የኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 8ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሀ ግብር ሁለቱ የሊጉ ጠንካራ ቡድኖች የሆኑት ደደቢት እና ንግድ ባንክን ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ሁለቱም ቡድኖች የሦስት ጊዜ ቻምፒዮን በመሆን የበላይነታቸውን ያሳዩ ቡድኖች እንደመሆናቸው ሁሌም እርስ በእርስ ሲገናኙ ጠንካራ ፉክክር ይስተናገድበታል። በዛሬው እለት የተመለከትነውም ይሄንኑ ሀቅ ነው ።
በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ፣ ወደ ጎል በሚደረግ እንቅስቃሴ ፣ ተጭኖ በመጫወት እንዲሁም ጠንካራ የጎል ሙከራ በማድረግ ንግድ ባንኮች ከደደቢቶች ፍፁም የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው በተጀመረ 2ኛው ደቂቃ ታሪኳ ደቢሶ ከርቀት መትታ ለጥቂት በግቡ አናት የወጣው ኳስም የመጀመርያ ሙከራ ነበር። በ9ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው ሚዛኗን ሳትቆጣጠር ያመከነችው ነፃ ኳስም ጎል መሆን የሚችል ሌላው አጋጣሚ ነበር። ከሦስት ደቂቃ በኋላ ንግድ ባንኮች በጥሩ ቅብብል ኳሱን ወደ ደደቢት የግብ ክልል ገፍተው ዙሌካ ጁሀድ ለረሂማ ዘርጋው ረሂማ ደግሞ በነፃ አቋቀም ላይ ለምትገኘው ሽታዬ ሲሳይ አቀብላት ሽታዬ ሲሳይ ጎል አስቆጠረች ተብሎ ሲጠበቅ ያመከነችው ኳስም በሚያስቆጭ ሁኔታ ጎል ሳይሆን ቀርቷል። የባንክ ጫና በ17ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍቶ ዙሌካ ጁሀድ በጥሩ መንገድ ያሳለፈችላትን ኳስ ዘንድሮ በጥሩ ብቃት ላይ የምትገኘው ረሂማ ዘርጋው አስቆጥራ ንግድ ባንክን መሪ ማድረግ ችላለች።
ደደቢቶች ቀድመው በሚታወቁበት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት አጨዋወትም ሆነ አጥቂዎቹ በሚታወቁበት የማጥቃት አቅማቸው እጅግ ተዳክው በተመለከትንበት በዛሬው ጨዋታ መረጋጋት አቅቷቸው ኳሱን እንኳ በአግባቡ መቀባበል ሲሳናቸው አይተናል። እስከ 36ኛው ደቂቃ ድረስ በዚህ መንገድ የዘለቁት ደደቢቶች በዚሁ ደቂቃ ግብ ጠባቂዋ ንግስቲ እና ተከላካይዋ ሳይናበቡ እርስ በእርስ ተጋጭተው የተተፋውን ኳስ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ሎዛ አበራ ጎል አስቆጥራ ደደቢቶችን አቻ ማድረግ ችላለች ። ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ ተመጣጣኝ ፉክክር ለማየት ብንችልም ተጨማሪ ጎሎች ሳንመለከት የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ተፈፅሟል።
ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ጠንካራ ፉክክር ቢደረግም የጎል እድል በመፍጠር ረገድ የነበራቸው እንቅስቃሴ ደካማ ሆኖ ታይቷል። በሁለተኛው አጋማሽ እንደ ጎል ሙከራ ሊጠቀስሚችለው በ62ኛው ደቂቃ የቀድሞዋ የንግድ ባንክ አማካይ ብሩክታዊት ግርማ ከርቀት መሬት ለመሬት መትታ የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣው ኳስ ብቻ ነበር።
ደደቢቶች ተጭነው ለመጫወት እና ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የደደቢት የአማካኝ ስፍራ ተጨዋቾችን ምንም አይነት ክፍተት እንዳያገኙ ሰው በሰው የመያዝ አጨዋወታቸውና በንቃት ተጠንቅቀው በመከላከላቸው የተሻለ የግብ አጋጣሚ እንዳይፈጥሩ ሆነዋል። ንግድ ባንኮች በአንፃሩ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት የተጨዋች ቅያሪ እና የነበራቸው የመጫወት ተነሳሽነት ጥሩ ሆነው እንዲወጡ አግዟቸዋል። የደደቢት የአማካኙ እና የአጥቂው ክፍል እንደ ከዚህ ቀደሙ አስፈሪነቱ በዘንድሮ አመት በተወሰነ መልኩ ሲከዳው የተመለከትን ሲሆን በአንፃሩ ንግድ ባንኮች ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻሉ የመጡበትን እንቅስቃሴ አሳይተዋል። የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽም የረባ የጎል ሙከራ ሳንመለከትበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
በሌላ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ትላንት ድሬዳዋ ላይ 10:00 ላይ በተደረገ ጨዋታ ድሬደዋ ከተማ መቅደስ መስረሻ በ61ኛው እንዲሁም ተራማጅ ተስፋዬ በ79ኛው ደቂቃ በስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ታግዘው ጌዲዮ ዲላን አሸንፈዋል።