በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ትላንት ምሽት ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን የሚገኙባቸው ፔትሮጄት እና ስሞሀ ተገናኝተው ፔትሮጄት በሽመልስ በቀለ ሁለት ጎሎች ታግዞ የኡመድ ኡኩሪው ስሞሀን 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ሽመልስ ከጨዋታው በኋላ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የግብፅ ፕሪምየር ሊግ የአምና እና የዘንድሮ የውድድር አመት እንዴት አየኸው? በክለቦች መካከል ያለው ፉክክርስ ምን ይመስላል?
ሊጉ በጣም ጠንካራ ነው። በዚህ ጥንካሬ ውስጥ ደግሞ ብዙ ስራህን ከባድ የሚያደርጉ ውስብስብ እና አስቸጋሪ ነገሮች አሉ። አል-አህሊ ብቻ ነው ከአመት አመት በጥንካሬ እየዘለቀ ያለው። ከዛ ውጭ ያሉ ክለቦች ወጥ የሆነ አቋም የላቸውም ፤ ወጣ ገባ ነው። የማታስበው ውጤት ይመዘገባል። በአጠቃላይ ይህ የሊጉ ጥንካሬ ማሳያ ቢሆንም አሰልጣኝ የሚቀያየርበት፣ ቡድኖች ተዘበራራቂ ውጤት የሚያስመዘግቡበት መሆኑ አንዱ የሊጉ ደካማ ጎን ነው።
ፔትሮጀት ከአምናው ዘንድሮ በተወሰነ መልኩ የተሻለ ቢሆንም የቡድኑ አቋም ጥሩ የሚባል አይደለም። በርካታ ተጨዋቾች ከክለቡ ለቀዋል። አራት አሰልጣኝም በአንድ አመት ውስጥ ቀያይሯል። የቡድናችሁን የዘንድሮ አመት አቋም እንዴት ታየዋለህ ?
ብዙም አስደሳች አይደለም ከባለፈው አመታት ከነበረን ውጤት ብዙም ማሻሻል አልቻልንም። ብዙ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ከቡድኑ ለቀዋል። እኔም በዚህ ቡድን የመቀጠል ሀሳብ የለኝም ፤ ያው ኮንትራት ስላለኝ ብቻ ነው የቆየሁት። ቡድኑ ወጥ አቋም የለውም። ዛሬም ጨዋታውን እንዳያችሑት ነው።
የአንተም አቋም ከአምናው አንፃር በተወሰነ መልኩ ቀዝቅዟል። እስካሁን ሦስት ጎል ነው ያለህ። ለጎል የሚሆን ኳሶችን አመቻችቶ የመስጠት ነገርህም ቀንሷል። የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች መልቀቅ የአሰልጣኝ መቀያየር አንተ ላይ ያሳደረብህ ተፅእኖ አለ?
እውነት ለመናገር ተፅዕኖ አለው አንድ ቡድን ሲረጋጋ ነው አቅምህን አውጥተህ የምትጫወተው። አሰልጣኞች ይቀያየራሉ ፤ የመጡት ሁሉ የራሳቸው ታክቲክ አላቸው። በዛላይ ጥሩ አሰልጣኞች አይደሉም። ልምምድ ላይ ኳስን ከመጫወት ይልቅ በታክቲክ አጥረህው ምንም እንዳትነቃነቅ ያደርጉሀል። የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾችም ከቡድኑ ለቀዋል። አጠገብህ የሚጫወቱ ተጨዋቾች ጥሩ ነገር ሲሰሩ አንተም አብረህ ትወጣለህ። ዛሬ እንኳን እንዳየህው ኳስ እንኳ አደራጅቶ ለመጫወት ፍላጎት የላቸውም ነበር። ባለው ነገር እኔ ጥሩ ነገር እንዳላሳይ ተፅዕኖ አድርጎብኛል። በቀጣይ ወጥተህ ለመጫወት እንኳ ብታስብ በዚህ ቡድን መሆንህ ተፅእኖ ያደርግብሀል። በዛሬው ጨዋታ ወደ ጎል አስቆጣሪነት መመለሴ መልካም ነው። በቀሪው ጨዋታም ጥሩ ለመንቀሳቀስ እሞክራለው።
በግብፅ ሊግ ውስጥ አንድ ኢትዮዽያዊ ክለብን በዋና አምበልነት ሲመራ አንተ የመጀመርያ ነህ። ይህ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ?
አምበል ሆኖ አንድን ቡድን መምራት በጣም ትልቅ ነገር ነው። ኃላፊነት ይሰማሀል ፣ ቡድኑን ለመለወጥ የበለጠ ትሰራለህ። ከዚህ በላይ ደግሞ ከሀገር ወጥተህ እንደ ግብፅ ባለ ትልቅ ሊግ ውስጥ አምበል መሆን የሚፈጥረው ስሜት ቀላል አይደለም። ቡድኑን በአምበልነት እየመራሁ በአራት ጨዋታ ላይ ተሳትፌያለው። ይህም የሆነው ካለኝ አቋምና በቡድኑ ውስጥ ከነበረኝ ቆይታ ነው። እዚህ ደረጃ ደርሼ አምበል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።
አምበልነትህ ጊዜያዊ ነው ወይስ በቀጣይ ቀሪ ጨዋታዎች ቡድኑን እየመራህ ይቀጥላል?
እኔ የቡድኑ ሀለለተኛ አምበል ነኝ። ዋናው አምበል በየጨዋታዎቹ እየተጫወተ አይደለም። በዚህ ምክንያት ከእርሱ በታች ያለሁት እኔ በመሆኔ ነው ዋና አምበል ሆኜ በአራት ጨዋታ ቡድኑን እየመራው የምገኘው። ከዚህ በኋላም እስከ ውድድሩ መጨረሻ ድረስ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር የቡድኑ አምበል ሆኜ እቀጥላለው ብዬ አስባለው።
በአፍሪካ ትልቁ ሊግ ውስጥ ተደላድሎ መጫወት በራሱ ፈታኝ ነው። ከዚህ ባሻገር ደግሞ የአምበልነት ደረጃ መድረስ ምን ያህል ፈታኝ ነው ትላለህ?
በጣም ከባድ ነው። ከብዙ ነገር ርቀህ ስትጫወት የፈለከውን ነገር አታገኝም። ስራ እስከሆነ ድረስ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ተቋቁመህ ስራህን ትቀጥላለህ። ሊጉ በጣም ጉልበት ይፈልጋል ፣ ብልጠትም ይጠይቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ አልፈህ ከ11 ተጨዋቾች መሀል አልፈህ የቡድን አምበል መሆን ከባድ ነው። ይህን እድል በእግርኳስ ህይወቴ አንድ ቀንም ይሆናል ብዬ አስቤ አላውቅም። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ልለያይ ስል አሰልጣኝ ክሩገር በሁለት ጨዋታዎች ከሀዋሳ ከተማ እና ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ጋር ስጫወት አምበል አድርጎኝ ስጫወት የተሰማኝ ስሜት አውቀዋለው። በሜሪክ ቆይታዬ በአንድ ጨዋታ 5 ጎል በማስቆጠርም ታሪክ ሰርቻለሁ። አሁን ደግሞ እዚህ መጥቼ ይህንን የአምበልነት ክብር በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ ።
ግብፅ ከረጅም ጊዜ በኋላ የአለም ዋንጫ ያለፈችበትን ድል ስታስመዘግብ በቅርብ ነበርክ። እንዴት ነበር የነበረው ድባብ የህዝቡ ስሜት ግብፅ የአለም ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ በሊጉ መነቃቃት ላይስ የፈጠረው ተፅእኖ አለ ?
ግብፅ የአለም ዋንጫ ከረጅም ጊዜ በኋላ ማለፉ በህዝቡ ላይ የፈጠረው ስሜት ቀላል አይደለም ። ጨዋታውን በቅርብ ተከታትያለው። የነበረው ድባብ እንዲህ በቃል የምትገልፀው አይደለም። እኔ እንዲህ አይነት ነገር አይቼ አላውቅም ። ካላቸው የገንዘብ አቅም ከክለቦቻቸው ጥንካሬ ፣ ለእግርኳሱ ከሚሰጡት ግምት አንፃር የአለም ዋንጫን ማለፋቸው ያንሳቸዋል። አሁን ሁሉም ለብሔራዊ ቡድናቸው ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን በማሰብ። ሀገሬ ይሄን ብታሳካ ደስ ይለኝ ነበር። ሆኖም የምጫወትበት ሀገር ለአለም ዋንጫ ማለፉ ደስተኛ ነኝ።
ከኡመድ ኡኩሪ ጋር በብሔራዊ ቡድን በአንድ ማልያ ተጫውታችኋል። ትላንት ደግሞ በግብፅ ሊግ በተለያየ ማልያ ተጫውታችኋል። እንዴት ነው ስሜቱ ከጨዋታ በፊት በኋላ አውርታቹ ነበር ?
በብሔራዊ ቡድን ጋር አብሮኝ ከተጫወተ የሀገሬ ልጅ ጋር በተለያየ ማልያ መጫወት በጣም ደስ ይላል። ከጨዋታ በፊት ተደዋውለን ነበር። መልካም እድል ተባብለን ነበር። ከጨዋታም በኋላ ለተወሰነ ደቂቃም ቢሆን አውርተናል። ጎል በማስቆጠሬ ደስተኛ ሆኖ እንኳን ደስ አለህ ሽመልስ ብሎኛል። ፎቶ ተነስተን እሱ ወደ ካይሮ ስለሚሄድ ተለያይተናል።
ኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ወደ መስከረም ወር ገፍቷል። በብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ አቋምም ህዝቡ ደስተኛ አይደለም። ያንተ ሀሳብ ምንድነው ?
ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ። ከሚታየው ነገር አንፃር አንደኛ ችግሩ ያለው ክለቦች ጋር ነው። ክለቦች ጠንካራ አደረጃጀት ቢኖራቸው አሰልጣኞች ተጨዋቾችን በአካል ብቃት በታክቲክ የሚያበቁ ቢሆኑ አሪፍ ብሔራዊ ቡድን ይወጣል። ተጨዋቾችም ቢሆን ባላቸው ክህሎት ላይ ጠንክረው መስራት አለባቸው። ብሔራዊ ቡድን መመረጥ ቀላል አይደለም። ሲጠሩ እንደ ቀላል ማየት የለባቸውም ፤ ሀገርን ወክለው ሊጫወቱ እንደሆነ ማሰብ አለባቸው። ለተጠሩበት ነገር አላማ ሊኖራቸው ይገባል። ተጨዋቾች ጋር ቀልድ ነው ያለው ፤ በጣም ችግር አለ። ከማየው አኳያ ፊትነሳችን ማስተካከል አለብን። ጥሩ ካልሆነ ሁሉም ነው የሚቀድመን። ውድድሩ መራዘሙ ጠቀሜታ አለው ፤ ብሔራዊ ቡድኑን በደንብ ለማየት ይረዳናል። የወዳጅነት ጨዋታ መኖር አለበት። እኛ ሀገር የትኛው ፌዴሬሽን ነው ተሯሩጦ የወዳጅነት ጨዋታ የሚያዘጋጀው? ይገርምሀል በወዳጅነት ጨዋታ ሊጉ ሲቋረጥ እዚህ ያሉት አሰልጣኞች አትሄዱም እንዴ ይሉናል። ምን ትላለህ? የወዳጅነት ጨዋታ ቢኖር መጥተን መጫወት እንፈልጋለን። ይህ ነገር መስተካከል አለበት። ሁልጊዜ ወሬ ብቻ ነው። 5 – 0 ፣ 4 – 0 ተሸነፉ አንባላለን ፤ በቃ። ሁላችንም ከልባችን እንስራ። በደጋፊው አልፈርድም ፤ ስላልሰራን ነው የሚናገረን። ከሰራን ሁሉም ከኛ ጎን ይሆናል።