የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በብቸኝነት በሚያስተናግደው ጨዋታ 10፡00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከተማ በአዲስ አበባ ስታድየም ይገናኛሉ። ይህን ጨዋታ በዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
የሁለቱ ክለቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት አምና ሶስተኛው ሳምንት ላይ የተገናኙበትን ጨዋታ ያስታውሰናል። በወቅቱ የሊጉ ክስተት የነበረው ፋሲል ከተማ በኤርሚያስ ሀይሉ ብቸኛ ጎል አሸናፊ መሆኑ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የአምናውን ያህል ባይሆንም ዘንድሮም ጥሩ የሚባል አጀማመር አድርጎ የነበረው ፋሲል በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና የደረሰበት ተከታታይ ሽንፈት ቀጣይ ጉዞውን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ቢሆንም ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን በሜዳው አስተናግዶ ማሸነፉ ለዛሬው ጨዋታ ጥሩ መነቃቃትን እንደሚፈጥርለት ይታሰባል። ኢትዮጵያ ቡናም ከድል ርቆ ከቆየባቸው ጊዜያት በኃላ ማገገም የቻለው በ13ኛው ሳምንት ወደ ድሬደዋ ተጉዞ በሳካው የ 2-0 ድል ነው። በመሆኑም በኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃ/ስላሴ የመሀል ዳኝነት የሚደረገው የዛሬው ጨዋታ ከአሸናፊነት የተነለሱ ቡድኖችን የሚያገናኝ በመሆኑ ሁለቱም በጥሩ መንፈስ አሸናፊነታቸውን ለማስቀጠል እንደሚፎካከሩ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው ማሸነፍ ከቻለ የተረጋጋ ውጤት ወደ ማስመዝገብ ከመመለስ ባለፈ ነጥቡን 18 በማድረስ ከተጋጣሚው በመቀጠል ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። ዘንድሮ በአዲስ አበባ ስታድየም ምንም ሽንፈት ያልገጠማቸው አፄዎቹም ሶስት ነጥብ ይዘው መመለስ ከቻሉ ከ 20 በላይ ነጥብ መሰብሰብ ከቻሉት ከበላያቸው ካሉ አምስት ክለቦች ጋር የሚቀላቀሉ ይሆናል።
መጠነኛ ልምምድ የጀመረውን አክሊሉ አያናውን ጨምሮ አለማየው ሙለታ ፣ ሮቤል አስራት እና ማናዬ ፋንቱ በጉዳት ምክንያት ዛሬ ለኢትዮጵያ ቡና አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ተጨዋቾች ናቸው። በፋሲል ከተማ በኩል አሁንም ማገገም ካልቻሉት ያሬድ ባየህ እና አይናለም ኃይለ በተጨማሪ አብዱርሀማን ሙባረክ እንዲሁም ዳዊት እስጢፋኖስ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ እንደማይሰለፉ ሰምተናል።
ኢትዮጵያ ቡናም ሆነ ፋሲል ከተማ 4-3-3 የመጀመሪያ ምርጫቸው ነው። ሆኖም ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጪ የሚኖረው አቀራረብ ከተጋጣሚው ፍፁም የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ለሙሉ በኳስ ቁጥጥር ላይ የሚመሰረት ቡድን እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ፋሲሎች ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ ፈጣን በሆነ ያማጥቃት ሽግግር ተጋጣሚን በመፈተን ይታወቃሉ። በመሆኑም በአሰላለፍ ደረጃ የሚመሳሰሉት የዛሬዎቹ ተጋጣሚዎች የአቀራረባቸው መለያየት እና የተጨዋቾቻቸው ቦታ አያያዝ አንዳቸው ለሌኛቸው የተመቹ እንዲሆኑ ያደርጋቸውል። ኢትዮጵያ ቡና በተቃራኒ ሜዳ ላይ ኳስ ተቆጣጥሮ ከተከላካዮች ጀርባ ለመግባት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ ሲያገኝ የተሻለ ይሆናል። ፋሲል ከተማ ቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ ካልመጣ በቀር ለመልሶ ማጥቃት ዝግጁ ሆነው የሚጫወቱት የመስመር አጥቂዎቹ በብዛት ከአማካይ ክፍሉ የተነጠለ አቋቋምም በተቃራኒው ከመስመር አጥቂዎቹ እገዛን ለሚያገኘ የባለሜዳዎቹ የአማካይ ክፍል በቀላሉ የቁጥር ብልጫን የሚያገኝለት ይሆናል። በአንፃሩ የኳስ ቁጥጥሩን ተከትሎ የሚኖረው የኢትዮጵያ ቡና ወደ መሀል ሜዳው የተጠጋ የተከላካዮች ቦታ አያያዝ ደግሞ ለፈጣኖቹ የፋሲል የመስመር አጥቂዎች ከተጋጣሚያቸው የኃላ መስመር ጀርባ የሚኖረውን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ዕድል የሚሰጥ ይሆናል። ከነዚህ ሀሳቦች መነሻነት መሀል ሜዳ ላይ የሚኖረው ፍልሚያ እጅግ ወሳኝ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች የቅብብል ስህተት ሳይሰሩ ተጋጣሚያቸውን ማስከፈት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ቅብብሎቻቸው ከተበላሹም በፍጥነት የማገገም ግዴታ ይኖርባቸዋል። ታታሪ አማካዮችን የያዙት ፋሲሎች ደግሞ የቡናማዎቹን የኳስ ቁጥጥር በሚያቋርጡበት ቅፅበት በተመጠነ ቅብብል የመስመር አጥቂዎቻቸውን በማግኘት የመልሶ ማጥቃቱን በስኬት የማጀመር ሀላፊነት ይኖራቸዋል። ሆኖም በሁለቱም በኩል የሚታየው ይመጨረሻ የጎል ዕድሎችን የመጠቀም ችግር ዛሬም ዋጋ ሊያከፍላቸው ይችላል። በዚህ ረገድ የአብዱርሀማን ሙባረክ አለመሰለፍ ለፋሲል ከተማ ክፍተት የሚፈጥር ሲሆን ግብ ካስቆጠረ ረዥም ሳምንታት ያስቆጠረው ፊሊፕ ዳውዝ እና የመስመር አጥቂዎቹ ራምኬል ሎክ እንዲሁም ኤርሚያስ ሀይሉ በግብ ፊት ስል መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሳምንት ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ የተመለሰው ሳሙኤል ሳኑሚም ሆነ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ደጋግመው የመግባት ዕድል የሚያገኙት የኢትዬጵያ ቡና የመስመር አጥቂዎች እና አማካዮችም በተመሳሳይ የሚያገኟቸውን ዕድሎች የመጠቀም ግዴታ ይኖርባቸዋል።