​የአሰልጣኞች ገጽ | 40 ዓመታት የዘለቀው የአስራት ኃይሌ ስኬታማ ጉዞ [ ክፍል አንድ ]


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


አስራት ኃይሌ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠሩ ስኬታማ አሰልጣኞች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የአሰልጣኝነት ስራ ከጀመሩ 40 አመታት የደፈኑት አሰልጣኝ አስራት በውጤታማነታቸው ፣ በቆራጥነታቸው እና ጠንካራ ሰራተኝነታቸው በበርካቶች ዘንድ ይወደሳሉ። የ”ጎራዴው” የአሰልጣኝነት ህይወትም በዚህ ገፅ በተከታታይ ይቀርባል። የአስራት የስራ ህይወት ፣ የስልጠና መንገድ ፣ የስኬት ታሪክ እና የመሳሳሉት ጉዳዮች ከአሰልጣኙ ጋር በነበረን ቆይታ በስፋት ተዳሷል። መልካም ንባብ!


አስራት ኃይሌ የተወለዱት በአዲስ አበባ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ ነው። ከ1958 ጀምሮ ከእግርኳስ ጋር የተቆራኙት አስራት በ52 አመታት የእግርኳስ ቆይታቸው ተጫዋች ፣ አሰልጣኝ እና በቅርብ አመታት ደግሞ የቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል።

የተጫዋችነትን ህይወታቸውን የጀመሩት ልደታ አካባቢ በሚገኘው መስከረም ኮከብ በተባለው ቡድን ውስጥ ነበር፡፡ በመቀጠልም በዳርማር፣ ጥጥ ማህበር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኋላም በአዲሱ የደርግ ክለቦች አደረጃጀት በትግል ፍሬ አሁንም ድረስ ” ጎራዴው” የሚል ቅፅል ስም ያተረፈላቸው ጠንካራ ተከላካይ ነበሩ። ለጥጥ ማህበር በሚጫወቱበት ወቅት የሀረርጌ ምርጥ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እያሉ ደግሞ ለሸዋ ምርጥ እና ለመሰኢማ ተጫውተዋል። ለረጅም ጊዜ በቆየው የብሄራዊ ቡድን ቆይታቸውም በ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች እና በ11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ ነበሩ።

በ1970ዎቹ በተጀመረው የአሰልጣኝነት ዘመናቸው በርካታ ክለቦችን አሰልጥነዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ህንፃ ኮንስትራክሽን ፣ መከላከያ ፣ ኤሌክትሪክ ፣ መድን ፣ ደደቢት ከብዙ በጥቂቱ ያሳለፉባቸው ክለቦች ናቸው።


አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የአሰልጣኝነት ህይታቸውን በራሳቸው አንደበት እንዲህ ተርከውታል።

ስራውን ስጀምር በቀጥታ ከትልቅ ቡድን አልጀመርኩም፡፡ ራሴን ለማስተካከልና ለማሻሻል፣ እንዲሁም ስራዬን በልበ ሙሉነት እንድሰራ እና የቋንቋ ችሎታዬን ለማዳበር የሰራተኛ ማህበር (መኢሰማ) ለአራት አመታት ያህል ከተጫዋችነት ሳልገለል አሰለጠንኩ፡፡ የአሰልጣኝነት መሠረታዊ ስልጠና (Basic Course) የወሰድኩት በ1971 ዓ.ም. ነው፡፡ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (ነፍሳቸውን ይማረውና) “እናንተ ተጫዋቾች መጫወትን ስታቆሙ አሰልጣኝ ስለምትሆኑ ኮርስ መውሰድ አለባችሁ፡፡” ብሎን በአንድ ጀርመናዊ አሰልጣኝ አማካኝነት ኮርስ ወሰድኩ፡፡ በሙሉ የአሰልጣኝነት ስራም ህንፃ ኮንስትራክሽን የመጀመሪያ ቡድኔ ሆነ፡፡ በወቅቱ 50 ቡድኖች ሲዋቀሩ ህንፃ በአዲስ መልክ የተመሠረተ ነበር ፡፡ ቡድኑ ሲቋቋም የእኔ ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ በውድድሩ ባስመዘገበው ጥሩ ውጤት መሠረትም ምርጥ 10ሩ ውስጥ ገባ፡፡ በዚህም ሳቢያ ህንፃ ከሁለተኛ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አለፈ፡፡ በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈርሶ ነበር፡፡ ደጋፊዎቹም እየመጡ “ጊዮርጊስን እንደገና ወደ ላይኛው ዲቪዚዮን ማምጣት አለባችሁ!” ይሉኝ ነበር፡፡ ይህንን ለማሣካትም ህንፃን እያሰለጠንኩ ለጊዮርጊስ መጫወት ነበረብኝ፡፡ ነገር ግን ጊዮርጊስ በመጨረሻው ጨዋታ በመድን ተሸንፎ ወደ ላይኛው ዲቪዚዮን ማለፍ ሳይችል ቀረ፡፡

ህንፃ ኮንስትራክሽን በ1ኛ ዲቪዚዮን ጥሩ ተወዳዳሪ ከሆነ በኋላ ቡድኑን ለቀቅኩ፡፡ በወቅቱ ህንፃን የለቀኩበት ምክንያት በጣም አስገራሚ ነው፡፡ በደርግ ዘመን በየመስሪያ ቤቱ በርካታ የመንግሥት ካድሬዎች ይገኙ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከስፖርት ኮሚሽን የመጡ ሹሞች የእግር ኳስ ክለቦችን እየዞሩ ይጎበኛሉ፡፡ በጊዜው ደግሞ ክለቡ የተሟላ የእግር ኳስ ፋሲሊቲዎች ነበሩት፡፡ የራሱ የሆነ ጥሩ ሜዳ እንዲሁም የተጫዋቾች ማደሪያ እና ማረፊያን አሟልቷል። ከኮሚሽኑ ከመጡት ካድሬዎች መሀል አንዱ ዶክተር ” ይህን ቡድን ማሰልጠን እፈልጋለሁ፡፡” አለ፡፡ ዶክተሩ የፖለቲካ ስልጣን የነበረው ስለሆነ የህንፃ ኃላፊዎች ጠሩኝና ” ሰውዬው ቡድኑን ያሰልጥን፣ አንተም ወደ መደበኛ ስራህ ተመለስ፡፡ ” አሉኝ፡፡ ዶክተሩ ህንፃን ማሠልጠን ሲጀምር እኔም የመተዳደሪያ መደበኛ ስራዬን በኮንስትራክሽን ድርጅቱ እየሰራሁ በእግር ኳሱ ግን ያለ ቡድን እና አሰልጣኝኝነት ስራ ቁጭ አልኩ፡፡ ያኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ በታችኛው ዲቪዚዮን ውስጥ ነበር፡፡ አንዳንድ የጊዮርጊስ የልብ ደጋፊ የሆኑ ሰዎችም እየመጡ “ይህ ክለብ ማሊያውን ለብሠህ የተጫወትክለት ቡድን ነው፡፡ ጊዮርጊስ ወደ ላይኛው ዲቪዚዮን ማደግ ይኖርበታል፡፡ አንተም ልታግዘን ይገባል፡፡” አሉኝ፡፡ በወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ፕሮፌሰር ሲሳይ ዘለቀ ነበር፡፡ እሱ ከለቀቀ በኋላ እኔ ቡድኑን ተረከብኩ፡፡ እኔም በህንፃ መደበኛ ስራዬን እየሰራሁ ጊዮርጊስን ማሰልጠን  ጀመርኩ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ክለቡን ወደ 1ኛ ዲቪዚዮን አሳደኩት፡፡ በጊዮርጊስ ቆይታዬ ልምምድ የማሰራው ከመደበኛው ስራዬ ስወጣ ከ11:00 በኋላ አልያም ደግሞ ወደ ስራ ከመግባቴ በፊት በሌሊት ነበር፡፡

በ1ኛ ዲቪዚዮን የህንፃ ኮንስትራክሽን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ግጥሚያ ቡድኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ 3-1 ድልን ተቀዳጀ፡፡ በጊዜው ጠንካራው ህንፃን ማሸነፍ ውድድሩን የመምራት ያህል ዋጋ ነበረው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በተገኘው ድል የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጠንካራ የማበረታቻ ሞራል ሲሰጡኝ እና የ”V” ምልክት እያሳዩኝ ሲጨፍሩ እኔም በምላሹ በጣቶቼ የ”V” ምልክት አሳይቼ በደስታ ከሜዳው ወጣሁ፡፡ ጨዋታውን ለማየት የህንፃ ካድሬዎች በሙሉ በስታዲየም ተገኝተው ነበር፡፡ በዕለቱ የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደስታ እና ጭፈራ ልዩ ነበር፡፡ በማግስቱ ሰኞ  በማለዳ ወደ መደበኛ ሰራዬ ሄድኩ፡፡ በሩ ላይ የተለመደው ፍተሻ ከተደረገ በኋላ እኔ ‘እንዳትገባ!’ ተባልኩ፡፡ ለምን? ብዬ ጠባቂዎቹን ስጠይቅ ‘አስተዳደሮች አስራት እንዳይገባ!’ ብለዋል፡፡ የሚል መልስ ሰጡኝ፡፡ እንግዲህ ትናንት ስላሸነፍኳቸው ተናደው ይሆናል ብዬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡በማግስቱም እንዲሁ ጊዮርጊሶችን በሌሊት ልምምዳቸውን አሰርቼ በሰዓቴ ወደ መስሪያ ቤቴ አመራሁ፡፡ የዕለቱ ጥበቃዎች በድጋሚ እንዳልገባ አደረጉኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳምንት አመላለሱኝ፡፡ እኔ አላወኩም እንጂ ለካ ታግጄ ኖሯል፡፡ የተለየ ያጠፋሁት ነገር አልነበረም፡፡ በደስታ ስሜት ያችኑ የ”V” ምልክት በማሳየቴ ካልሆነ በስተቀር፡፡ በኋላ እኔም ለ መ.ኢ.ሰ.ማ. “ያለ ምክንያት ከስራ ታግጃለው፡፡ ስለዚህም በቶሎ ወደ ስራ ገበታዬ ይመልሱኝ።” ብዬ ክስ ባቀርብም በመኢሰማ የነበሩት ካድሬዎች ስለሆኑ ክሴን ጭራሹኑ ሳያዩት ቀሩ፡፡ በዚሁ ምክንያት ከኮንስትራክሽን ድርጅቱ መደበኛ ስራዬ ወጣሁ፡፡ ጊዮርጊሶችም ይህን ተረድተው በወር 300 ብር ይከፍሉኝ ጀመር፡፡ ገንዘቡ ሙሉ ቤተሰብ ለማስተዳደር በቂ የነበረ ባይሆንም ከባዶ ይሻል ነበር፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን እያሰለጠንኩ ክለቡን ለተለያዩ ድሎች አበቃሁት፡፡ የአዲስ አበባ ሻምፒዮና፣ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎች ባለቤት ሆንን፡፡ ከዚያም ክለቡ ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ማለፉን አረጋገጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ በክለቡ ውስጥ አሉታዊ ነገሮች እየገጠሙኝ የመጡት፡፡ አላስፈለጊ አሉባልታዎች መናፈስ ጀመሩ፡፡ ”አስራት አዲስ እና ወጣት አሰልጣኝ ነው፡፡ ልምድ የለውም፡፡ የአፍሪካ ክለቦችን ስለማያውቅ ጊዮርጊስን ይዞ ለአህጉራዊ ውድድር መሄድ የለበትም፡፡” የሚሉ ትችቶች ማስተጋባት ተጀመረ፡፡ በጊዜው የነበሩት ስራ አስኪያጅ በቢሮአቸው አስጠርተውኝ ” አስራት – አንተ ለጊዮርጊስ ብዙ አድርገሀል። ለአፍሪካው ውድድር ግን ከወጣትነትህ እና ከልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ ብዙ ቅሬታዎች እየቀረቡብህ ነው፡፡ ቡድኑን ይዞ ሄዶ የተበላሸ ውጤት ከሚያመጣ ሰፊ ልምድ እና የአፍሪካን ኳስ የሚያውቅ አሰልጣኝ መምጣት ይኖርበታል፡፡ እኔ ከዚህ ብዙ እንድትርቅ አልፈልግም፡፡ ስለዚህም በወር 700 ብር እየከፈልንህ የ’B’ ን ቡድን ይዘህ እያሰለጠንክ ቆይ፡፡ ይህም ለቡድኑ ላደረከው አስተዋፅኦ የሚሆን ነው፡፡” የሚል ሀሳብ አመጡ፡፡ እጅግ በጣም ተበሳጨሁ። አሰብኩበትም፡፡ ለስራ አስኪያጁም ” ሀሳብዎን አድምጫለው፡፡ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎ ይፈቀድልኝ አልኳቸው፡፡ ”ጠይቅ፣ ምንም ችግር የለውም፡፡” አሉኝ ፡፡ እርስዎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ ነዎት፡፡አሁን በሚያገኙት ደመወዝ ላይ ጭማሪ ተደርጎልዎት የጠርሙስ ክፍል ኃላፊ ቢደረጉ ስራውን ይቀበላሉ ወይ? ብዬ ጠየኳቸው፡፡ ” አይ ይህማ የሞራል ጥያቄ ነው፡፡ አልሰራም!!! ምን ማለትህ ነው? ከላይ ወደ ታች…….!!! ጠርሙስ ክፍል!! ” የሚል ምላሽ ሰጡኝ ፡፡ እኔም “እንግዲያውስ የኔም የሞራል ጥያቄ ነው፡፡ ከዋናው ቡድን ዋና አሰልጣኝነት አንስታችሁ የ ‘B’ ቡድንን አሰልጥን ስትሉኝ ምን ያህል ስሜቴ ሊጎዳ እንደሚችል ልትረዱ በተገባ ነበር፡፡ እኔም እንደርስዎ ሞራል ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ” አልኳቸው ፡፡በመልሴ በጣሙን አዘኑ፡፡ ተሰማቸውም፡፡ ” እሺ ምን ላድርግ? ” ብለው ጠየቁኝ፡፡ ” ምንም አያስቡ፡፡ እሄዳለሁ፡፡ ለእስካሁኑም አመሰግናለሁ፡፡” አልኳቸው፡፡ ” አይ እንዲሁማ አንሸኝህም፡፡ ” አሉኝ፡፡ቀደም ብለው ተዘጋጅተው ስለነበር የምሳ ግብዣ ተደርጎ ተለያየን፡፡ እኔም ጊዮርጊስን ለቅቄ ቁጭ አልኩ፡፡

በዚያኑ ሰሞን የቀድሞ ክለቤ ህንፃ ሰዎች ቤቴ መጡ፡፡ የመጀመሪያ ልጄ ተቀበለቻቸው፡፡ ሰዎቹ የድርጅቱ ትልቁ የፖለቲካ ሰው እና የቡድን መሪው ነበሩ፡፡ የቡድን መሪው በጣም የምወደው እና የማከብረው ሰው ነበር፡፡ ገና ከውጪ መኪናቸው ውስጥ አይቻቸው ልመለስ ስል ቡድን መሪው ሮጦ መጥቶ በሩን ያዘብኝ እና አስቆመኝ፡፡ ምን ፈልጋችሁ መጣችሁ ብዬ በእልህ አለቀስኩ፡፡ ቡድን መሪውም ” አስራት – የመጣነው ይቅርታ ልንጠይቅህ ነው፡፡ ሰዎች አሳስተውን አጥፍተናል፡፡ኃላፊው (አቶ ሽብሩ) የመጡት ይቅርታህን ፈልገው ነው፡፡ የህንፃ ኮንስትራክሽን ሰዎች በሙሉ ተመልሰህ እንድትመጣ ይፈልጋሉ፡፡ ደሞዝህ ጭማሪ በማድረግ ያስተካክሉልሃል ፣እስካሁን ያልተከፈለህ የአመት ከወራት ደመወዝ እንዲከፈልህ ይደረጋል፡፡” አለኝ፡፡ ባለቤቴን አማከርኳት፡፡ እሷም ” አሁን እየተቸገርን ያለበት ወቅት ነው፡፡ ስራ የለህም። ስለዚህ ተቀበላቸው፡፡” አለችኝ፡፡ ምክንያትም እውነትም ነበራት፡፡ ቤቱን የማስተዳድረው እኔ ነበርኩ፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን ተቀበልኩና ወደ ህንፃ አሰልጣኝነት ተመለስኩ፡፡ቃላቸውን ጠብቀውም 420 ብር ወርሀዊ ደመወዜን ስራ ላይ ባልነበርኩባቸው ወራት አባዝተው ከፈሉኝ፡፡ ብዙ ገንዘብ የቆጠርኩትም ያን ግዜ ይመስለኛል፡፡ የወር ክፍያዬ ወደ 750 ብር አደገልኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ህንፃ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ወርዶ ነበር፡፡ እኔም ጠንክሬ አሰርቼ ወደ 1ኛ ዲቪዚዮን መለስኩት፡፡

በአንድ ወቅት ህንፃ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ሆኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የዲቪዚዮን ዋንጫን ድል አድርጎ ለአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፍፃሜ ተገናኝተን በመጀመሪያው ጨዋታ እኛ አሸነፍን፡፡ ቀደም ባሉት አመታት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ የሚደረገው አንድ ጊዜ ብቻ የነበረ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫው አሸናፊ እንዲሆን ስለተፈለገ ብቻ ጨዋታው እንደገና መደረግ አለበት ተባለና በድጋሚ ተደረገ፡፡ የተወሰኑ የህንፃ ተጫዋቾች እንዲያውም በከፍተኛ የደስታ ስሜት ሆነው በተጋጣሚያችን (ጊዮርጊስ) ደጋፊዎች ፊት የውስጥ ሱሪ እስከ ማውለቅ የደረሱ ነበሩ፡፡ አንዳንድ የጊዮርጊስ ደጋፊዎች በተጫዋቾቹ የደሰታ አገላለጽ ተበሳጭተው የክለቡን የስፖርተኞች ሰርቪስ በድንጋይ እንዳልነበር አደረጉት፡፡ ጨዋታውን በድጋሚ የማድረግ ግዴታ ውስጥ እንድንገባ የተደረገበት ውሳኔ የተላለፈው በሜዳው ውስጥ እያለን ነበር። አብዛኞቹ የቡድኔ ተጫዋቾች ቀጣዩን የመልስ ጨዋታ ለማድረግ ብቁም ዝግጁም አልነበሩም። እያነከሱ ከሜዳ ከወጡት ሌላ ለፍጻሜው ጨዋታ ያላቸውን በሙሉ የሰጡና እጅግ የተዳከሙ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በማግስቱ በተደረገው ሁለተኛ ግጥሚያ ጊዮርጊሶች አሸንፈው ዋንጫውን ወሰዱ፡፡ ይሄን ሁሌም የማልረሳው ታሪክ ነው፡፡

ከህንፃ ኮንስትራክሽን በመቀጠል ያሰለጠንኩት ሜታ ቢራን ነው፡፡ የ100 ብር ልዩነት የነበረውን የተሻለ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ ተቀብዬ ህንጻን ለቅቄ ወደ ሜታ አመራሁ፡፡ ቡድኑ ውድድሩን የሚያደርገው በአዳማ ነበር፡፡ በክለቡ የተሳካ ቆይታ ነበረኝ፡፡ ሜታን በእኔ አሰልጣኝነት ዘመን የሸዋ ሻምፒዮና እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤት እንዲሆን አድርጌዋለው፡፡ የጊዜው የአዲስ አበባ ጥሎ ማለፍ አሸናፊ የነበረው ቡና ነበር፡፡ በዋና ከተማዋ በሚደረገው ይህ የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ አሸናፊዎች ፍጻሜ ሜታ ቢራን እና ቡናን አገናኘ፡፡ ቡና 1-0 አሸንፎ ዋንጫውን ወሰደ፡፡ ያን ጊዜም በሜታ ቢራ ላይ ግፍ ተሰርቷል፡፡ ዝርዝሩን በአጭሩ ላስቀምጥ፡፡ የሜታ ተከላካይ አብዶ ሰርቶ ሲያልፍ የቡናው ሙሉጌታ ወልደየስ ይጠልፈውና ኳሱን ይቀማዋል፡፡ የመሀል ዳኛው ተስፋዬ ገ/የሱስ ጥፋት ብሎ ማስቆም ነበረበት፡፡ ቦታው ለእኛ የፍ.ቅ.ምት የሚያሰጥ ነበር። ፍ.ቅ.ምቱን ቢሰጠን ኖሮ ጨዋታውን የማሸነፍ እድል ይኖረን ነበር፡፡ ተስፋዬ ግን ሳይወስንልን አለፈው፡፡ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ‘አቶ ተስፋዬ ልክ ነህ? ውሳኔህስ ፍትሀዊ ነበር?’ ብዬ ጠየኩት፡፡ እሱም ‘ስማ አስራት አንተ ሸዋ ነህ፣ ሜታ ነህ፣ ማንም ያውቅሀል፡፡ ቡናን የመሰለ ቡድን የሚደግፍ ይህ ሁሉ ደጋፊ ከሚያዝን አንተ እዚህ ምንም ደጋፊ የሌለህ ብታዝን ይሻላል፡፡’ አለኝ፡፡ በንዴት ብግን ብዬ የነበርኩትን ሰውዬ በሳቅ አበረደኝ፡፡ ይህም መቼም የማልዘነጋው ትውስታዬ ነው፡፡

ከሜታ ቢራ በመቀጠል እርሻ ሰብል፣ ፊናንስ ፖሊስ፣ በድጋሚ ቅዱስ ጊዮርጊስን(ለ9 አመታት)፣ አየርመንገድ፣ መከላከያ፣ መብራት ሐይል፣ ባንክ፣ መድን እና ደደቢት የአሰልጣኝነት ህይወቴን ያሳለፍኩባቸው ክለቦች ናቸው፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ  ደግሞ የተስፋውን፣ የወጣቱንና ዋናውን ቡድኖች አሰልጥኛለው፡፡

አስራት ኃይሌ እና ሰር ቦቢ ቻርተን

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመልሼ በምሰራበት ወቅት ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚወዳደረው የታችኛው የሊጉ ደረጃ በነበረው የከፍተኛ ዲቪዝዮን ነበር፡፡ ቀደም ባለው አመት (1989) በቀጣዩ የውድድር አመት (1990) በአዲሱ ፎርማት የሚደረግ ውድድር ስለመጀመሩ ለክለቦች የደረሰን በቂ መረጃ አልነበረንም፡፡በ1989 ጊዮርጊስ 1ኛ ዲቪዚዮኑን እየመራ በነበረበት ሁኔታ 5 ወይም 6 የሚደርሱ ተጫዋቾች ጣልያን ላይ ይጠፋሉ፡፡ እኔ ደግሞ ኮርስ ልወስድ ወደ ኡጋንዳ ሄጃለው፡፡ ሰር ቦቢ ቻርተን የከፍተኛ ደረጃ (High Level) የአሰልጣኞች ኮርስ ይሰጥ ነበር፡፡ ከኡጋንዳ  ስመለስ ጊዮርጊስ በውድድሩ 4ኛ ደረጃን ይዞ ጠበቀኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ”በሚቀጥለው አመት (1990) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ይጀመራል፡፡ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የሚወጡት ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡” የሚል መረጃ መጣ፡፡ አመቱ ሲጠናቀቅ ጊዮርጊስ 5ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ በመጨረስ ፕሪምየር ሊግ ሳይገባ ቀረ፡፡ መብራት ኃይል፣ ቡና እና መድን የመጀመሪያውን አመት የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎን አሳኩ። ጊዮርጊስም የከፍተኛ ዲቪዝዮን ቆይታውን ለአንድ አመት ቀጠለ፡፡

በክልል ክለቦች ሻምፒዮና አንድም ጊዜ ሳንሸነፍ በፍፃሜው ድሬደዋ ላይ ሙገርን አሸንፈን ሻምፒዮን ሆነን በ1991 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተቀላቀልን፡፡ እንደሚታወቀው ጊዮርጊስ የብዙ ደጋፊዎች ባለቤት ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በጊዜው ይህንን የሚፈልገው አልነበረም። በኢትዮጵያ ሻምፒዮና አብዛኞቹ ደጋፊዎቻችን በሄድንባቸው  ቦታዎች ሁሉ በመገኘት ከፍተኛ ድጋፋቸውን ይሰጡን ነበር፡፡ ቫርኔሮ፣ አባሰኒ እና ሌሎች ጫካማ ቦታዎች የበዙባቸው ሜዳዎች ላይ ነበር እየመጡ የሚደግፉን፡፡ እኛም ተወደደም ተጠላም ጊዮርጊስን ወደ ፕሪምየር ሊግ በመጣበት አመት በቶሎ ቻምፒዮን አደረግነው፡፡ በሰዓቱ በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ፉክክር እና ጎበዝ አሰልጣኞች ነበሩ፡፡ ሁሉም አሰልጣኞች ተጫዋቾቻቸውን በርትተው ያሰሩ ነበር፡፡ ተጫዋቾችም የአሰልጣኞችን ስራ ለማቅለል እና ትዕዛዛትን በአግባቡ ለመፈፀም የሚለፉና የሚተጉ ነበሩ፡፡ በርካታ አሰልጣኞች ለውጤት የመልፋትና የመድከም ጉጉት ያደረባቸው ነበሩ፡፡ መንግስቱ ወርቁ፣ ስዩም አባተ፣ ካሳሁን ተካ፣ ሐጎስ ደስታ እና ወንድማገኝ ከበደ በፕሪምየር ሊጉ ጅማሮ ከለቦችን እያሰለጠኑ የውድድሩን ደረጃ ያሳደጉ ናቸው፡፡ ከአብዛኞቹ ጋር በተጫዋችነት ዘመናችን ጠንካራ ትውውቅ ነበረን፡፡በአሰልጣኝነት ጊዜያችንም ቀጥተኛ መተዋወቅ ፈጥረናል። ሁላችንም በየክለቦቻችን ምን ስራ ላይ እንደምናተኩርም ይታወቅ ነበር፡፡

የእኔ ቡድን በአብዛኛው የአካል ብቃት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ተጫዋቾቼ ሁለት 90 ደቂቃዎች የመጫወት አቅም ነበራቸው፡፡ ቡድኔ 3 ጎሎች ቢቆጠርበት 4 አስቆጥሮ እና ማሸነፍ እንደሚችል ከፍተኛ እምነትና እርግጠኝነት ነበረው፡፡ አብዛኛዎቹ ተጋጣሚዎቼን እያሳመንኩ ነበር የማሸንፈው፡፡በወቅቱ ቡና ምርጥ ቡድን ነበር፡፡ ሌሎችም ጠንካራ ተፎካካሪዎች የነበሩ ሲሆን ብዙዎቹ ክለቦች በርካታ አነሳሽ ደጋፊዎች ነበሯቸው፡፡ የሐጎስ ደስታው መብራት ኃይል እጅግ ጥሩ ቡድን ነበር፡፡ ቡድኔ ጨዋታ በማይኖረው ጊዜ የሌሎች ቡድኖችን ጨዋታዎች በመገምገም እይታ እመለከት ስነበር የሚያመልጠኝ ጨዋታ አልነበረም። የተጋጣሚን ቡድን አጨዋወት በጥልቀት ለማወቅ ተመራጭ ፎርሜሽንን፣ የቋሚ ተሰላፊዎችንና ታክቲካዊ አቀራረብን የተመለከቱ መረጃዎችን እመዘግብ ነበር፡፡ ቀጣይ ተጋጣሚዎቼን ሰገጥምም በደንብ ተዘጋጅቼ ነው የምቀርበው፡፡ በነበረን ቅርርብ መሠረትም አንዳንድ አሰልጣኞች ከስራችን ጋር በተገናኘ በግልፅ እንነጋገር፣ እንከራከር፣ በጠንካራና ደካማ ጎኖቻችን ዙሪያም እንወያይ ነበር፡፡

አዳዲስ ነገሮችን የመሞከር ዝንባሌ ነበረኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጫዋቾቼን የአካል ብቃት ልምምድን በጂም ያሰራሁት እኔ ነበርኩ፡፡በኤግዚቢሽን ማዕከል የጂም መሳሪያዎች አይቼ ከነጋዴዎቹ ጋር በመነጋገር  በአንድ ሰዓት የእኔ አደረኩት። እቃው በአንድ ጊዜ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ዘመናዊ የአካል ብቃት ልምምድን እንዲያደርጉ ያግዘን ነበር፡፡ ወደ 25 ሺህ ብር በሚጠጋ ሒሳብ ከፋይናንስ ክፍሉ ጋር በፍጥነት ጉዳዮችን በመጨረስ የእኔ አደረኩ፡፡ ቀድሞ በነበረኝ ልምድ የውጭ መጽሐፎች ስመለከት የአካል ብቃት ስራ በዘመናዊ መሳሪያዎች ማሠራት በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ግንዛቤው ነበረኝ፡፡ እኔ ራሴ የክብደት ስራዎችን እሰራ ነበር፡፡ የአካል ብቃት ስራ እወዳለው ፤ በተጫዋችነት ዘመኔ ሁሌም ከ75-80 ኪ.ግ ባለው የክብደት መጠን ውስጥ ነበርኩ፡፡በተጫዋችነት ዘመኔ ሁሌም ጥሩ ጉልበት ነበረኝ፡፡ያው ‘ጎራዴው’ የተባልኩትም ከዛ በመነጨ ነው፡፡

ተጫዋቾቼ በአካል ብቃት ረገድ የተሻሉ እንዲሆኑ እፈልጋለው፡፡ ከክብደት ስራ ጋር በተገናኘ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች በምን ያህል ደረጃ መሆን እንዳለበት ከመፅሐፎች ላይ በማንበብ መረጃዎችን አገኝ ነበር፡፡ ተጫዋቾቼን በአቀበት ላይ የትንፋሽ ስራን አሰራቸው ነበር ፤ የተለያዩ ክብደት ያላቸው ነገሮችን (sand jacket) በማስያዝ ዳገት እንዲወጡ አደርጋቸው ነበር፡፡ ተጫዋቾቹ ከፍተኛ ጉልበት እንዲኖራቸው እና የአካል ብቃታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ያግዛቸው ነበር፡፡ ሆኖም በኋላ ላይ በዚሁ ስራዬ እታማ ጀመር፡፡ “አስራት ተጫዋቾችን ተራራ ያስሮጣቸዋል፡፡” የሚል ወቀሳና ትችት ተከተለ፡፡ልምምዱ ቢያስተቸኝም ለዘጠኝ አመታት ውጤታማ ቡድን ስገነባ የማሰራው ይህን መሠል የአካል ብቃት ስራ ነበር። ሌሎች ቴክኒካዊ፣ ታክቲካዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ የማተኩረውን ያህልም ለአካል ብቃት ልዩ ትኩረት እሰጥ ነበር፡፡ ቡድኔ በረጅም ኳስ እንደሚጫወት ቢነገርም የአጭር ኳስ ጨዋታንም ይተገብር ነበር፡፡ ”አስራት የሚሰራው የሚጠልዝ ቡድን ነው፡፡” እየተባለ ቢወራብኝም ቡድኔ በወቅቱ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን በጥሩ ሁኔታ በመተግበሩ የመጣ ትችት ነበር፡፡ በምተገብረው አጨዋወት ከአሰልጣኞች ጭምር ወቀሳ ይቀርብብኝ ነበር፡፡ እኔም ”ቀዶ ጥገናው ጥሩ ነበር፣ በሸተኛውን ግን ማትረፍ አልቻላችሁም፡፡’ እያልኩ እተርትባቸዋለው፡፡ ” ውጤቱ እኮ እኔ ጋር ነው ያለው፡፡ እናንተ የኔን አጨዋወት ጠንካራና ደካማ ጎኖች ማጥናት እና ለዛ መዘጋጀት ነው ያለባችሁ፡፡” እላቸዋለው፡፡ ብዙዎቹ ማለትም ጋዜጠኞች፣ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች የጨዋታ ዘይቤዬ ባይመቻቸውም እኔ ግን ዘላቂ ውጤት አመጣበት ነበር፡፡ የእግር ኳስ ትልቁ ፍሬ ነገር ውጤት ነው፡፡ እነ ስዩምም ሆነ መንግሥቱ ከፍልስፍናዬ ጋር በተገናኘ ለሚሰጡት አስተያየት ምላሽ የምሰጠው ውጤት በማምጣት ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ንትርኮች እና የሀሳብ አለመግባባቶች መሀል ውስጥ ሆነን እንኳ ጥብቅ ትስስር ነው የነበረን፡፡ ቂም መያያዝ  የሚባል ነገር አልነበረብንም፡፡ የምንታየውም ቁጭ ብለን ስናወራና ስንጨዋወት ነው፡፡ በመካከላችን የነበረው ትግልና ፉክክርም ኃይለኛ የነበረ ቢሆንም ሰላማዊ ነበር። ደስታዬ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ አልነበረም፡፡ ውድድሩ ሲያልቅ በማመጣው ዋንጫ ነበር ይበልጥ የምደሰተው፡፡

ተጫዋቾችን በዕኩል አይን እመለከታለው፡፡ ጥሩ ብቃት በማሳየት በሚመጣ የህዝብ ድጋፍና መወደድ የሚከተል ስንፍና በተጫዋቾቼ ውስጥ እንዲኖር አልሻም፡፡ በልምምድ ሰዓት የሚያለምጥ እና የሚዘገይ ተጫዋች እንዲኖረኝ አልፈልግም፡፡ በመከባበር ላይ የተመሠረተ የተጫዋቾች የርስ በርስ የግንኙነት መስመር አበጃለው፡፡ ደጋፊዎችም በልምምድ ሜዳ ከተጫዋቾቹ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ አላደርግም፡፡ በዚህ መልኩ ነው እንግዲህ ስሰራ የቆየሁት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *