን 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።
በተለያየ ቀን እንዲካሄድ መርሐግብር ወቶለት የነበረ ቢሆንም በፀጥታ አካላት ትዕዛዝ ምክንያት ሁለት ጊዜ ሳይካሄድ የተቋረጠው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ ረፋድ 5:00 ላይ በኦሜድላ ሜዳ ተካሂዷል። በከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር በተከናወነው በዛሬው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ደጋፊዎች የተገኙ ሲሆን ጨዋታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስም በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት ቡድናቸውን ደግፈው ወጥተዋል።
በመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢደረግበትም ባልተሳካ ሁኔታም ቢሆን ባህርዳሮች የግብ እድል በመፍጠር እና ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት የተሻሉ ነበሩ። 6ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ታሪኩ በተከላካዮች መካከል ሆኖ የሞከረው ኳስ ለጥቂት የወጣበት እና ከሰባት ደቂቃ በኋላ ራሱ ሙሉቀን ታሪኩ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባሩ ገጭቶ በግቡ አናት የወጣው በባህርዳር ከተማ በኩል ተጠቃሽ የግብ ሙከራዎች ነበሩ።
ሽረዎች በቀኝ መስመር አድልተው የሚፈጥሩት የማጥቃት እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም የመስመር አጥቂዎቹ የሚያገኙት ኳስ በአግባቡ ለአጥቂዎች በማድረስ በኩል ውስንነት የነበራቸው በመሆኑ ብዙ ለግብ የቀረበ ሙከራ እንዳያደርጉ ገደባቸዋል። በመጀመርያው አጋማሽ ፍፃሜ ላይ በ45ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉጌታ አንዶም ያገኛት የግብ አጋጣሚ የሽረ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። የመጀመርያው አጋማሽም ያለ ጎል ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ ከመጀመርያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻለ ጨዋታ የተመለከትን ሲሆን ሽረዎች በአንድ አጥቂ ለመጫወት ማሰባቸው ብዙም አልተሳካላቸውም። ቢሆንም ልደቱ ለማ በ54ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ ብቻውን ኳሱ ገፍቶ ወደ ሳጥን በመግባት ጎል አስቆጠረ ሲባል ከጀርባው ተከላካዮች ደርሰው ያወጡበት ኳስ ለሽረ የሚያስቆጭ የጎል አጋጣሚ ነበር። ባህርዳር ከተማዎች በ64ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው እንዳለ ከበደ አማካኝነት ጎል ቢያስቆጥሩም የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው ጎሉን ባለማፅደቃቸው የባህርዳር ከተማ ተጨዋቾች ውሳኔውን ተቀውመዋል።
ጨዋታው ከተወሰኑ ውዝግቦች በኋላ ቀጥሎ ባህርዳሮች በተረጋጋ ሁኔታ በእንቅስቃሴ ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ የነበሩ ሲሆን የግራ መስመር ተከላካዩ ግርማ ዲሳሳ ከቦታው በፍጥነት ወደ ሽረ የግብ ክልል ውስጥ በመግባት ያሻገረውን ኳስ የሽረ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዩ ኳሱን ለማውጣት ሲሞክሩ ኳሱ ራሳቸውን ገጭቶ ወደ ጎልነት ተለውጧል። ጎሉን ተከትሎም በስፋራው የነበሩ የባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች ደስታቸው ወደር አልነበረውም።
በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 89ኛው ደቂቃ ላይ የሽረው ልደቱ ለማ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ከወጣበት ሙከራ በቀር ጨዋታው ሰአት በማባከን እና ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ታይቶ የሽረ ተጨዋቾችም ምንም የጎላ ጫና ሳይፈጥሩ ጨዋታው በባህርዳር ከነማ 1-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ድሉን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ 3 ጨዋታ እየቀረው በ15 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ 2 ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሽረ እንዳስላሴ ደግሞ ወደ 6ኛ ደረጃ ወርዷል።