በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሀ ግብሮች መሀከል የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የድሬደዋ ከተማ ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ከተላለፈ በኃላ ዛሬ የሚደረግ ይሆናል። ይህን ጨዋታ እንደተለመደው በቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
ብሔራዊ ቡድናችን በቻን 2018 ተሳትፎ ለማድረግ በነበረበት የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአራት በላይ ተጨዋቾችን በማስመረጡ በወቅቱ ሳይካሄድ የነበረው ጨዋታ ዛሬ በኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን መሪነት ሲደረግ ሁለቱም ቡድኖች ከሽንፈት መልስ የሚገናኙ ይሆናል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት እንዲሁም ድሬደዋ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሊያደርጓቸው የነበሩት የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከተላለፉ በኃላ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ሻምፒዮኖቹ ወደ ሶዶ አምርተው በወላይታ ድቻ 2-1 ሲሸነፉ ድሬዎችም በሜዳቸው በኢትዮጵያ ቡና 2-0 ድል ተደርገዋል። ከሶስት ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በኃላ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የሚመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከገጠመው ሽንፈት በኃላ ወደ አሸናፊነቱ ለመመለስ የሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል። የትናንትናውን የደደቢትን ሽንፈት ተከትሎም ቡድኑ ወደ መሪው ለመጠጋት መልካም አጋጣሚ የተፈጠረለት ይመስላል። ይህ ውጤት ጨዋታው ሁለተኛ ሽንፈትን ላለማስተናገድ ከመደረጉ ባለፈ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሻምፒዮንነት ጉዞ ከማቃናት አንፃር የጨዋታውን አስፈላጊነት የሚያጎላው ነው የሚሆነው። አሁንም ከሁለተኛው ሳምንት የጅማ አባ ጅፋሩ ድል በኃላ በሌላ ጨዋታ ማሸነፍ የተሳነው ድሬደዋ ከተማ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው የመጨረሻ ሶስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስቆጥር ለመሸነፍ ተገዷል። አምና 9ኛው ሳምንት ላይ በተመሳሳይ መርሀግብር 3-0 ተሸንፈው የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ለቡድኑ አዲስ አይነት መነቃቃትን የሚፈጥር እና ለቀጣይ ጉዟቸው መሰረት የሚጥል ውጤት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አሉላ ግርማ ፣ አዳነ ግርማ እና አሜ መሀመድ ከጉዳት የተመለሱ ሲሆን የድሬደዋ ከተማው ሳውሬል ኦልሪሽም ለጨዋታው ብቁ ሆኖ አዲስ አባባ ተገኝቷል። ከዚህ ውጪ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላዲን ሰይድ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ታደለ መንገሻ እንዲሁም የድሬደዋ ከተማዎቹ ዘነበ ከበደ ፣ ሀብታሙ ወልዴ እና ሳምሶን አሰፋ አሁንም ከረዥም ጊዜ ጉዳታቸው አላገገሙም።
ምንአልባት ጨዋታው በመጀመሪያ ሳምንት ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ ድሬደዋ ከተማ የአማካይ ክፍሉን በእጅጉ ወደ ተከላካይ መስመሩ አስጠግቶ የሚከላከልበት ቅዱስ ጊዮርጊስም በተጋጣሚው ሜዳ ላይ በመቆየት ሙሉ ለሙሉ ጫና ፈጥሮ የሚጫወትበት እንደሚሆን ይገመት ነበር። አሁን ላይ ያለው ድሬደዋ ከተማ ግን የማጥቃት ፍላጎት የሚታይበት ነው ማለት ይቻላል። ቡድኑ ምንም እንኳን አሁንም መጀመሪያ ይከተለው ከነበረው አጨዋወት ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ወጥቷል ማለት ባይቻልም በተጨዋች ምርጫውም ሆነ በአቀራረቡ በአሰልጣኝ ስሞኦን አባይ ስር በለውጥ ላይ ይገኛል። በለውጥ ላይ ከመገኘት አንፃር ቅዱስ ጊዮርጊስም ሙሉ ለሙሉ ወደ ሚፈልገው አጨዋወት ያልመጣ በመሆኑ በሁለቱ ተጋጣሚዎች መሀከል መመሳሰል ይታያል። እንደየተጋጣሚው አይነት የኳስ ቁጥጥርን መሰረት በማድረግ እንዲሁም ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ሲጫወት የሚታየው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለቱ ተቃራኒ አካሄዶች መሀል እየዋለለ ያለ ይመስላል። ሁለቱን አቀራረቦች እንደ አማራጭ መያዙ ከተገማችነት የሚያርቀው ቢሆንም በተጨዋቾች መሀከል የሚኖረውን የሜዳ ላይ መግባባት ሙሉ ትኩረቱን በተመሳሳይ አጨዋወት ላይ ባደረገ ቡድን ልክ ለማድረግ እንዲቸግረው አድርጎታል።
በዛሬው ጨዋታ እንደሌሎቹ ጊዜያት ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለመውሰድ በመሞከር እንደሚጀምር ይገመታል። ቡድኑ ሰሞኑን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ ግቦችን የሚያስቆጥርበት መንገድም የዕቅዱ አካል ሊሆንም ይችላል። ሁለት የፊት አጥቂዎችን የሚጠቀሙት ድሬደዋ ከተማዎች አማካይ ክፍል ላይ የሚኖራቸው የቁጥር ብልጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አጥቂዎች ተሳትፎ የማይካካስ ከሆነ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሊጠቅማቸው ይችላል። ዘላለም ኢሳያስ ከሙሉአለም መስፍን እንዲሁም ሱራፌል ዳንኤል እና ዮሴፍ ደሙዬ ወይንም በቦታው ሊሰለፉ የሚችሉ ሌሌች የመስመር አማካዮች ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ በጨዋታው ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮችም ከድሬደዋው የተከላካይ አማካይ ኢማኑኤል ላርያ ፊት በኳስ ቁጥጥር ወቅት የሚኖራቸው ነፃነት ወደ ሶስቱ የፊት አጥቂዎቻቸው ለሚሰራጩ ኳሶች ወሳኝነት ይኖረዋል። እዚህ ላይ የእንግዶቹ ሌሎች አማካዮች የመከላከል ተሳትፎ በቡድኑ ላይ የሚኖረውን ጫና ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ይታመናል። በጥቅሉ ከመሀል ሜዳ ቅብብሎች በሚነሱ ኳሶች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመስመር አጥቂዎቻቸው አማካይነት ወደ ጎን አስፍተው ድሬደዋዎች ደግሞ ወደ መሀል በጠበበ መልኩ የፊት አጥቂዎቻቸውን ለማግኘት በመሞከር የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ይጠበቃል።