የቀን ለውጥ ተደርጎበት ዛሬ የተካሄደው የሱሉልታ ከተማ እና የሽረ እንዳስላሴ ጨዋታ በያያ ቪሊጅ ተደርጎ በሱሉልታ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጨዋታውን እስከማቋረጥ ያደረሱ ውዝግቦችም ተከስተውበታል።
በርከት ያለ ደጋፊ በታደመበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 20ኛው ደቂቃ ድረስ ይህ ነው የሚባል የጎል ሙከራ ያልታየበት ነበር፡፡ በአንፃራዊነት አምበሉ ንጉሴን በ5 ቢጫ ቅጣት ምክንያት ሳይዙ ወደ ሜዳ የገቡት ሱሉልታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ሽረዎች ረቡዕ ዕለት ከተጠቀሙበት ስብስባቸው መጠነኛ ለውጥ ያደረጉ ቢሆንም በእንቅስቃሴ እስከ መጀመሪያው አጋማሽ ድረስ በተጋጣሚያቸው ተበልጠው ታይተዋል፡፡
በ20ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የሱሉልታው ቢኒያም አማረ ከፍ አድርጎ የግብ ጠባቂውን አቋቋም በመመልከት የመታውን ኳስ የሽረ ግብ ጠባቂ ሙሴ ዮሐንስ እንደምንም ብሎ ወደ ማዕዘን ቢያወጣትም ግብ ጠባቂው ኳሱን ለማዳን ሲሞክር የግቡ ቋሚ ገጭቶት በመውደቁ ለአንድ ደቂቃ ያህል የህክምና እርዳታ ከተደረገለት በኃላ ነበር ወደ ጨዋታው የተመለሰው፡፡ በ25ኛው ደቂቃ ይድነቃቸው የሺጥላ ከማዕዘን የተመታውን ኳስ በግንባሩ ቢገጭም በሽረ ግብ ጠባቂ ሙከራው ወደ ግብነት ሳይለወጥ ቀርቷል፡፡
ረዣዥም ኳሷችን ወደ ፊት በመጣል የባለሜዳው ተከላካይ ክፍል ርቆ እንዳሄድ ያደረጉት ሽረዎች በ30ኛው ደቂቃ በልደቱ ለማ የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገዋል፡፡ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ልደቱ በግንባሩ ለማስቆጠር ቢጥርም በሱሉልታ ከተማ ግብ ጠባቂ ከሽፎበታል፡፡ በቀኝ መስመር ለሱልልታ ከተማ ፈተኝ ሁኖ የነበረው ብሩክ ገብረአብም በ36ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ወደ ፊት የጣለው ኳስ በድጋሚ ልደቱ ለማ አግኝቶ ቢመታውም በግቡ አግዳሚ በግራ በኩል ወጥቶበታል፡፡
በ39ኛው ደቂቃ ባለሜዳዋቹን ቀዳሚ እና አሸናፊ ያደረገችውን ግብ ኢሳያስ አለምእሸት አስቆጥረዋል፡፡ ከቀኝ መስመር እንዳለ ዘውገ ያሻገረውን ኳስ ኢሳያስ አለምእሸት በግንባሩ በመግጨት ነበር ኳስን ከመረብ ጋር ያገናኘው፡፡ ለመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ በነበረችው ሙከራ ደግሞ 42ኛው ደቂቃ ላይ ንስሃ ታፈሰ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ከግራ መስመር ቀጥታ ይዞ የገባውን ኳስ አክርሮ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ብዙአየው አስፋው አድኖበታል፡፡
ከዕረፍት መልስ የጨዋታውን ድባብ የለወጡ ድርጊቶች ተፈፅመዋል፡፡ ውጤቱን ለመለወጥ ጫን ብለው መጫወት በጀመሩት ሽረዎች በኩል በ48ኛው ደቂቃ ብሩክ ገብረአብ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገ ሲሆን በሌላኛው ፅንፍ ደግሞ 55ኛው ደቂቃ ላይ የሱሉልታው አድማሱ ጌትነት ለኢሳያስ አለምእሸት ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ የሽረ ተከላካይ ደርሶበት ሙከራውን አክሽፎበታል፡፡
በ58ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የቀኝ መስመር ተመላላሹን እንዳለ ዘውገን ተክቶ የገባው ስታየው በረዥሙ የተሸገረትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ንፁህ የማግባት ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ግን የሁለቱ ቡድን አመራሮች አራተኛ ዳኛ ባለበት ዱላ ቀረሽ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው ታይተዋል፡፡ ለሁኔታው መፈጠር መንስኤ የነበረው ከጨዋታ ውጭ የነበረን ኳስ ለማስጀመር የኳስ አቀባዩ በሰዓቱ ኳሱን ባለማቀበሉ የሽረው ተጫዋች ከአንደበቱ ስድብ በመውጣቱ ሲሆን የሱሉልታው ምክትል አሰልጣኝ ሰለሞን አዳነ ከሽረ አሰልጣኝ ጋር እስጣ ገባ ውስጥ ገብተዋል። በዕለቱ የነበሩት አራተኛ ዳኛም የሁለቱንም የቡድን መሪዎች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ለማረጋጋት ጥረት አድርገዋል፡፡
ሆኖም 67ኛው ደቂቃ ላይ የሽረው አሸናፊ እንዳለ በሱልልታ ከተማ ተጫዋች ላይ የማይገባ ጥፋት ከመስራቱም በላይ የወደቀውን ተጨዋች ለመማታት በመቃጣቱ ፊሽካ ያሰማው ዳኛ ወደ ተጨዋቹ በሚሮጥበት ቅፅበት የሱሉልታ ከተማ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በየቦታውም የተጨዋቾች የአንድ ለአንድ ፀብ ታይቷል። በአንጻሩ ደሞ የሱሉልታ ከተማ አንዳንድ ተጨዋቾች ፀቡን ለማብረድ እና ለማረጋጋት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በቂ የፀጥታ ሀይል በቦታው ያልነበረ ከመሆኑ በተጨማሪም የነበሩትም ፀቡን ለማብረድ ያደረጉት ጥረት አነስተኛ ነበር። የሱሉልታ ከተማ ደጋፊዋች በእግር ኳስ ሜዳ ላይ አላስፈላጊ ቁሳቁስ ይዘው ገብተው የነበረ ሲሆን በሽረው ተጨዋች ልደቱ ለማ ላይ ጥቃት አድርሰዋል፡፡ ተጨዋቹም የከንፈር መሰንጠቅ አጋጥሞታል፡፡
ጨዋታውን መጨረስ ይከብደናል ሲሉ ቅሬታቸው ያሰሙት ሽረዎች ከረጅም ደቂቃ በኃላ ድርጊቱ ለፌዴሬሽን አባላት ከደረሰ በኃላ የፀጥታ ሀይሉ እና የሱሉልታ የቡድን መሪ ሀላፊነቱን እንወስዳለን በማለት ካረጋጓቸው በኃላ ለ25 ደቂቃዎች የተቆረጠው ጨዋታ ካቆመበት ቀጥሏል፡፡ ዳኛው ጨዋታውን በመልስ ምት ከማስጀመራቸው በፊትም ጥፋቱን ለፈፀመው አሸናፊ እንዳለ የቀይ ካርድ አሳይተውታል፡፡ ከዚህ በኃላ በጎዶሎ የተጨዋች ቁጥር ጨዋታውን ለመጨረስ የተገደዱት ሽረዎች በኳስ ቁጥጥር ከሱሉልታ ተሸለው ታይተዋል። በተለይም በ76ኛው ደቂቃ ልደቱ ለማ በግንባሩ እንዲሁም 80ኛው ደቂቃ ላይ በግራ እግሩ የሞከራቸው ኳሶች ለግብ የቀረቡ ነበሩ፡፡
ጨዋታው መገባደጃ ላይ ወደ ውጪ የሚወጡ ኳሶች በትክክል እየቀረቡልን አይደለም በሚል አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ ከአራተኛው ዳኛ ጋር ክርክር ውስጥ ገብተው የታዩበትበት አጋጣሚ ነበር። ጭማሪ ደቂቃ ላይም አንድ የሱሉልታ ከተማ ተጨዋች በመውደቁ ሁለቱ ቡድኖች አላስፈላጊ ፀብ ውስጥ በድጋሚ የገቡ ሲሁን ከዳኛ ዕይታ ውጭ የሽረው ልደቱ ለማ ኳስን በረጅሙ ለግቶ ነበር። ነገር ግን የቡድን መሪዎቹ ወደ ሜዳ በመግባት ሁኔታውን ያረጋጉ ሲሆን ጨዋታውም ከጥቂት ደቂቃ በኃላ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
ከጨዋታውም መጠናቀቅ በኃላ ሽረዎች ቅሬታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ የገለፁ ሲሆን ከዚህም በኃላ እንዲህ አይነት ድርጊት እንደማይፈፀምባቸው ምንም አይነት መተማመኛ እንደሌላቸውና ከዚህ ቀደምም ቅሬታቸውን ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በማሰማት ጨዋታዎቹ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም እንዲዘዋወርላቸው በባህር ዳሩ ጨዋታ ላይ ቢጠይቁም ተቀባይነት እንዳላገኙ ተናግረዋል።