በኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ዛሬ አአ ስታድየም ላይ በተደረገ የ8ኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ መከላከያ እና ሀዋሳ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
ለወትሮም በኢትዮዽያ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ሊኖር የሚችለውን ጠንካራ ፉክክርና ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ዛሬም በአአ ስታድየም ያስመለከቱን ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በምርቃት ፈለቀ እና በልደት ተሎአ ፈጥን እንቅስቃሴ የመከላከያ ተከላካዮችን መፈተን ቢችሉም ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት ግን መከላከያዎች ነበሩ። 17ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ አባይነሽ አርቁሎ ከግብ ክልሏ መውጣቷን ያየችው የመከላከያ የፊት አጥቂ ሄለን ሰይፉ በጥሩ ሁኔታ ባስቆጠረችው ግሩም ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
በ30ኛው ደቂቃ በዘንድሮ አመት ከአርባምንጭ ከተማ ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅላ ምርጥ የአማካይ ስፍራ ተጫዋችነቷን መሀሰኗን እያሳየች የምትገኘው ሳራ ኪዶ በቅንቅስቃሴ ወደ ፊት ገብታ ያስቆጠረችው ጎል ሀዋሳዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው በከፍተኛ ፉክክር ቀጥሎ በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ እንደሚፈጥሩት ጫና ጎል ለማስቆጠር የተሻለ የነበሩት ሀዋሳዎች ከመመራት ተነስተው ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የሚችለውን አጋጣሚ በ43ኛው ደቂቃ ላይ እንደ ሳራ ኪዶ ሁሉ በዘንድሮ አመት ከአርባምንጭ ከተማ ሀዋሳን ተቀላቅላ ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፈች የምትገኘው ተስፈኛዋ አጥቂ ልደት ተሎአ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ባስቆጠረችው ጎል ወደ መሪነት በመሸጋገር የመጀመርያውን አጋማሽ አጠናቀዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ የአቻነቱን ጎል እስኪያስቆጥር ድረስ ጫና ፈጥረው ይጫወቱ የነበሩት ሀዋሳዎች በ48ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ በግራ መስመር ሰብራ ገብታ ለልደት በጥሩ ሁኔታ አሻግራለት ልደት አስቆጠረች ሲባል ሳትጠቀም የቀረችው ፣ 61ኛው ደቂቃ ምርቃት ፈለቀ የግብ ጠባቂዋ ማርታን መውጣት ተመልክታ ከርቀት የሞከረችው ኳስ ይበልጥ መሪነታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
መከላከያ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የአቻነት ጎል ፍለጋ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙም የተሳካ ባይሆንም 64ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ አባይነሽ ኤርቀሎ ከግብ ክልሏ ውጭ ኳስ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን ቅጣት ምት እመቤት አዲሱ ወደ ጎል ስትመታ የሀዋሳ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂዋ ተጋጭተው ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ተጎድታ በወደቀችበት አጋጣሚ እመቤት አዲሱ በድጋሚ ኳሱን አግኝታ በቀጥታ ወደ ጎል የሞከረችውን ቅድስት ዘለቀ ግልፅ በሆነ መንገድ ሊገባ ያለውን ኳስ በእጅ በመመለሷ የዕለቱ ዳኛ ለመከላከያ ፍ/ቅ/ምት ስትሰጥ ኳስ በእጅ የነካችው ቅድስት ዘለቀ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳለች። ግብ ጠባቂዋ ተጎድታ በመውደቋ ጨዋታው መቆም ነበረበት በሚልም የሀዋሳ ከነማ ተጨዋቾች የዕለቱ ዳኛን ተቃውመዋል። የተሰጠውን ፍ/ቅ/ምትም እመቤት አዲሱ በጥሩ ሁኔታ አስቆጥራ መከላከያን አቻ ማድረግ ችላለች።
በቀሩት 25 ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫ የወሰዱት መከላከያዎች አሸንፎ ለመውጣት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙም የተሳካ ያልነበረ ሲሆን በአንፃሩ ሀዋሳዎች በቁጥር ቢያንሱም በምርቃት እና በልደት አማካኝነት የጎል እድል ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መልካም የነበረ ቢሆንም ጎል ማስቆጠር ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት በዛሬው ጨዋታ በመጨረሻም 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
የ8ኛው ሳምንት እሁድ በተደረገ ጨዋታ የተጀመረ ሲሆን ሲዳማ ቡና በረድኤት አስረሳኸኝ የ78ኛ ደቂቃ ብቸኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል። የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤልም ወደ ቡድኑ በመመለስ በጨዋታው ላይ ቡድኑን መስራት ችሏል።
ሊጉ ነገ ፣ ቅዳሜ እና እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል።