ኢትዮጵያዊው አማካይ ጋቶች ፓኖም ለሙከራ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጪው እሁድ እንደሚያመራ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ ጋቶች በቤድቬስት ዊትስ የሙከራ ግዜውን እንደሚሳልፍ የተጫዋቹ ወኪል ደቬድ በሻ አስታውቋል፡፡
ጋቶች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በውል ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችል ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የነበረው እድል የከሸፈ ሲሆን ከአንዳንድ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ጋር ስሙ ለዝውውር ቢነሳም ከኢትዮጵያ ውጪ ወጥቶ መጫወትን የመጀመሪያ ምርጫው ነበር፡፡ በሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ ጋር የነበረውን 3 ዓመት ውል በስምምነት አፍርሶ ወደ ፈለገው ክለብ የማምራት እድል ነበረው፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሪምየር ሳከር ሊግ ክለብ የሆነው ቤድቬስት ዊትስ ለጋቶች ፓኖም የሙከራ ግዜን ሰጥቶታል፡፡ ጋቶች ለሙከራው ከወኪሉ ጋር በመጪው እሁድ ወደ ጆሃንስበርግ የሚያመራ ይሆናል፡፡
ዴቪድ ስለሙከራው እድል ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ጋቶች ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያመራበትን ቪዛ ሐሙስ ያገኘ ሲሆን ለአንድ ሳምንትም የሙከራ ግዜ እንደሚሰጠው ጠቁሟል፡፡ “ከዚህ በፊት እንደተናገርነው ከሃር ወጥቶ የሚጫወትበትን ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ስንሰራ ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ ነገር ተሳክቶ ለሙከራ ወደ ዊትስ ጋቶች ያመራል፡፡ ሙከራውን በጥሩ ሁኔታ እንደሚያሳልፍ ተስፋ አደርጋለው፡፡ ለአንድ ሳምንት በክለቡ ቆይታ ያደርጋል፡፡ ከሳምንት በኃላ የሚመጣውን አብረን እናያለን፡፡” ብሏል።
ጋቶች ከዚህ አስቀድሞ ወደ ግብፁ ክለብ ዋዲ ደግላ ሊያመራ ከጫፍ ደርሶ በቪዛ ጉዳይ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡
አምና ማሜሎዲ ሰንዳውንስን በመብለጥ የሊጉን ዋንጫ ያሸነፈውና ዘንድሮ በ22 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ አስከፊ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው ቤድቬስት ዊትስ ከዚህ ቀድሞ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን አጥቂዎች ጌታነህ ከበደ እና ፍቅሩ ተፈራ የተጫወቱበት ክለብ ነው።