ቻን 2018፡ ሞሮኮ እና ናይጄሪያ ለፍፃሜ አለፉ

በቶታል የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች እረቡ ምሽት ካዛብላንካ እና ማራካሽ ላይ ተደርገው አዘጋጇ ሞሮኮ እና ናይጄሪያ ወደ ፍፃሜ ማምራተቸውን ያረጋገጡበት ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ የ2014 ቻምፒዮኗ ሊቢያ እና ሱዳን ለፍፃሜ ለማለፍ ያደረጉት ጥረት ከሽፏል፡፡

በስታደ መሃመድ አምስተኛ ሞሮኮ ሊቢያን ገጥማ በጭማሪ 30 ደቂቃ ላይ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች 3-1 አሸንፋለች፡፡ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ በተገናኙት ሁለቱ ሃገራት የሞሮኮው የፊት አጥቂ አዩብ ኤል ካቢ አሁንም ግብ በማስቆጠሩ ቀጥሎበታል፡፡ ኤል ካቢ ሞሮኮን በ73ኛው ደቂቃ መሪ ሲያደርግ የሞሮኮው ግብ ጠባቂ አንስ ዚኒቲ በ86ኛው ደቂቃ በሰራው ስህተት ሊቢያዎች በአብዱልራህማን ፊቶሪ ግብ አቻ ሆነዋል፡፡ መደበኛው 90 ደቂቃ 1-1 መጠናቁቅን ተከትሎ ሃገራቱ ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ ያመሩ ሲሆን ልማደኛው ኤል ካቢ ከማዕዘን ተሸግሮ ተጭርፎ የማጣን ኳስ ከግቡ አፋፍ ላይ አግኝቶ በማስቆጠር ሞሮኮን ዳግም መሪ ሲያደርግ ጨዋታው ከመገባደዱ ሁለት ደቂቃዎች አስቀድሞ ዋሊድ ኤል ካርቲ በፍፁም ቅጣት ምት  ጨዋታውን ደምድሟል፡፡ ኤል ካቢ በውድድሩ 8 በማድረሰ በቻነ ታሪከ ቡዙ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ሆኗል፡፡

በክረምት ወር በቦቶላ 2 ከሚወዳደረው ሬሲንግ ደ ካዛብላንካ ለቆ ሬኔሳንስ ስፖርቲቭ ደ በርካን አቅንቷል፡፡ በርካን በሞሮኮ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ፋውዚ ሌካ ፕሬዝደንትነት የሚተዳደር ክለብ ነው፡፡ ሞሮኮ ወደ ቻን ፍፃሜ ስታልፍ የመጀመሪያዋ ስትሆን ውድድሩን ማሸነፍ ከቻለች የመጀመሪያዋ አዘጋጅ ትሆናለች፡፡

ናይጄሪያ በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠረችው ግብ ሱዳንን 1-0 በመርታት ወደ ፍፃሜ አምርታለች፡፡ ጋብርኤል ኦኬቹኩ በ17ኛው ደቂቃ ከመረብ ያዋሃደው ግብ የሁለቱ ሃገራት ልዩነት ሆኗል፡፡ በጨዋታው ሱዳን ከናይጄሪያ ብትሻልም ግብ ለማስቆጠር ግን ስትቸገር ተስተውሏል፡፡ የናይጄሪያው ኢፋኒ ኢፋኒ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ከወጣ በኃላ ሱዳኖች የተገኘውን የቁጥር ብልጫ መጠቀም አልቻሉም፡፡ ባክሪ ባሽር ባክሪ ከሱዳን በኩል በቀጥታ ቀይ በ87ኛው ደቂቃ ተወግዷል፡፡

የፍፃሜ ጨዋታ ካዛብላንካ ላይ እሁድ ሲደረግ የደረጃ ጨዋታው ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ይካሄዳል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *