የኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 8ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አባባ ስታድየም በተካሄደ አንድ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አዳማን 1-0 በማሸነፍ አስመዘገቧል።
ባለሜዳዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድል በመፍጠር ተሽለው በቀረቡበት የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቤተልሔም ሰማን 8ኛው ደቂቃ ላይ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝታ ራሷ መጠቀም ስትችል ለቡድን አጋሯ እሰጣለው ብላ ረዝሞ ወደ ውጭ የወጣው ኳስ በጨዋታው ጎል ሊሆን የሚችል የመጀመርያ አጋጣሚ ነበር። የአዳማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ይርጋሸዋ ከግብ ክልሏ ውጭ ኳሰ በመያዟ የተሰጠውን ቅጣት ምት ወርቅነሽ ሜልሜላ ሳትጠቀምበት የቀረችው ሙከራም የ15ኛው ደቂቃ ሌላ የፈረሰኞቹ የጎል አጋጣሚ ነበር።
ፈረሰኞቹ እንደወሰዱት የማጥቃት ጫና በ21ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው በአዳማ የግብ ክልል ውስጥ ቱቱ በላይ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ጎሎች እያስቆጠረች በድንቅ አቋም ላይ የምትገኘው ቤተልሄም ሰማን ወደ ጎልነት ቀይራ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።
በአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች እና በአጥቂዎች መካከል ምንም አይነት ግኑኝነት ባልነበረበት የመጀመርያው አጋማሽ አዳማዎች በተለያዩ ደቂቃዎች ሁለት ጊዜ ከረጅም ርቀት መቅደስ ማሞ የሞከረቻቸው ኳሶች በቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ናርዶስ ክንፈ አማካኝነት ሊከሽፉ ከቻሉት ሙከራ ውጭ ሌላ የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 መሪነት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ አዳማዎች የነበረባቸውን ድክመቶች በሚገባ አሻሽለው ተሽለው የቀረቡበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲሆን በተለይ 61ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ ገነት ኃይሌ ከ25 ሜትር ርቀት በግሩም ሁኔታ አክርራ የመታችውና የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ናርዶስ ክንፈ እንደምንም ያወጣችው ኳስ አዳማዎችን አቻ ማድረግ የሚችል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በሚያደርጉት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለይ የደጋፊው ድጋፍ ተጨምሮበት ተጋግሎ የቀጠለው ጨዋታ አዳማዎች ወደ ጨዋታው ማጠቃለያ ላይ ተቀይራ በገባችው አስካለ ገ/ፃድቅ አማካኝነት ያገኙትን መልካም የጎል አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ፈረሰኞቹ ውጤቱን ለማስጠበቅ እየተከላከሉ በሚያገኙት አጋጣሚ የሚፈጥሩት የማጥቃት መንገድ ያልተሳካ በመሆኑ ተጨማሪ ጎል ሳያስቆጥሩ ጨዋታውን 1 – 0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ በ1ኛው ሳምንት ጌዲዮ ዲላን ካሸነፉ በኃላ ከድል የራቁት እንስቶቹ ፈረሰኞች ወደ ድል በመመለስ ደረጃቸውን አሻሽለው ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችሉ በአንፃሩ አዳማዎች በ3ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌትሪክን ከረቱበት ድላቸው መልስ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ተስኗቸዋል።