በ14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዓዲግራት ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ 1-0 በማሸነፍ ከ8 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።
በወልዋሎ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጀመረው ጨዋታ ቢጫ ለባሾቹ ከድር ሳልህ በተሰለፈበት የግራ መስመር አዘንብለው የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ የተስተዋለ ሲሆን ሀዋሳዎች በአንፃሩ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በሙሉው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መውሰድ ችለዋል። እንግዶቹ በጨዋታው የመጀመርያውን ሙከራም ማድረግ የቻሉ ሲሆን በ6ኛው ደቂቃ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ በበረከት አማረ ተመልሶበታል።
በ11ኛው ደቂቃ ላይ ከድር ሳሊህ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጫዋቾችን በማለፍ ለፕሪንስ ሰቨሪንሆ ያመቻቸለትን ኳስ ቡርኪናፋሷዊው የመስመር አጥቂ በግምት 30 ሜትር ርቀት አክርሮ መትቶ ወደ ግብነት በመለወጥ ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከጎሏ መቆጠር በኋላ ወልዋሎዎች ወደኋላ በማፈግፈግ እና በማጥቃት እንቅስቃሴው ቀስ በቀስ መቀዛቀዝ ማሳየታቸው ሀዋሳዎች ጨዋታውን እንዲቆጣጠሩ በር ከመክፈቱ ባሻገር ያለቀላቸው የጎል እድሎችንም እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል። በተለይም በ35ኛው ደቂቃ እስራኤል ከታፈሰ ሰለሞን የተላከለትን ኳስ ወደ ግብ መትቶ ኳሷ ግብ ጠባቂው በረከትን አልፋ ብትሄድም በረከት ተሰማ እንደምንም ጎል ከመሆን ያገዳት ሙከራ ሀዋሳን አቻ ልታደርግ የተቃረበች እድል ነበረች።
በአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች እና የወልዋሎ ተጫዋቾች ሰዓት ማባከን ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ በ42 ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል የተገኝውን ቅጣት ምት ሙሉዓለም ረጋሳ መትቶ ወደ ጎልነት ቢቀየርም የእለቱ ዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ጎሏን በመሻራቸው የተነሳ በሃዋሳ ከተማ አሰልጣኞች ቡድን እና በዋና ዳኛው መካከል ለደቂቃዎች የቆየ አለመግባባት ተስተውሏል።
በመጀመርያው አጋማሽ የአቻነቷን ግብ ለማግኝት ሀዋሳ ከተማዎች ተጭነው ቢጫወቱም ጎልና መረብ ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በ44ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው እስራኤል ከፍ.ቅ.ም ክልል ጠርዝ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ወደ ላይ የወጣበት ሙከራም ከእረፍት በፊት ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ እንደመጀመርያው ሁሉ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ቢችልም በ4 ተከላካይ እና 2 ለተከላካይ ክፍሉ ሙሉ ሽፋን በሚሰጡ የተከላካይ አማካይ ተጫዋቾች የተዋቀረው የመከላከል አደረጃጀትን ሰብረው ጎል ማስቆጠር ተስኗቸዋል።
በ2ኛው አጋማሽ ጅማሮ ሙሉዓለም ረጋሳ በረጅም ኳስ ነፃ አቋቋም ለነበረው ሲይላ መሀመድ አቀብሎት አይቮሪኮስታዊው ሞክሮ በግቡ ቋሚ ለጥቂት የወጣችበት በ70ኛው ደቂቃ ጋብሬል አህመድ እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ እስራኤል እሸቱ የሞከሯቸው ሙከራዎች በሀዋሳ በኩል የሚያስቆጩ ነበሩ። በአንፃሩ በወልዋሎ በኩል በ68ኛው ደቂቃ ላይ ዋለልኝ ገብሬ በረጅሙ መትቶ የግቡ አግዳሚ ከመለሰበት ሙከራ ውጭ አመዛኙን ክፍለ ጊዜ በራሳቸው ሜዳ ክፍል በመገደብ እና ተከላክለው በመጫወት ያስቆጠሩትን ጎል በማስጠበቅ ጨዋታውን በአሸናፊነት መወጣት ችለዋል።
ድሉን ተከትሎ ከ5ኛው ሳምንት በኋላ ሶስት ነጥብ ማግኘት ተስኖት የቆየው ወልዋሎ ከ8 ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ሲመለስ ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ 6ኛ ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታው ሆኖ ተመዝግቧል።
ከጨዋታው በኋላ የወልዋሎው ጊዜያዊ አሰልጣኘረ ሀፍቶም ኪሮስ ” በተጫዋቾቼ ጥረት እና በደጋፊያችን ልዩ ድጋፍ የምንፈልገውን አሳክተናል” ሲሉ የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ” ሙሉ የጨዋታ ብልጫ ነበረን። ወልዋሎዎች ባገኙት አንድ አጋጣሚ አሸንፈውን ወጥተዋል። ጨዋታው ውጤቱን አይገልፀውም” ብለዋል።