የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞች እና ሙያ ታዛቢዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ሰሞኑን አሰልጣኞች በዳኝነት ላይ በሚሰጧቸው አስተያየቶች እና ማህበሩ በቀጣይ ሊወስድ ያሰባቸውን እርምጃዎች እንዲሁም ዕቅዶቹን አስመልክቶ ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቡን አካፍሏል።
ማህበሩ እንደማህበር ያለው ቁመና ምን ይመስላል? መስራት የሚጠበቅባቸው ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብላችሁ ታምናላችሁ?
ማህበሩ የተለያዩ ስራዎችን ይሰራል። መብት ከማስጠበቅ አኳያ ስራዎችን እየሰራን ነው ያለነው። በአመት ውስጥ እቅድ አውጥተን ነው የምንንቀሳቀሰው። የእቅዱን የተወሰነ ነገር ሙሉ ለሙሉ ማለት ባይቻልም የቀሩንንም እናሳካለን። በተወሰነ መንገድ እየተንቀሳቀስን ነው የምንገኘው። ያን በሂደት እናሳካለን። አሁን ከጥቅም አኳያ የዳኛ የሙያ እና የውሎ ክፍያ የሚከፍሉት ክለቦች ስለሆኑ ከነሱ አኳያ እየተንቀሳቀስን ነው። በቀጣይ ደግሞ የክለቦችን ዋስትና በማይነካ መልኩ ማስጠበቅ እና ከክፍያ ጋር ዳኛው ተጨማሪ የማሻሻያ አበሎችን በሚገኝበት ጉዳዮች ዙሪያም እየሰራን ነው። አንድ ዳኛ በሄደበት ሁሉ በሰለም አጫውቶ የሚመጣበትን መንገድ ከፌድሬሽኑ ጋር በመሆን እየሰራን ነው ያለነው። ሀሳባችንንም ሆነ እቅዳችንን እንተገብራለን ብለን እናስባለን፡፡ በርግጠኝነትም እንሰራዋለን ብለን ተነስተናል። ፌድሬሽኑም በዚህ አመት ይሁን በቀጣዩ አመት የዳኞች የሙያ እና የውሎ አበል ይጨምራል የሚባል ነገር አለ። ያን ተግባራዊ ለማድረግ እና ዳኛውን ተጠቃሚ ለማድረግ እንጥራለን፡፡
በዳኞች ላይ የሚሰሙ ቅሬታዎች አግባብነት ያላቸው እንዳሉት ሁሉ የስፖርት ቤተሰቡ ከግንዛቤ እጥረት እና ህጎችን በአግባቡ አለመረዳትም ምክንያታዊ ያልሆኑ ቅሬታዎች ሲሰሙ ይስተዋላል። ይህን ለመቅረፍ የዳኞች ማህበር አዳዲስ ህጎችን ለስፖርት ቤተሰቡ የማስተዋወቅ ፣ አጠቃላይ የእግርኳስ ህግጋት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሲሰራ የማይታየው ለምንድነው ?
በቅድሚያ ፊፋ ነው ህጎችን እያሻሻለ በየአመቱ እና በየጊዜው የሚዘጋጀው ይሄ ሲመጣ አባል ፌድሬሽኖች ጋር ይደርሳል። ፌድሬሽኖች ደግሞ በሰርኩላር ደብዳቤ ለክለቦች ይበትናሉ። 2017/18 ከተሻሻሉ ህጎች ላይ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ዳኞች እና ኮምሽነሮች ከፊፋ በተገኘ እርዳታ ተምረዋል። ልጆቹን ግን ወጥ የሆነ ትምህርት ሰጥቶ ወደ አንድ ሙያ መግባት ነበረበት። ነገር ግን ከወጪ አንፃር በኛ ማህበር ብቻ የሚሸፈን አይደለም። አንድ ቦታ ላይ ብቻ ሰብስቦ ለማስተማር በትንሹ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ወጪን ይጠይቃል። ከተለያዩ ቦታዎች ነው እነዚህ ዳኞች የሚመጡት። ፌድሬሽኑ በብሔራዊ ዳኞች ማህበር አማካኝነት ውድድር ከመጀመሩ በፊት ስልጠና ይሰጥ ነበር። ዘንድሮ ከምን ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ እንዳልተሰጠ አልገባኝም። በየአመቱ ብሔራዊ ፌድሬሽኑ ከዳኞች ኮሚቴ ጋር በመሆን ማሻሻያ ስልጠናዎችን ይሰጥ ነበር ዘንድሮ ግን አልተሰጠም፡፡ ለስፖርት ቤተሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንፃር ከፌድሬሽኑ ጋር በመሆን በጋራ የምንሰራው ስራ ነው። ይህም በኛ ከእቅድ ውጭ ስለሆነ እንጂ መሰራት ያለበት የግዴታ ተግባር ነው። ምክንያቱም የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች የሚጀመረው ህግን ካለማወቅ ነው። ግን አሁን ላይ እየተቸገርኝ ያለነው ህግ እናውቃለን በሚሉት አካላት ላይ ነው። በተለይ በአሰልጣኞች አካባቢ ከፍተኛ ችግር እየመጣ ነው ያለው። ስለዚህ እነዛም ሰዎች ሊቆጠቡ ይገባል። አንዳንድ ክለቦች ለክለብ ተጫዋቾቻቸው ትምህርት እና የዳኝነት ህጎችን ያስተምራሉ። ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ እኔ እስከማውቀው ድረስ በሚገባ ስልጠና ሰጥተዋል። እንደዚህ አይነት ትምህርት ክለቦች ሲሰጡ የሚደገፍ ነው። ምክንያቱም ህግን ካለማወቅ ይመጡ ከነበሩ ችግሮች አንፃር ህጉን ያወቀው ተጨዋች ውሳኔን በፀጋ የመቀበል አቅሙ ከፍተኛ ነው። ሌሎቹም ክለቦች ተመሳሳይ ስራን ይሰራሉ ብዬ አስባለው። በማንኛውም ክለብ ውስጥ የተሻሻለውንም የድሮውንም ህግ ተጨዋቾች ቢማሩ በየጊዜው የተሻለ ነገር ይኖራቸዋል። ምክንያቱም ህግን ካለማወቅ ተጨዋቾች በአንድ ጨዋታ ቀይ አይተው አራት እና አምስት ጨዋታዎች ይቀጣሉ። ህጉን ቢያውቁ ኖሮ ግን ተጫዋቹ በሚገባ ክለቡን ማገልገል የሚችልበት አግባብ ይኖራል። በመሆኑም ፌድሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ክለቦችም ኢንስትራክተሮችን በመመደብ ቢያስተምሩ የተሻለ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡
ዳኞቻችን በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር እና ራሳቸውን እንዲያስከብሩ የሚያበረታቱ ስራዎች ሲሰሩም እምብዛም አንመለከትም…
እሱ ይሰራል። ዳኞችን በራስ መተማመን ማብቃት ማለት ህጉን በቅድሚያ በደንብ እንዲያውቁት ማድረግ ማለት ነው። አብዛኛው ዳኞች አሁን ላይ ከኢንተርኔት ላይ የሚገኙ ናቸው። ከጊዜው ጋር በተያያዘ አሁን ላይ የመተርጎም እና የመረዳት ነው። ከኢንስትራክተሮች የሚጠበቀው ደግም በፊልምም ሆነ በተለያዩ አማራጮች እያስደገፉ ማስረዳት ነው እንጂ ዳኛው በአሁን ሰአት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ራሱን ለማብቃት በየቀኑ ይጥራል። ማህበሩም ስለፈለገ ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን ተሻሽለው በማደግ ከፍ ወዳለ ቦታ መድረስ ስለሚፈልጉ ራሳቸውን በብዙ መንገድ ለማሻሻል ዝግጁ ናቸው ብዬ አስባለው፡፡
በሌሎች ሀገራት ከፊፋ ህግ በተጨማሪ የየራሳቸው ህጎች ሲያወጡ ይታያል። እኛም ሀገር የዳኛን ውሳኔ ያለመቀበል፣ የዳኛ ውሳኔን ለማስቀየር የሚደረጉ ጫናዎች፣ ዳኛን ለማጭበርበር የሚደረጉ ሙከራዎች እና የመሳሰሉትን ለመቀነስ የሚረዱ ተጨማሪ ህጎች ፌዴሬሽኑ እንዲያወጣ የእናንተ ጥረት እና ግፊት ምን ያህል ነው ?
ይሄ ህግ ሳይሆን ደንብ ነው። በአንድ ሀገር ለምሳሌ እንግሊዝን ብንወስድ አንድ አሰልጣኝ ከጨዋታ በኋላ ዳኛን ተቃውሞ ከተገኘ ራሱ አስተዳዳሪው አካል ይቀጣዋል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ስያሜውን ከእንግሊዝ እንዳገኘ ሁሉ ሌሎች ነገሮችም አብረው አሉ። ለምሳሌ ዳኛን ሲናገሩ ወይም ፌድሬሽንን ሲናገሩ ምን እንደሚያስጠይቅ በደንብ ላይ አለ። አሁን ላይ ያን የመተግበር እና ያለመተግበር ጉዳይ ነው እንጂ ሜዳ ላይ እንዳልኩት ዳኞች ራሳቸውን ለማብቃት ብዙ ነገር ይሰራሉ። የአካል ብቃታቸው ፊት ሆኗል ተሯሩጠው ያጫውታሉ። ያን አድርገው ከሜዳ ከወጡ በኃላ አሰልጣኞች ከጨዋታ በኃላ የሚሰጡት አስተያየት በጣም የዳኛውን ስሜት የሚጎዳ እና የሚነካ ነው። ምክንያቱም ከዚህ በፊትም ሁለት ሶስት አሰልጣኞች እንደዚህ በዳኛ ላይ ቀለል ያለ ነገርን ብለዋል። ባለፈው ግን በ13ኛው ሳምንት ደደቢት 3ለ2 በጅማ በተሸነፈበት ጨወታ የደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የሰጠው አስተያየት በጣም አስነዋሪ እና ለማንምኛው ዳኛ እና ታዛቢ ስሜት የጎዳ ነው። በደደቢት በኩል በእለቱ ጌታነህ በቀይ ወጥቷል። ጌታነህ ፕሮፌሽናል ተጫዋች እንደመሆኑ መጠን የሰራውን ጥፋት እና ስህተቱን አምኖ ቀዩን በፀጋ ተቀብሎ ከሜዳ ወጥቷል። ያለምንም እንከን ሜዳ ላይ የምናየውን አይነት መልካም ተግባርን አሳይቶ ከሜዳ ወጥቷል። ነገር ግን አሰልጣኝ ንጉሴ የሰጡት አስተያየት በፍፁም በእለቱ ያጫወተውንም ዳኛ ሆነ ሌላውን ዳኛ የሚወክል አይደለም። በዚህ አጋጣሚ ውድድሩን ሆን ብለው የሚበጠብጡት እነሱ የሚሰጡት አስተያየት ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስን እንዳያድግ የሚያደርጉት ዳኞች ናቸው ብሎ በድፍረት ተናግሯል። እኛም ደብዳቤ አስገብተናል። የዳኞች እና የዲሲፕሊን ኮሚቴም ይሄንን ነገር በሚገባ እየተከታተለ ነው። የተናገረውም ነገር ዳኛውን የሚያንቋሽሽ ነው። ደደቢት እየመራ ያለ ቡድን ነው። ለ12 ሳምንትታ ደደቢት ሊጉን ሲመራ ከዩጋንዳ ወይም ከኬኒያ አይደለም ዳኛ አምጥተን ስናጫውት የነበረው። እስከ አሁንም ክለቡ ሲጫወት በ13 ጨዋታ ላይ በኢትዮጵያዊያን ዳኞች ነበር ሲመራ የነበረው። በ13ኛ ሳምንት ግን የመጀመሪያውን ሽንፈት ሲያስተናግዱ ለምን ተሸነፍን ብለው እ.ራሳቸውን ከመፈተሽ ይልቅ በዳኛ ላይ ማላከክ ተገቢ አይደለም። የደደቢት ደጋፊም ይሁን አዲስ አበባ ስቴዲየም የነበረ የጅማ ደጋፊም የፌድሬሽኑም አመራር ጨዋታውን አይተውታል። ጌታነህም የሰራውን አይተዋል። እሱ በፀጋ ተቀብሎ ቢወጣም አሰልጣኙ የሰጡት ምላሽ ራሳቸውን ወደ ውስጥ ከማየት ይልቅ ወደ ዳኛ ጣታቸውን የመቀሰርን መርጠዋል። ደደቢት ትልቅ ክለብ ነው። ኢትዮጵያን ወክሎ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫም ሆነ በቻምፒየንስ ሊግ ተካፍሏል። ይህ ግን የክለቡ አቋም ነው ብዬ አላምንም። አስተያየቱ የአሰልጣኙ ሀሳብ ብቻ ነው ብዬ አምናለው። ጨዋታው ካለቀ በኃላ ነበር ሀሳቡን የሰጡት። ዳኛ እንደሌለ ፣ የሚመራ ፌድሬሽን እንደሌለ አድርገው ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ባወጣው መርሀ ግብር የሚወዳደር አሰልጣኝ ፌድሬሽኑን የሚመራ አካል የለም ብሎ ነው የተናገረው። እናም ፌድሬሽኑም ይህን በዝምታ የሚያልፈው አይደለም። የዲሲፕሊን ኮሚቴም ቢሆን እኛም በደብዳቤ እንጠይቃለን። ገና በአንደኛው ዙር እንዲህ አይነት ነገር ከመጣ በሁለተኛው ዙር ሌሎች ክለቦችም እንዲህ አይነቱን ነገር በዳኞቻችን ላይ ማድረጋቸው ስለማይቀር የዳኞች ማህበርም ሆነ የዳኞች ኮሚቴ እርምጃ ይወስዳል። አሁን ላይ ይህን ሁሉ ህዝብ ወክሎ ኢትዮጵያን በቻን እያስጠራ ያለው ዳኛ ባምላክ ተሰማ አለ። ሚሊዮን ህዝብ ወክሎ እየሰራ ያለም ዳኛ ነው። በዚህ ውሰጥ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የለም። አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየተወከለች ያለችው በዳኞቻችን ነው። በተለያየም ጊዜ በአፍሪካ የውድድር መድረኮች ላይ በርካታ ዳኞች ይወጣሉ ካፍ እና ፊፋ ዳኞቻችንን አምነው ሲመድቡ አሰልጣኞች ከሚሰጡት የወረደ ንግግር ሊቆጠቡ ይገባል፡፡
የአሰልጣኞችም ሆነ ሌሎች አካላት የሚሰጡት አላስፈላጊ አስተያየት በዳኞት ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ ይኖረዋል?
ከሀገር ወጥተህ ስታጫውት በጣም ቀላል ነው። ለምን አሰልጣኙ ፣ ተጫዋቹ እና አመራሩ አስተሳሰቡ ፕሮፌሽናል ነው። እኛ ሀገር ግን የሚሰነዘሩ ቃላቶች ገና እያደገ ያለውን እግር ኳሳችንን የሚገድል ነው። ነገር ግን ዳኞች በዚህ አይደናገጡም። ከአሁን በኃላ ግን ለዳኞቻችን አስፈላጊውን ከለላ እናደርጋለን። ተፅዕኖ አድራጊው ላይም እርምጃ እንዲወሰድ እናደርጋለን እንጂ ዳኞቻችንን በንግግሩ ተፅዕኖ ስር እንዲወድቁ አናደርግም። አሁን ላይ ችግሩ የሚታየው አሰልጣኞች ላይ ነው። ሽንፈትን ከማመን ይልቅ ዳኛውን እየወቀሱ መውጣት ሆኗል የአሰልጣኞች አላማ። አሰልጣኞች ከአሁን በኃላ ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል እንጂ ሊወቅሱን አይገባም። ይህን አይነት ድርጊቶች ሲፈፀሙ የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ በፊት የያዝናቸው አሉ። ዳኛ አሸነፈን ፣ በዳኛ ተሸነፍን ፣ ዳኛው ነው የተጫወተው የሚባሉ ነገሮች አሉ። ካሜራ በማይደርስበት ቦታ ላይ ሙሉ ለሙሉ ዳኞችን ጥፋተኛ ነው የሚያደርጉት። በዚህ ጊዜ ዳኞች ገምግመው ጥፋተኛውን በኮሚሽነሩ አማካኝነት እንዲያቀርቡ ይደረጋል። ካሜራ ባለበት ቦታ ለምሳሌ ሚዲያዎች በሚደርሱበት ሁሉ ግን ሁሉም ሊማር በሚቻልበት መልኩ እዚህ አሰልጣኝ ላይ ፌድሬሽኑ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ነው የኛ አቋም፡፡
ከዚህ በኃላስ ማህበሩ አፋጣኝ እርምጃዎች በሚወጣው ደንብ መሠረት እንዲወሰን ለማድረግ ያለው ተነሳሽነት?
ደንቡ ላይ ተፅፏል። ፌድሬሽኑንም ሆነ የፌዴሬሽን አመራሮችን እንዲሁም ዳኞችን በግልፅ የሚናገር በዲሲፕሊን መመሪያው ላይ ቁጭ ብሏል። አሁን የመፈፀም እና የማስፈፀም ብቻ ነገር ነው የሚቀረው። አሰልጣኙ የሰጠው አስተያየት ለቀጣዮቹ ጊዜያት አንድ አሰልጣኝ ከጨወታ በኃላ የሚሰጠው አስተያየት ዳኞችንም ሆነ ፌድሬሽኑን የሚነካ ከሆነ ያ አሰልጣኝ ይቀጣል ይላል። ስለዚህ ያን የመፈፀም እንጂ ደንብ የለም ማለት አይደለም። አሁን ላይ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማስታወሻ ሀሳብን ዲሲፕሊን ኮሚቴው አይቶ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ማህበሩ ከዳኞች ጎን ይቆማል። ይህም አንዱ የማህበሩ አላማ ስለሆነ ነው የዳኞትን መብት ማስጠበቅ። ዛሬ ዳኛ ላይ መጥቷል ነገ ታዛቢወች ላይ ስለሚመጣ ከዚህ በኃላ እርምጃችንን በጥብቅ አጠናክረን እንቀጥላለን ፡፡